1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ቦርድ ምላሽ

ሐሙስ፣ መጋቢት 9 2013

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እግድ ተጥሎበታል የተባለው የምክር ቤቱ የሥራ አመራር ቦርድ በጠቅላይ ምክር ቤቱ የተላለፈ ውሳኔው ሕገ ወጥ ነው አለ። ቦርዱ አሁንም በሥራ ላይ እንደሚገኝ እና የተጠራው ጠቅላላ ጉባዔም ሕግን የተከተለ ነው ሲል ጠቅላይ ምክር ቤቱ ትናንት ላወጣው መግለጫ ምላሽ ሰጥቷል።

https://p.dw.com/p/3qo3u
Äthiopien EIASC Gericht für islamische Angelegenheiten
ምስል EIASC

በኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የተፈጠረው ውዝግብ

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እግድ ተጥሎበታል የተባለው የምክር ቤቱ የሥራ አመራር ቦርድ በጠቅላይ ምክር ቤቱ የተላለፈ ውሳኔው ሕገ ወጥ ነው አለ። ቦርዱ አሁንም በሥራ ላይ እንደሚገኝ እና የተጠራው ጠቅላላ ጉባዔም ሕግን የተከተለ ነው ሲል ጠቅላይ ምክር ቤቱ ትናንት ላወጣው መግለጫ ምላሽ ሰጥቷል።
ሚያዝያ 23 ቀን 2011 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል የተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተቋማዊ ለውጥ እንዲከናወን 26 ዑለማዎች እና 7 የቦርድ አባላት በድምሩ 33 የጠቅላላ ጉባዔ አባላት በሙስሊሙ ማሕበረሰብ ተመርጠው ተቋሙ በአዋጅ እንዲፀድቅ፣ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲከናወንና የዑለማ የአንድነት ሰነድ ፀድቆ በሙስሊሙ መካከል የሚታዩ ልዩነቶችን በማጥበብ አንድነትንና በጋራ መሆንን ለማምጣት አልሞ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን የተናገሩት በጠቅላይ ምክር ቤቱ "ታግዷል " የተባለው "ቦርድ" ዋና ፀሐፊ ሐጂ ከማል ሀሩን አሁን እየተስተዋለ ያለው ችግር በጥቂት አመራሮች መካከል ያለ ነው ብለዋል።
ቦርዱን አግልሎ የመሄድ ፍላጎት መኖሩን የተናገሩት ሐጂ ከማል እግድ የሚለው ውሳኔ ከምክር ቤቱ የመተዳደሪያ ድንብ እና ከሽግግር ጊዜ መጅሊሱ አሠራር ውጪ ነው ብለዋል።
ቦርዱ አሁንም በሥራ ላይ እንደሚገኝና ከ33 ቱ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት መካከል ሁለት ሦስተኛዎቹ አብላጫዎቹ በመጭው ቅዳሜ እና እሁድ የተጠራውን ጉባዔው መካሄድ ይሁንታ የሰጡት በመሆኑ ሥራውን ማከናወናችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
የተቋሙ የበላይ አካል ጠቅላላ ጉባዔ መሆኑን በመጥቀስ በዑለማውም ይሁን በሥራ አመራር ቦርዱ ላይ እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን የጠቅላላ ጉባዔው ነው ያሉት ሐጂ ከማል አሁን እየታየ ያለው ከዚህ ውጪ የሆነ እና ተቋሙ ተቋም ሆኖ እንዳይቀጥል የመፈለግ አዝማሚያ ነው ብለዋል።
የተቋሙ ማኅተም አሁንም በእኛ እጅ ላይ ይገኛል ፣ ምክንያቱም በሥራ ላይ ስለሆንን ያሉት ሐጂ ከማል ሀሩን ሕገ ወጥ ሁለተኛ ማኅተም አስቀርፆ እየሰራ ያለው የዑለማው ምክር ቤት ነው ይላሉ።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ እንደሚለው ደግሞ ቦርዱ በተለይ ከተሰጡት ተልዕኮዎች ውጪ የጠቅላይ ምክር ቤቱን ሥራ ይዞ በተቋሙ የሐጂ እና ዑምራ እንቅስቃሴ ላይ በመግባቱ እና ስህተቶችን በመሥራት ተገምግሞ ከወራት በፊት በዑለማዎች ምክር ቤት የሥራ እግድ ተጥሎበታል።
ጠቅላላ ጉባዔው ራሱ ተሰብስቦ ቦርዱ የታገደበትን ምክንያት መርምሮ አንድ ውሳኔ እስከሚያሳልፍ ድረስ የቦርዱ አባላት ራሳቸውን እንደ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት መቁጠር የለባቸውም። ምክንያቱም ስለታገዱ በማለት የጠቅላይ ምክር ቤቱ እና የዑለማ ምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ሸህ ቃሲም መሐመድ ታጁዲን ተናግረዋል።
ጠቅላላ ጉባዔ መደረጉ አስፈላጊ ቢሆንም አንድም በተገቢው ሕጋዊ አካል መጠራት አለበት ፣ በሌላም በኩል ሌሎች አስተዳደራዊ ተግባራት ቅድሚያ መከናወን አለባቸው ብሏል ትናንት በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የወጣው መግለጫ።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ