1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእንቅስቃሴ ገደብ መነሳትና መዘናጋት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 22 2013

መላውን ዓለም ያዳረሰው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት አንስቶ ከ3,9 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ፈጅቷል። ከአንድ ዓመት ከ6 ወር በላይ የመላው ዓለም መነጋገሪያ ሆኖ የከረመው ተሐዋሲ ከ181 ሚሊየን በላይ ሰዎችንም መያዙ ተመዝግቧል። ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ጥቂት የማይባሉ ሃገራት ጥለውት የከረሙት የእንቅስቃሴ ገደብ ለቀቅ እያደረጉ ነው።

https://p.dw.com/p/3vlzk
Portugal Urlauber Coronavirus Pandemie
ምስል Pedro Fiuza/Zuma Wire/picture alliance

ጥንቃቄ የሚያሻው ኮቪድ 19

በጎርጎሪዮሳዊው 2019 ታኅሣስ ወር ከቻይና አንዲት ከተማ የተነሳው የኮሮና ተሐዋሲ ቢያንስ 3,932 ሺህ 561 ሰዎችን መፍጀቱ ተመዝግቧል። በተሐዋሲው በአጠቃላይ በመላው ዓለም የተያዘው ሰው ብዛት ደግሞ 181 ሚሊየን 357 ሺህ 670 ደርሷል። ከእነዚህ መካከል አብዛኛው ከህመሙ ማገገማቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ።  ኮቪድ 19 በተለይ በአውሮጳ ሃገራት ላይ አስከትሎት የነበረው ከባድ ጉዳት እና የእንቅስቃሴ ገደብ ጫና ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ ቀለል ያለ መስሏል። ሰዎች ከሀገር ወደ ሀገር ለበጋው እረፍት መንቀሳቀሳቸው ደስታን ቢፈጥርም፤ የወቅቶች መፈራረቅን ተከትሎ የሙቀቱ ጊዜ ሲያልፍ ዳግም ወረርሽኙ እንዳያገረሽ ግን ከወዲሁ ስጋት አለ። 
ላለፉት በርካታ ወራት የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎ በቆየባት ጀርመን ለወትሮ ሰዎች የሚበዙባቸው መንገዶች እረጭ ብለው ብለው ነበር። በየዕለት እጅግ ብዙዎችን ያስተናግዱ የነበሩት ትላልቅ የአልባሳት፣ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁስ መሸጫዎች እንዲሁም ሌሎች መደብሮች እጅግ ጥብቅ በነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ጊዜ ተዘግተው፤ ገደቡ በመጠኑ ለቀቅ ባለበት ወቅት ደግሞ ደንበኞች ፈጣን የኮሮና ምርመራ ውጤት፤ አለያም መከተባቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እያሳዩ በተራ ሲስተናገዱባቸው ከርመዋል። ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ደግሞ ገደቡ በመነሳቱ እነሱም ደንግገውት የነበረውን ቅድመ ግብይት ግዴታዎችን አንስተው ሸማች እንደፈለገውና ከወረርሽኙ መስፋፋት በፊት እንደለመደው በየሱቁ እንደልብ ይገባና ይወጣ ጀምሯል። እንዲህ ያለው ለውጥ በተለይ የሰሜኑን ንፍቀ ክበብ የበጋ እና ሙቀት ወቅት ተከትሉ በመምጣቱ የእረፍት ጊዜን ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ማሳለፍ ለለመደው ጀርመናዊም ሆነ ለአብዛኛው አውሮጳዊ ወረርሽኙ ያስከተለው የእንቅስቃሴ ገደብ ካሳደረበት ድብርት ቀስ በቀስ እንዲላቀቅ የረዳው መስሏል። ልዩነቱም ለመላው ኅብረተሰብ የሚታይ ቢሆንም በተለይ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት በሚሰጥ ዘርፍ ላይ ለተሠማሩ ወገኖች ደግሞ ትርጉሙ ከዚህም በላይ ነው።  ከጀርመኗ ኮሎኝ ከተማ ወጣ ብላ ባለችው ኤንግልስ ኬርሸ ከተባ በቅዱስ ዮሴፍ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሰብለ ወንጌል ይመኔ፤ አሁን ለሚታየው ፋታና ለውጥ ክትባቱ አስተዋጽኦ ሳይኖረው እንደማይቀር ነው የገለጹልን።

የጀርመኑ የተዛማች ተሐዋሲዎች ምርምር ተቋም ሮበርት ኮኽ በየዕለቱ በኾቪድ 19 የተያዙ ሰዎችን አስመልክቶ ይፋ የሚያደርጋቸው ቁጥሮች በጣም መቀነስ ከጀመሩ ከሁለት ሳምንት በላይ ሆኗል። ቀደም ሲል የእንቅስቃሴ ገደብ ይጣል የነበረው ለሰባት ተከታታይ ቀናት ከ100 ሺህ ሰዎች ውስጥ ከ100 በላይ በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች መኖራቸው በምርመራ ከተረጋገጠ ነበር። በመላው ጀርመን እስካሁን ቢያንስ ክትባቱን አንዴ የወሰዱት ሰዎች ቁጥር ከ43,4 ሚሊየን በላይ ደርሷል። በየሀኪም ቤቱ የጽኑ ሕሙማን መታከሚያ የሚገኙትም 781 መሆናቸውን የሮበርት ኮኽ ተቋም መረጃ ያመለክታል። በዚህ መሀል ተቋሙ ዛሬ ይፋ ባደረገው መሠረት ዴልታ የተባለው የኮቪድ 19 ዝርያ አዲስ በተሐዋሲው መያዛቸው በምርመራ ከሚረጋገጥ ጥቂት የማይባሉት ላይ እየተገኘ በመሆኑ የእንቅስቃሴ ገደብ መነሳቱን ተከትሎ ሰዎች ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ ተገቢውን ጥንቃቄ ከማድረግ እንዳይዘናጉ አሳስቧል።
ሀገር ጎብኚዎችን በማስተናገድ ዘርፍ የተሰማሩት ጀርመናዊቱ ሽቴፋን ቦርግማን ባለፉት ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቁት ወራት ተዘግቶ የከረመው የቱሪዝም ዘርፍ ተገልጋዮችን በማስተናገዱ በኩል ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑን ይናገራሉ። 
«አሁን በትክክል አንድ ሰው በቱሪዝሙ መስክ እንዴት ኃላፊነት በተላበሰ መንገድ ሥራውን ማከናወን እንደሚገባው በማወቃችን፤ ራሳችን በአግባቡ ተፈትነናል። ለዚህም አስተናጋጆችም ሆንን እንግዶች ባጠቃላይ በቂ ዝግጅት አድርገናል። ለጉዞ የሚደረገው ምዝገባም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው።»
የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዋ እንደሚሉት በርካቶች ለበጋው ጉዞ ተጋጅተዋል። የአውሮጳ አባል ሃገራት የአየርም ሆነ የየብስ ድንበሮቻቸውን የኮቪድ 19 ክትባት ለተከተቡ፤ በተሐዋሲው ተይዘው ለዳኑ፤ እንዲሁም ተመርምረው በተሐዋሲው አለመያዛቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለሚያቀርቡ የሕብረቱ ሃገራት ዜጎች እና ነዋሪዎች ከፍተዋል። ይኽም በርካቶች ከሀገር ወደ ሀገር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በማስከተሉ ባለሥልጣናት ጉዞውን ሙሉ በሙሉ ለማገድ ባይደፍሩም ሰዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ከማድረግ እንዳይዘናጉ እያሳሰቡ ነው። ከጉዙ መልስ ምርመራ ከማድረግ በተጨማሪ ራሳቸውን ለይተው ከአስር ላልበለጡ ቀናት በቤታቸው እንዲወሰኑም መመሪያ አውጥተዋል። አንዳንድ ሃገራት  እንደውም  ምንም እንኳን ክትባት ለዜጎቻቸው በብዛት ቢያዳርሱም ተሐዋሲው እንደተስፋፋባቸው ከሚነገሩ ሃገራት በረራዎችን እስከ ማገድ ደርሰዋል። ለበርካታ ወራት ከእንቅስቃሴ ተገድቦ እና በየቤቱ ተዘግቶ የከረመው ኅብረተሰብ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነጻነት ማግኘቱ አንድ ነገር መሆኑ ባያነጋግርም ጥንቃቄው ከተጓደለ ወረርሽኙ ዳግም ሊያንሰራራ አይችልም ማለት እንደማይቻል ነው ዶክተር ሰብለ ወንጌል የሚያሳስቡት።

በርካታ የአውሮጳ ሃገራት የእንቅስቃሴ ገደብ ባነሱበት በዚህ ወቅት ሩሲያ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ትግል ይዛለች። በሀገሪቱ ከ5,4 ሚሊየን በላይ በተሐዋሲው የተያዙ ሲሆን ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻም ከ20,616 ሰዎች መያዛቸው ተረጋግጧል። እስካሁንም ሩሲያ ውስጥ  270 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ከተሐዋሲው ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል። በተለይም በዋና ከተማ ሞስኮ እና በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ  በኮቪድ 19 የተያዙና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መበራከቱ ነው የተነገረው።  የኮሮና ክትባቶችን ቀደም ብለው ካዘጋጁት ሃገራት አንዷ በሆነችው ሩሲያ እስካሁን ቢያንስ አንድ ጊዜ ክትባቱን የወሰዱ 23 ሚሊየን ሰዎች ብቻ ናቸው። አፍሪቃ ውስጥ በተሐዋሲው ክፉኛ በተጎዳችው ደቡብ አፍሪቃ 60 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከአህጉሩ የደቡብ አፍሪቃ ይዞታ ጎልቶ ይነገር እንጂ ክትባቱ እንደልብ ባለመገኘቱ እና በሚታየው መዘናጋት ምክንያት በበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ወረርሽኙ በስፋት እንዳይዳረስ ስጋት አለ። ከበለጸጉት ሃገራት በሚገኘው የክትባት አስተዋጽኦ ላይ የተመረኮዘው የአፍሪቃ ሃገራት ፍላጎት አንዳች መፍትሄ እንደሚያስፈልገው ሲታሰብበት ከርሟል። የዓለም የጤና ድርጅትም የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ቴክኒዎሎጂውን በማጋራት አፍሪቃ ራሷን የቻለ የክትባት አምራች ተቋም እንዲኖራት ሃሳብ አቅርቧል። 

በመጀመሪያ ህንድ ውስጥ የተገኘው ዴልታ የተባለው የኮቪድ 19 ዝርያ አሁን የበርካታ ሃገራት ስጋት ሆኗል። የመተላለፍ ፍጥነቱ ከበፊተኛው የበለጠ መሆኑ የተነገረለት ዴልታ የተባለው የተሐዋሲው አይነት በበርካታ ሃገራት መገኘቱም አሳሳቢነቱን ከፍ አድርጎታል። አሁን በእጅ ላይ የሚገኘው የኮቪድ 19 ክትባትም ይኽኛውን አይነት የመቋቋም አቅሙ  እያነጋገረ ነው። በነገራችን ላይ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ትናንት ይፋ ባደረገው መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከ3 ሺህ በላይ ምርመራ ተደርጎ ኮቪድ 19 የተገኘባቸው 39 ሲሆኑ የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል። ምንም እንኳን ቁጥሩ አነስተኛ ቢመስልም ኅብረተሰቡ ሊያደርግ የሚገባውን ጥንቃቄ አጠናክሮ መቀጠል እንደገባ ከሌሎች ሃገራት ተሞክሮ ትምህርት መውሰድ ይገባል። 

Gesichtsmaske erkennt Covid-19 Infektion
ምስል Felice Frankel and MIT News Office
Symbolbild Kontrolle Covid-19 Coronavirus App Flughafen
የኮቪድ 19 ክትባት ዲጂታል ፓስፖርትምስል ROBIN UTRECHT/dpa/picture alliance
Infografik COVID-19 Delta Variante Europa EN
ኮቪድ (ዴልታ) የተዛመተባቸው ሃገራት

ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ