1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእነ መሐመድ አሚን ግድያ፤ የግንቦት 20 ሌላ ውዝግብ 

ዓርብ፣ ግንቦት 21 2012

በኦሮሚያ ተፈጽመዋል የተባሉ ግድያዎች ትኩረት እንዲሹ የሚጥሩ ዜጎች በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ግፊት እያደረጉ ነው። ግንቦት 20ም እያወዛገበ አልፏል። ትግትጉ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ብቻ አልተገታም። የፖለቲካ ልሒቃኑ በሚቆጣጠሯቸው ራዲዮና ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ስለቀኑ በሰሯቸው ዘገባዎች አሊያም ባደረጓቸው ቃለመጠይቆች የደረሱበትን ጥልቅ ክፍፍል አሳይተዋል

https://p.dw.com/p/3czeA
Äthiopien Universität Adis Ababa
ምስል picture alliance/robertharding/M. Runkel

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሰሞኑን በትዊተር እና ፌስቡክ ሲዘዋወሩ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የመሐመድ አሚን ስም፣ ፎቶዎቹ እና የማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች የእርሱ እንደሆነ የገለጹት አስከሬን ይገኝበታል። አስከሬኑ ጭንቅላቱ ከተቀረው የሰውነት ክፍሉ ተለያይቷል። በትክክል የተባለው ሰው መሆኑን ለማረጋገጥ አይቻልም። የመሐመድ አሚን አሟሟት ትኩረት እንዲያገኝ የሚሹ የፌስቡክ እና የትዊተር ተጠቃሚዎች ግን ከፎቶው ባሻገር ስለ አሟሟቱ ተጨማሪ ማብራሪያ አቅርበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጽህፈት ቤት እንዲሁም ሒውማን ራይትስ ዎች ትኩረት እንዲሰጡት ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል። 

መሐመድ አሚን ማነው?

መረራ ስልኩ የተባሉ ግለሰብ "መሐመድ አሚን ይባላል። የሶስት ልጆች አባት ነበር። ከመኖሪያ ቤቱ በጸጥታ ኃይሎች ከተወሰደ በኋላ ሞቶ በጅብ ተበልቶ ተገኝቷል" ሲሉ በትዊተር ፅፈዋል። ጀስት ቢንግ ሒውማን በሚል ስም ትዊተር የሚጠቀሙ ሌላ ኢትዮጵያዊ እንዳሉት በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ የተባለ ቦታ ይኖር የነበረው መሐመድ በጸጥታ ኃይሎች የተወሰደው "ሳይመረመር የኮሮና ቫይረስ አለብህ" በሚል ነበር። እኚሁ የትዊተር ተጠቃሚም የመሐመድ "ከፊል አስከሬን በዱር እንስሳት መበላቱን" ገልጸዋል።
ባለፉት ቀናት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በጸጥታ ኃይሎች መገደሉ በማኅበራዊ ድረ ገፆች የተገለጸው ግን መሐመድ አሚን ብቻ አይደለም።  ዋቆ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ቦና ሐብታሙ የተባለ የ15 አመት ወጣት ከሚኖርበት የምዕራብ ወለጋ ላሎ አሳቢ አካባቢ ዋንጆ በተባለ ቦታ ወደሚገኝ ወታደራዊ የጦር ካምፕ ተወስዶ ተገድሏል የሚል መልዕክት በትዊተር ፅፈዋል። ለሊሳ ተፈሪ የተባለ ወጣት በምዕራብ ወለጋ ዞን በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ሞቶ መገኘቱ ሌላ መነጋገሪያ ሆኗል።  

እንደ ጆርጅ ፍሎይድ?

አብቹ የፊንፊኔ አራዳ በሚል ስም ፌስቡክ የሚጠቀሙ ኢትዮጵያዊ በኦሮሚያ ክልል ተፈጽመዋል የተባሉ ግድያዎችን ከጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ አሟሟት አነጻጽረው ኮንነዋል። ጆርጅ ፍሎይድ የአሜሪካ ፖሊስ እጁን የፊጥኝ አስሮ ለበርካታ ደቂቃዎች አንገቱ ላይ በጉልበቱ ከቆመበት በኋላ ወደ ጣቢያ ተወስዶ ሕይወቱ ያለፈው በዚሁ ሳምንት ነበር። የ46 አመቱ ፍሎይድ አንገቱ ላይ ፖሊስ በጉልበት በቆመበት ቅፅበት "መተንፈስ አልቻልኩም" እያለ ይማጸን እንደነበር በአካባቢው የነበሩ የዐይን እማኞች የቀረጹት ቪዲዮ አሳይቷል። ነጭ ፖሊሶች በተደጋጋሚ ጥቁር አሜሪካውያንን እየተኮሱ በሚገድሉባት አሜሪካ የፍሎይድ ሞት ሌላ ተቃውሞ ቀስቅሷል። 

USA Demonstrationen wegen des Todes von George Floyd in Minnesota
የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በሚኒያፖሊስ ተቃውሞ ቀስቅሷልምስል Getty Images/S. Maturen

አብቹ የፊንፊኔ አራዳ "ሊጠብቁት እና ሊያገለግሉት ቃል የገቡ ፖሊሶችን ሕይወቱን ለማትረፍ ይለምን የነበረው ጆርጅ ፍሎይድ ታሪክ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ ኦሮሞዎች ታሪክ ነው" ሲሉ በግል የፌስቡክ ገፃቸው ጽፈዋል። "ሰዎች ወደ መንግሥት ወይም ፖሊስ ጣቢያ ይወሰዳሉ፤ ከዚያ የገቡበት ይጠፋል፣ እናቶች የልጆቻቸውን አስከሬን በጫካ እና በኦሮሚያ ጎዳናዎች ወድቆ ያገኙታል" ያሉት አብቹ የፊንፊኔ አራዳ "መሐመድ አሚን ሲራጅ የእኛ ጆርጅ ፍሎይድ ነው" የሚል መልዕክት አስፍረዋል። "ይኸ መከራ የሚቆመው መቼ ነው? እናቶቻችን ማልቀስ መቼ ያቆማሉ?" ሲሉ የጠየቁት እኚሁ የፌስቡክ ተጠቃሚ ጥቁር አሜሪካዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማልኮም ኤክስን ጠቅሰው "በየትኛውም ቦታ የሚኖር የፍትኅ መጓደል በሁሉም ቦታ ለሚኖር ፍትኅ ስጋት ነው" የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። 

በኦሮሚያ ክልል ተፈጽመዋል ለተባሉ ግድያዎች፣ እስርና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ይወነጀላል። ባለፉት ወራት በፌስቡክ እና ትዊተር ገፆቻቸው አዘውትረው መልዕክቶች የሚያስተላልፉት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጉዳዩ ላይ ያሉት ነገር የለም። ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንም ይሁን ከክልሉ መንግሥት እስካሁን ድረስ ይፋ ማብራሪያ ወይም ማስተባበያ አልቀረበም። 

ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ያላቸው ደረጄ ገረፋ ቱሉ መንግሥት "በተለያየ ሚዲያ እየቀረበበት ያለውን ክስ አጣርቶ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እና ማብራሪያ" ማቅረብ እንዳለበት  በፌስቡክ ገፃቸው በፃፉት መልዕክት አሳስበዋል።  ደረጀ "ኦሮሚያ ውስጥ በተለያየ ጊዜ፤ በተለያየ ቦታ በመንግሥት እና በታጠቂ ኃይሎች መከከል በሚደረግ ግጭት የኦሮሚያ ፖሊስ ላይ ግድያ እንደተፈፀመ በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቦ አንብበናል። በሌላ በኩልም ያለው ነገር ባይታወቅም እንዲሁ የሰው ህይዎት እያለፈ ይሆናል። ይኸ እጅግ የሚያሳዝን ተግባር ነው። በየትኛውም በኩል ይሁን የሁለት ወንድማማቾች መገዳደል በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተቀባይነት ያሌለው እና ልብ የሚሰብር ተግባር ነው። ይህ የወንድማማቾች መገዳደል እንዲቆም ሁሉም ወገን ተገቢውን መነሳሳት በመፍጠር የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት" ብለዋል። "በተለይ በማረሚያ ቤት በመንግሥት ቁጥጥር ስር ላሉ ዜጎች ተገቢውን ጥበቃ ማድርግ መንግስት የመሆን ትንሹ መስፈርት መሆኑን መርሳት ዋጋው ከባድ ነው" ሲሉ ደረጀ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ሌላ ግድያ- ሐይማኖት በዳዳ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሚገኝ ላብራቶሪ ሐይማኖት በዳዳ የተባለች ተማሪ ባለፈው ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ተገድላ መገኘቷን ፖሊስ ገልጿል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በፌስቡክ ገፁ ያሰራጨው መረጃ እንደሚለው የጤና ኮሌጅ የ2ኛ አመት ተማሪ የነበረችው ሐይማኖት "በኮሌጁ  አስተዳደር ህንፃ ላይ በሚገኘው ቤተ ሙከራ ክፍል ለምርምር በገባችበት" ተገድላለች።  ፖሊስ "የተለያየ የሰውነት ክፍሏ በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተወግቶ ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም.  ከቀኑ 11 ሰዓት አስከሬኗ በክፍሉ ውስጥ ተገኝቷል" ሲል የተፈጸመውን ድርጊት አብራርቷል። ተማሪዋን በመግደል የተጠረጠረው ግለሰብ ወንጀሉን ፈፅሞበታል ከተባለው በደም የተለወሰ ስለት ጋር መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ በፌስቡክ ገፁ ያሰራጨው መረጃ ይጠቁማል። ከስለቱ በተጨማሪ የእጅ ስልክ፣ ላፕቶፕ እና ሌሎች ማስረጃ ያላቸውን እቃዎችን ፖሊስ በፌስቡክ ለዕይታ አብቅቷል። 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ሐይማኖት "በድንገት ሕይወቷ ማለፉን የሰማነው በከፍተኛ ሀዘን ነው" የሚል መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ከማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። ፕሬዝዳንቱ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት በዩኒቨርሲቲው የፌስቡክ ገጽ ነበር። ሹንፋ ሹፍ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "የተማሪዎቹን ደህንነት ማረጋገጥ ያልቻለ ዩኒቨርሲቲም፤ መንግስትም ዋጋ ቢስ ናቸው" ሲሉ ቁጣቸውንም ገልጸዋል። 

"ዩኒቨርሲቲው የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎች በሁሉም ግቢዎች መትከል አለበት" ሲሉ ጥቆማ ጣል ያደረጉት አወቀ ደርቤ ናቸው። አክሊሉ ከበደ የተባሉ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ "የዚች ምስኪን ልጅ ደም በከንቱ ፈሶ መቅረት የለበትም። አሜሪካዊ ተሰቃይቶ ሲገደል በካሜራ ስለታየ አለም አዘነለት። የዚህችን ልጅ የግፍ ግፍ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ግን በካሜራ ስላልተቀረፀ እንደዋዛ ሊታለፍ ነው። ፍትህ ለሚስኪኗ ወጣት" የሚል መዕክት አስተላልፈዋል። "ይኸ ዩኒቨርሲቲ ስንቱን በእውቀት ካመከነ በኋላ በአካል መግደል ደግሞ ጀምሯል። የተማሪዎቻችሁን ደህንነት መጠበቅ እና ማስጠበቅ እንኳን ባትችሉ ይህን ለማለት ሳልስት ባጠብቁ" የሚሉት አልዓዛር ተረፈ የፕሬዝዳንቱ የሐዘን መግለጫ ዘግይቷል የሚል ወቀሳ ሰንዝረዋል። 

እንደገና የግንቦት 20 ውዝግብ

Logos TOLF  EPRDF
በኢሕአዴግ ልሒቃን መካከል በተፈጠረ ልዩነት ግንባሩ ከፈረሰ በኋላ ግንቦት 20ን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ መስማማት ተስኗቸዋል

ኢሕአዴግ ደርግን በትጥቅ ትግል ከሥልጣን ያስወገደበት ግንቦት 20 ለ29ኛ ጊዜ ትናንት ሐሙስ ሲከበር ኢትዮጵያውያን እንደየ ፖለቲካ አቋማቸው በየሰልፋቸው ሲተጋተጉ ታይተዋል። የቃላት መወራወር እና ውዝግቡን ለመታዘብ ማኅበራዊ ድረ-ገፆች ኹነኛ መድረክ ናቸው። 

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ግንቦት ሃያ የዘመናዊት ኢትዮጵያን ታሪክ ከቀየሩ ዕለታት መካከል አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ለማድረግ አያሌ ታጋዮች እጅግ ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ነፍስ ሠውተዋል፡፡ የግንቦት ሃያ ታጋዮች የነፍስ ዋጋ የከፈሉለት ዓላማ ግፍና ጭቆና፣ አድሎና ወገንተኝነት ቆሞ፤ እኩልነት ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ነው" ሲሉ ከትናንት በስቲያ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈው ነበር። 

እውነቱ እውነቱ የሚል የፌስቡክ ስም የሚጠቀሙ አንድ ግለሰብ ግን "ሕዝብ ውስጥ ያለው ስሜት ይህ አይደለም። ክቡር የሆነ የታጋዮች አላማ እና የታየው ፍሬ ማን እንዳበላሸው በመግለፅ አዲስ ምዕራፍ ማሳየት ይገባ ነበር" ሲሉ ለጠቅላይ ምኒስትሩ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። "ኢሕአዴግ የደርግን ስርዓት ደጋግሞ አውግዟል። አሁንም ከድለላና ማስመሠል መውጣት" ያስፈልጋል ያሉት እውነቱ ተፈጽመዋል ያሏቸው ጭፍጨፋዎች ማውገዝ "አዲሱን የብልፅግና ተስፋ በሀቅ ማሳየት ይገባል። አሮጌ እርሾ መደፋት አለበት። አካፋን አካፋ ማለት ይገባል" የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። 

ግርማይ ይኸደጎ "ግንቦት 20 ኢትዮጵያ በ800 የነፍጥና የነገስታት ዓመታት አይታው የማታውቀው ለውጥና ዕድገት በ27 ዓመታት እንዲመጣ አድርጋለች። የ2012 ግንቦት 20 በዓይነትም በይዘትም ከ83ቱ ግንቦት 20 በላቀ ከፍታ ላይ መገኘትዋም ለቀባሪ ማርዳት ነው የሚሆነው። ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝቦች አለኝታ ስትሆን ለግዛት አንድነት ኃይሎች የእግር እሳት ናት። ለማንኛውም ግንቦት 20 ድምቀትዋ ከፊታችን ነው" የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። 

ሐዊና ታሜ ግን "ግንቦት 20 ኢትዮጵያን ከብሔረሰቦች እስርቤትነት ወደ ብሔረሰቦች ቄራነት የቀየረ ጥቁር የሃዘን ቀን ነው። ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያንም ብሔራዊ የሃዘንና የውርደት ቀን ነው" ሲሉ መረር ያለ አስተያየት በጠቅላይ ምኒስትሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሥር አስፍረዋል። 

ኢክራም ኑርሑሴን "በተወሰኑ ራስ ወዳድ አመራሮች ምክንያት ቀኑን ማጥላላት ተገቢ አይደለም። ስለ ሀገራቸው ክብር ብለው የወደቁትን ሁሉ ደም ከንቱ ማስቀረት ነው ሚሆነው። ይህንን ቀን ለሀገራቸው ነፍሳቸውን የሰዉትን ታጋዮቻችንን አርበኞቻችንን ብንዘክርበት መልካም ነው። ዘላለማዊ ክብር ለሰማዕታቶቻችን" የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። 

ትግትጉ ግን በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ብቻ አልተገታም። የፖለቲካ ልሒቃኑ በሚቆጣጠሯቸው ራዲዮ እና ቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንዲሁም ጋዜጦች ስለ ቀኑ በሰሯቸው ዘገባዎች፤ ባደረጓቸው ቃለ መጠይቆች እንዲሁም በጻፏቸው ሐተታዎች የደረሱበትን ጥልቅ ክፍፍል አሳይተዋል። 

እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ