1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"የእኛ ለውጥ ነው ብለን ስላመንን ነው የመጣንው"- አቶ ዳውድ ኢብሳ

ቅዳሜ፣ መስከረም 5 2011

በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ "ሰላማዊ በሆነ መንገድ ግቡን እንዲመታ" ድርሻውን ለመወጣት ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አስታወቀ። የኢትዮጵያ መንግሥትን ለመጣል ነፍጥ አንግቦ ኤርትራ በረሐ የወረደው ኦነግ አመራሮች በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ገብተዋል።

https://p.dw.com/p/34v8k
Äthiopien Bevölkerung begrüßen OLF-Führungskräfte
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

ዛሬ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት የኦነግ ሊቀ-መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በኢትዮጵያ ታይቷል ላሉት ለውጥ ኦነግ እና ሰራዊቱ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። 

"የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ቄሮ ቢልሱማ ኦሮሞ እንደዚሁም የኢትዮጵያ ወጣቶች እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይኸንን ለውጥ ለማምጣት ሙሉ በሙሉ ተሳትፈውበታል። በዚህ ለውጥ ውስጥ ሙሉ በሙሉ አለን። የእኛ ለውጥ ነው ብለን ስላመንን ነው የመጣንው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ ቡድኖች ይኸንን ለውጥ በሰላማዊ መንገድ እንዲሔድ ወስነው ለዚህ በር ስለከፈቱ ከእነዚህ ጋር ሥምምነት አድርገን፣ ይኸ ለውጥ በጣም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ግቡን እንዲመታ፣ የእኛን ተሳትፎ ለማድረግ ነው ወስነን የመጣንው" ብለዋል የኦነግ ሊቀመንበር።

የኦነግ አመራሮች አዲስ አበባ የደረሱት ዛሬ እኩለ ቀን ሲሆን ከቀናት በፊት ከኤርትራ የተነሱ የኦነግ የሰራዊት አባላትም ዛሬ ጠዋቱን ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀዋል። በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተሰበሰቡ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ የኦነግ ደጋፊዎች አቶ ዳውድ እና አብረዋቸው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ አመራሮች በስፍራው ሲደርሱ በከፍተኛ ሆታ ተቀብለዋቸዋል።

በአቀባበል መርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ፣ የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ በርካታ የኦሮሞ ፖለቲከኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተገኝተዋል። በመርሐ ግብሩ ረዘም ያለ ንግግር ያሰሙት አቶ ዳውድ ለትግሉ አስተዋጽኦ ያደረጉ ያላቸውን በርካታ ግለሰቦችን በስም እየጠሩ ሲያመሰግኑ ተደምጠዋል።

Äthiopien Bevölkerung begrüßen OLF-Führungskräfte
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የኦነግን የአጭር ጊዜ እቅድ በተመለከተ ሊቀመንበሩ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ በኦሮሞ ሕዝብ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አካሔድ ላይ ከድርጅቱ አባላት፤ ከወጣቶች እና ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ውይይት ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል። በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ በሁሉም መስክ ግቡን የሚመታበትን መንገድ ለመቀየስ ኦነግ ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማድረግ እንደሚፈልግም አቶ ዳውድ አስታውቀዋል። 

"በኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ለብዙ ዓመት ትግል የተደረገበት እና ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት ነው። በዚህ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል። ይኸ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን እና ሕዝቡ በራሱ መሪዎቹን ከታች እስከ ላይ እንዲመርጥ እና የፖለቲካ ሥልጣኑን በእጁ እንዲያስገባ ዋንኛ ምኞታችን እና የታገልንበት ነው። በሩቅ ግባችን ከመንግሥት እና ከሌሎች ኃይሎች ጋር ይኸ ሥራ ላይ እንዲውል ምኞታችን እና እቅዳችን ነው" ሲሉ ሊቀመንበሩ አስረድተዋል። 

አቶ ዳውድ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫቸው የሕግ የበላይነትን በተመለከተ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ከዛሬ ጀምሮ ሁሉም ተሳትፎ ማድረግ አለበት ብለዋል። መቀመጫውን በኤርትራ አድርጎ የነበረው ኦነግ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የተስማማው ባለፈው ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁና በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ ከተመራ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን ቡድን ጋር በአስመራ ካደረገው ድርድር በኋላ ነበር። 

ከ42 አመታት በፊት የተመሠረተው ኦነግ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ይመራ የነበረው ደርግ ሲወድቅ የሽግግር መንግሥት ከመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነበር። በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ አራት የምኒስትርነት ቦታዎች የነበረው ፓርቲው ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ጋር ከገጠመው አለመግባባት በኋላ ለቆ የወጣ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት የመከፋፈል ዕጣ ገጥሞታል። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ሥልጣን ከጨበጡ ጀምሮ የተለያዩ የኦነግ አንጃዎች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ