1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእርዳታ ሠራተኞች ኬላ መተላለፋቸው እና ሌሎችም

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 2 2013

የድርጅቱ ሰራተኞች የኢትዮጵያ መንግስት «የተከለከለ» ባለው አካባቢ ተላልፈው በመገኘታቸው በኃይል በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል። ሂደቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል ቅሬታን ሲያጭር የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ሰራተኞቹ ወደ ተከለከሉ አካባቢዎች እንዳይገቡ የተከለከሉት ለራሳቸውም ደህንነት ጭምር ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/3mZqY
Symbolbild Apps Facebook, Google und Google + Anwendungen
ምስል Imago Images/P. Szyza

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ጤና ይስጥልን አድማጮች ወቅታዊ እና በብዙዎች ዘንድ ትኩረትን ባገኙ እንዲሁም በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከሁለት ወገን አስተያየት የተሰጠባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች የምንቃኝበት ሳምንታዊው የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችን እነሆ ጀምሯል። ከዝግጅቱ ጋር ታምራት ዲንሳ ነኝ አብራችሁን ቆዩ።
የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል «ሕግ የማስከበር» ዘመቻ ባለው እና የሕወሓት ታጣቂዎች በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ እየተካሄደ ያለው ውግያ አሁንም ድረስ አለመቋጨቱ እየተነገረ ነው። የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት የሕወሃት ከፍተኛ የፖለቲካ እና የጦር መሪዎችን ማሳደዳቸውን እንደቀጠሉ ቢሆንም መንግስት ቀደም ሲል ተፈላጊ ናቸው ብሎ የስም ዝርዝራቸውን ካወጣባቸው በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው  ከመነገሩ ባለፈ የተቀሩት እስካሁን ያሉበት ሁኔታ በግልጽ አይታወቅም። ቀደም ሲል ከሰሜን ዕዝ በሕወሓት ታጣቂዎች ታግተው ተወስደው የነበሩ ከ1000 በላይ የዕዙ የመካከለኛ እና መስመራዊ የሚባሉ መኮንኖች ከእገታ መለቀቃቸው የኢትዮጵያ መንግስት የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ውግያው ረገብ ባለበት በዚህ ጊዜ በትግራይ የሰብአዊ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር እጅጉን በማየሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ በክልሉ ለማድረስ የሚያስችለውን ስምምነት ባሳለፍነው ሳምንት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተፈራርሞ ነበር ። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ የድርጅቱ ሰራተኞች የኢትዮጵያ መንግስት «የተከለከለ» ባለው አካባቢ ተላልፈው በመገኘታቸው በኃይል በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል። ሂደቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል ቅሬታን ሲያጭር የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ሰራተኞቹ ወደ ተከለከሉ አካባቢዎች እንዳይገቡ የተከለከሉት ለራሳቸውም ደህንነት ጭምር ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን በብሔራዊ የመረጃ ማጥሪያ በኩል አስታውቋል። አያይዞም በትግራይ የሚከናወን የሰብአዊ እርዳታ የማድረሱ ስራ በመንግስት አስተባባሪነት መሆኑን ግልጽ አድርጓል። ጉዳዩን በተመለከተ በርካቶች በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሃሳባቸውን አጋርተውበታል።
ጸጋዬ ጀምበር እንግዳው የተባሉ አስተያየት ሰጭ « ይህቺኮ የመን፣ሊቢያ ወይም ሶርያ ኣ,ይደለችም ። ይህቺ ኢትዮጵያ ናት ። አያውቁንም ኮርያ ዘማቾችን » የሚል አስተያየት አስፍረዋል። ሰለሞን ሆሲ ሆሲ በሚል መጠርያ ሃሳባቸውን እንዲህ ሲሉ አጋርተዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዚህ የባሰ ችግር ያለባቸው ሃገራት እያሉ ለምን እዚህ ጩኸት አበዛ ሲሉ ይጠይቃሉ ። ወንጀለኞችን ሽፋን ሰጥቶ ለማስወጣት የተቀናጀ ሴራ ለመስራት ነው ።» በማለትም ሰራተኞቹ ወደ  ተከለከለ ስፍራ መግባታቸውን የሚቃወም አስተያየት አስፍረዋል። ቻን ማን በሚል መጠርያ አስተያየታቸውን ያሰፈሩ ሰዉ በበኩላቸው «ሶስተኛው ኬላ ላይ ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የኤርትራን ስደተኞች በግድ እየመለሳቸው መሆኑን አለም እንዳያውቅ ያደረጋችሁት ጥረት የሚደነቅ ነው ሲሉ» የመንግስትን እርምጃ የነቀፉበትን ሀሳብ አስፍረዋል። ደበበ በቀለ ደግሞ «እነርሱ የገቡበት ሁሉ ረብሻው ይባባሳል፤ የአፍሪካ ችግር ሁሉ የእነርሱ እጅ አለበት » ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የተቹበትን ሃሳብ አስፍረዋል። ሙህዲን ከማል ደግሞ ትግራይ ስድስት ሚሊዮን ይዛ ከኢትዮፕያ 10 ክልሎች አንዷ በሆነችበት የተቀረው ዓለም ጉዳዩን ለምን ለማራገብ እንደፈለገ አይገባኝም ። ይህ ከምን የመነጨ እንደሆነ እረዳለሁ «አንዳንድ» በአለማቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች የሚፈጥሩት ተጽዕኖ እንደሆነም ነው የሚገባኝ» የሚል ሀሳብ አስፍረዋል።
 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትግራይ የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ የሚችለው በመንግስት አስተባባሪነት መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን « ኢትዮጵያ ኃላፊነቱን የሚወጣ መንግሥት ያላት ሀገር በመሆኗ ሞግዚት አያስፈልጋትም» ብለው ነበር። በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት በበኩሉ «የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ የሚተጉ ሰራተኞች ከጥቃት ስጋት ነጻ ሆነው የሕይወት አድን ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ማረጋገጥ አለበት » ሲል አሳስቧል። በትግራይ ሲደረግ በነበረው በዚሁ ውግያ «የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያ መንግስት ኃይሎችን ወግነው በጦርነቱ ላይ ተሳትፈዋል» የሚሉ ሃሳቦች ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲሰራጩ ታይተዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ እንዳስታወቁት የኤርትራ ወታደሮች በጦርነቱ ተሳትፈዋል መባሉ «ያልተረጋገጠ ነው» ማለታቸው ተዘግቧል።

UNTV Videostill | Konferenz: UN Generalsekretär Antonio Guterres
ምስል UNTV/AP/picture alliance
Tigray-Konflikt | Militär in Addis Abeba
ምስል Minasse W. Hailu/AA/picture alliance
Äthiopien Verteidigungstruppe Amhara
ምስል Alemnew Mekonnen/DW
Tigray-Konflikt | Flüchtlinge im Sudan
ምስል ASHRAF SHAZLY/AFP

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ከሰሞኑ ወደ ኬንያ ማቅናታቸው እና በኢትዮጵያ እና በኬንያ የድንበር ከተማ ሞያሌ በመገኘት ሁለቱን ሀገራት በማስተሳሰር ረገድ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውን የጋራ መቆጣጠርያ ኬላን እና ከሁለቱም ወገን የተገነባ መንገድ  መርቀው ከፍተዋል። ከዚያም ባሻገር ኬንያ ኢትዮጵያን እና ደቡብ  ሱዳንን በጋራ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የታቀደለትን እና በግንባታ ላይ የሚገኘውን የላሙ ወደብን ጎብኝተዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በሞያሌ የጋራ መቆጣጠርያ ኬላን ሲመርቁ እንዳሉት  በአካባቢው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱትን የአልሸባብ እና የኦነግ ታጣቂዎችን ከአካባቢው ለማጥፋት የኬንያን ትብብር ጠይቀዋል። ኢትዮጵያ እና ኬንያን ያስተሳስራሉ የተባሉት እነዚሁ ግንባታዎች በእርግጥ ማን ያህል ውጤታማ ናቸው ሲሉ በርካቶች ይጠይቃሉ። ይህንኑ በተመለተም  በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ በርካታ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል።
አቡበከር አቡኪ ባሰፈሩት አስተያየት «ይህ ግሩም ስራ ነው ። አዲስ ዘመን ለመምጣቱም ማሳያ ነው። ወሳኝነቱም አብሮ ለመበልጸግ ብቻ አይደለም ። ነገር ግን የጋራ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እና መደመርን በአካባቢው ሀገራት ተግባራዊ በማድረግ ድህነትን አሽቀንጥሮ ለመጣል ሁነኛ ነው።» ብለዋል። ማሞ ታሪኩ በበኩላቸው « ስራዎች ተጠናቀው ሳያልቁ ማስመረቅ ተገቢ አይደለም። በዚህ ላይ ያለቁትም ጥራታቸውን የጠበቁ አይደሉም። ውሸት ጥሩ አይደለም። »ሲሉ ሌላው አስተያየት ሰጭ አዲሱ ኪጴ «በኢትዮጵያ ወገን ያለው መንገዱ መመረቁ ጥሩ ቢሆንም በተለይ በጌዴኦ ዞን ከፍተኛ የጥራት ጉድለት እና ይርጋ ጨፌ አካባቢ ገና ስራ ላይ ያለ በመሆኑ ለከፍተኛ አመራር የሚሰጥ መረጃ ተአማኒ መሆን አለበት » በማለት የመንገድ ግንባታው በኢትዮጵያ ወገን የጥራት ችግር እንደነበረበት የገለጹበትን ሐሰብ አካፍለዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በተለይ በአካባቢው የታጣቂዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ሀገራቱ በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ደረጀ ተስፋዬ ባሰፈሩት አጭር መልዕክት « ልማቱን እየሰሩ ሕግ የማስከበር ስራውን ጎን ለጎን ማከናወን ተገቢ ነው ።» አካባቢው ኢትዮጵያ ኬንያ እና ሶማሊያ ለሚዋሰኑባቸው የድንበር አካባቢዎች ቅርበት ያለው በመሆኑ ለታጣቂዎች እንቅስቃሴ ምቹ እንደሆነ ይነገራል። ይህንኑ አስመልክቶ በድሩ ከማል ባጋሩት ሀሳባቸው አልሸባብንም ሆነ ኦነግ ሸኔን ለመዋጋት ከመንግስታት በላይ የህዝቡ ሚና የጎላ መሆን አለበት። የታጣቂዎችን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ሕዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል። ምክንያቱም ታጣቂዎቹ ራሳቸው ከሌላ ቦታ የመጡ ስላልሆነ ። በመሆኑም ታጣቂዎችን ከአካባቢው ለማስወገድ ከመንግስት ወታደሮች በላይ ሕዝቡ እርምጃ ቢወስድ ለመንግስት ይቀል ነበር » በማለት ታጣቂዎችን ለመከላከል ያስችላል ያሉበትን ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

Äthiopien Oromo-Befreiungsfront (OLF)
ምስል DW/N. Desalegn
Bildcombo I Abiy Ahmed und  Uhuru Kenyatta

ሽግግር 
ብሪታንያ የኮሮና ክትባት ለዜጎቿ በይፋ መስጠት መጀመሯ በአንድ በኩል ዓለም ከወረርሽኙ የምትድነበት ጊዜ ቀርቧል የሚሉ የተስፋ ሀሳቦች ሲንጸባረቁ በሌላ በኩል በወረርሽኙ አሁንም አሁንም በርካቶች እየተጠቁ እና በየዕለቱ ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መሄዱ አሁንም አስፈሪነቱ እንደቀጠለ ነው። በእንደ ኢትዮጵያ ባሉ ወረርሽኙን ለመግታት በሚደረግ ጥረት መሰላቸት እና ግዴየለሽነት በሚታይባቸው ሀገራት ችግሩን የከፋ እንዳያደርገው ተሰግቷል። የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በተህዋሲው ተይዘው እና በጠና ታመው ወደ ጤና ተቋማት እየገቡ ያሉ ታማሚዎች ቁጥር እጅጉን እያሻቀበ ነው። ቁጥሩ ከፍተኛ ጭማሪ  ከማሳየቱ ባሻገር የጤና ተቋማት ጽኑ ሕሙማንን የመቀበል አቅማቸው መሟጠጡን ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጓል። የክትባቱ መገኘት እና የበሽታው አሁንም ስጋት ሆኖ መቀጠል ሰሞኑን አስተያየት ከተሰጠባቸው ጉዳይ አንደኛው ነው። የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ የወረርሽኙን አሳሳቢነት ያስተላለፉትን መልዕክት ተከትሎ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የታዩ አስተያየቶች በኢትዮጵያ ተሕዋሲውን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት ምን ያህል እንደተገታ ማሳያ ሆኗል። ሜናል አብዱ « እሱ ነገር አሁንም አለ እንዴ ?»ሲሉ ይጠይቃሉ። አብረሃም ዱሬሳ ደግሞ «ዶክተርዬ ሕዝቡኮ የኮሮና ሁኔታ ተመችቶታል» የሚል አስተያየት አስፍረዋል። ኑቲ ዘካርያስ በሚል መጠርያ የሰፈረ አስተያየት ደግሞ ኮሮና ቫይረስ ምን ነበር?» የሚል ምጸት አዘል ጥያቄ ያቀርባሉ። በእርግጥ ወረርሽኙ ገዳይ መሆኑን አጥተው አይመስለንም ። ነገር ግን ምን ያህል ቸልተንነት እየታየ እንደሆነእና  ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አሁንም የወረርሽኙ ስርጭት የሚሰጋቸው ወገኖች እንዳሉ መረዳትም ተገቢ ነው። ባገኙት አጋጣሚ የጥንቃቄ መልዕክቶቻቸውን  ሲያስተላልፉ ይታያል። አንዳርጌ በላይ « ማህበረሰቡ ጠንቃቄውን ትቶታል ። ማስክ ሳያደርጉ በመኪና ሳይቀር መንቀሳቀስ ተጀምሯል ። መሳሳም ፣ መጨባበጥም ተጀምሯል ። ይህ በሽታ እናት አይምሬ መሆኑ ይታወቃል ። እባከችሁ እንተዛዘን ፣ ላዛውንቶች ፣ ተደራራቢ በሽታ ላለባቸው ወገኖቻችን እንዘንላቸው ። ያንዱ መታመም የሌላው መታመም ስለሆነ ።» ሲሉ ተመስገን ኮራም እንዲሁ በተመሳሳይ « መንግስት በሽታውን ለመከላከል የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች አስፈላጊ ናቸው» ይላሉ።«  ነገር ግን ህዝቡም ሆነ መንግስት በጉዳዩ ዙርያ ቸል ብለዋል። ይህን ስልም በየቦታው ትምህርት ቤቶች መከፈት፣ የትራንስፖርት ወደ ቀድሞ ቦታ መመለስ እና በተለያዩ አከባቢ የተፈጠሩ ግጭቶች ጉዳዩን አሳሳብ አድርጎታል። ስለዚህ ወቅታዊ ሁኔታዎች ቶሎ ተገምግም ቀጣይ የመፍተሔ አቅጣጫ ቢቀመጥ ጥሩ ነዉ የሚል እምነት አለኝ። ህዝባችንን ከዚህ ክፉ በሽታ ፈጣሪ ይጠብቅ!» በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል። እኛም ለዛሬ ያልነውን በዚሁ እናብቃ ሳምንት በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እንደምንገናን ተስፋ እያደረግን እንሰነባበት። ከዝግጅቱ ጋር ታምራት ዲንሳ ነኝ ጤና ይስጥልልኝ። 
ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ
 

Äthiopien Coronavirus Ausbreitung
ምስል Solomon Muchie/DW
Äthiopien | Corona Isolations-Zentrum im Campus der Hawassa Universität
ምስል Privat