1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስራኤል ምርጫና ኔታንያሁ አጣብቂኝ

ሐሙስ፣ መስከረም 8 2012

በእስራኤል ጠቅላላ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ አጣብቂኝ ዉስጥ የገቡት ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጥምር መንግሥት እንመስርት ሲሉ ጥሪ አቀረቡ። የሊኩድ ፓርቲ መሪዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ ተቃናቃኛቸዉ ሰማያዊና ነጭ ፓርቲ ሊቀመንበር ጋር በጋራ ጥምር መንግሥትን እንመስርት ሲሉ ጥሪ አቅርበዉላቸዋል።

https://p.dw.com/p/3PuJz
Benjamin Netanjahu, Reuven Rivlin und Benny Gantz
ምስል Reuters/R. Zvulun

በእስራኤል ጠቅላላ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ አጣብቂኝ ዉስጥ የገቡት ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጥምር መንግሥት እንመስርት ሲሉ ጥሪ አቀረቡ። የሊኩድ ፓርቲ መሪዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ ተቃናቃኛቸዉ ሰማያዊና ነጭ ፓርቲ ሊቀመንበር  ቤኒ ጋንትዝን ከሊኩድ ከቀኝ ዘመም እና የሃይማኖት ፓርቲዎች ጋር በጋራ ጥምር መንግሥትን እንመስርት ሲሉ ጥሪ አቅርበዉላቸዋል። እንድያም ሆኖ ይህን ጥምረት ማን እንደሚመራዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የጠቀሱት ነገር የለም። እስራኤልን ለ 10 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈዉ ማክሰኞ በእስራኤል በተካሄደዉ ጠቅላላ ምርጫ ቀኝ ፓርቲያቸዉ ሊኩድ  በተቀናቃኛቸው ሰማያዊና ነጭ ፓርቲ 33 ለ 31 ተበልጦአል። እንድያም ሆኖ የቀኝ ክንፍም ሆነ የማሃል ግራዉ ፓርቲዎች ከእስራኤል ፓርላማ 120 መቀመጫ መንግሥትን ለመመስረት የሚያስችላቸዉን ከ 61 በላይ መቀመጫን አላገኙም። ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ ሠፊ ተጣማሪ መንግሥት እንመስርት  ሲሉ ለተቀናቃኛቸዉ እንዲህ ነዉ ጥሪ ያስተላለፉት። 

«መራጮች ከሁለት ፓርቲዎች መካከል አንዱን አለመወሰናቸዉን የምርጫ ዉጤቱ ያመለክታል። ስለዚህ ሠፊ ተጣማሪ መንግሥት ከመመስረት ሌላ አማራጭ የለም። ትናንት ከቀኝ ክንፍ ፓርቲ ጓደኞቼ ጋር ተገናኝተን ባደረግነዉ ዉይይት በድርድር እንደ አንድ ቡድን ለመቅረብ ተስማምተናል። አሁን ለክኔሴት አባል ቤኒ ጋንትዝ ጥሪ አቀርባለሁ።  ቤኒ  ፣ ዛሬ የአንድነት መንግሥት መመስረት የእኛ ፋንታ ነው ፡፡ ህዝቡ ከሁለታችንም ወገን አብሮ የመስራት ኃላፊነትን ይጠብቃል። እናም ቤኒ ዛሬ በማንኛዉም ሰዓት ተገናኝተን ጉዳዩን ነገሩን ወደፊት እናራምድ» 

ሰማያዊና ነጭ ፓርቲ  በበኩሉ የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር የቤንያሚን ኔታንያሁን ጥሪ ዉድቅ አድርጎአል። የፓርቲዉ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መልስ ናታንያሁ በሚመሩት ጥምር መንግሥት ማንም መሳተፍ አይፈልግም ብለዋል። የኔታንያሁ ተቀናቃኝ የሰማያዊና ነጭ ፓርቲ ሊቀመንበር፤ ጡረተኛዉ  የእስራኤል መከላከያ ኤታማዦር ሹም የቀድሞ ጄኔራል ቤኒ ጋንትዝ  በበኩላቸዉ እኔ ራሴ ለዘብተኛ ጥምር መንግሥት ማቋቋም እፈልጋለሁ ሲሉ ነዉ መልስ የሰጡት። እስራኤል ባካሄደችዉ ጠቅላላ ምርጫ ስልጣን መንበራቸዉ የተነቃነቀዉ  የ69 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን  ኔታንያሁ በሙስና ስማቸዉ ሲብጠለጠል መቆየቱ የሚታወስ ነዉ።

 

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ