1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእምዬ ምኒልክ ወዳጆች

እሑድ፣ ነሐሴ 19 2011

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱ ልደትቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦአል፤ ተከብሮአል። «የእምዬ ምኒልክ ወዳጆች ማህበር» በመባል የሚታወቀዉ  በአብዛኛዉ ወጣቶችን ያካተተዉ ቡድን በበኩሉ፤ በእምዬ ምኒልክ የትውልድ ቦታ ዝግጅት አካሂድዋል።

https://p.dw.com/p/3OSLd
Addis Abeba Geburtstagsfeier von Kaiserin Taitu und Kaiser Menelik
ምስል DW/S. Mushie

የዳግማዊ አጼ ምኒልክን እና የእቴጌ ጣይቱ የትዉልድ ቀን መታሰብያ

«የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ማዕከላዊ መንግሥታቸዉን ከመሰረቱ በኋላ ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት ብለዉ የኢትዮጵያን ሕዝብ በአራቱም ማዕዘናት በማነቃነቅ ሃገራችንን ለመዉረር የመጣዉን የጣልያን ወራሪ ድል በማድረግ ለጥቁር አፍሪቃዉያን የነፃነት ድል ችቦ አብርተዋል። በአዉደ ዉግያዉ ላይ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱት መካከል ንግስተ ጣይቱ እና ፊታዉራሪ ገበየሁ፤ ከዋና ዋናዎቹ የጦር መሪዎች መካከል ግንባር ቀደሞቹ ነበሩ። በጦርነቱ ፊታዉራሪ ገበየሁ ስሸሽ ጥይት በጀርባዬ ከመታኝ፤ እንዳትቀብሩኝ በግንባሪ ከመታኝ ግን፤ ሪሳዬን በትዉልድ ቦታዬ እንድታሳርፉት ሲሉ ተናግረዉ ስለነበር፤ የፊት አዉራሪ ገበየሁ አፅም ፤ በእምዬ ምኒልክ ትዕዛዝ ከሰባት ዓመታት በኋላ በአንጎለላ ኪዳነምህረት እንዲያርፍ ተደርጎአል።»

Addis Abeba Geburtstagsfeier von Kaiserin Taitu und Kaiser Menelik
ምስል DW/S. Mushie

የዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱን የልደት ቀን አስመልክቶ በደብረብርሃን በእምዬ ምኒልክ የትውልድ ቦታ አንጎለላ በተካሄደዉ ልዩ ዝግጅት ላይ ንግግር ያደረጉትና ለዚህ ዝግጅት መሳካት ከፍተኛ ስራን መስራታቸዉ የተነገረላቸዉ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ የተናገሩት ነዉ። በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱ ልደትቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦአል፤ ተከብሮአል። የዳግማዊ አጼ ምኒልክ 175ኛ እና የእቴጌ ጣይቱ  179ኛ የትዉልድ ቀንን አስመልክቶ ከተካሄደዉ ዝግጅት መካከል አንዱ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ፤ ደራስያን ገጣምያን እና እንዲሁም የታሪክ ባለሞያዎች ነገስታቱን በየሞያቸዉ ያወደሱበት ታሪካቸዉን የዘከሩበት ነበር። «የእምዬ ምኒልክ ወዳጆች ማህበር» በመባል የሚታወቀዉ  በአብዛኛዉ ወጣቶችን ያካተተዉ ቡድን በበኩሉ፤ በእምዬ ምኒልክ የትውልድ ቦታ ዝግጅት አድርገዋል። የነገስታቱን ገድል ለማስታወስ የእግር ጉዞን ጨምሮ የደም ልገሳ ሁሉ አካሂደዋል። በዝግጅቱ ላይ የታደመዉ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም፤ የዳግማዊ አጼ ምኒልክን ልደት በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች አስቦ ይዉላል። ዘንድሮም በንጉሱ የትዉልድ ስፍራ አንጎለላ ኪዳነምህረት ተገኝቶ ነበር። 

Addis Abeba Geburtstagsfeier von Kaiserin Taitu und Kaiser Menelik
ምስል DW/S. Mushie

« ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት፤ አስር አስራ አምስት እየሆንን ነበር ወደ አንጎለላ የምንሄደዉ። ቦታዉ ላይ አበባ አስቀምጠን፤ ማስታወሻ እንዲሆን የየራሳችንን፤ ማስታወሻ ብለን የያዝነዉን ተናበን፤ ገጣምያንም አንረዉን ይሄዳሉ፤ ስለሳቸዉ ገድል አንስተን፤ በአሉን አክብረን እንመለስ ነበር። የዘንድሮዉ አከባበር ለየት የሚያደርገዉ ነገር፤ አንደኛ እዝያዉ አቅራብያዉ ላይ የሚገኘዉ  የደብረ ብርሃን ዩንቨርስቲ ጉዳዩ ያገባኛል ብሎ በአከባበሩ ዝግጅት ላይ ገባበት። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሰሜን ሸዋ አስተዳደር፤ በተለየ ሁኔታ ይሄን በዓል መደገፍ ብቻ ሳይሆን፤ አክባሪ ነኝ ይመለከተኛል ብሎ በኃላፊነት ያዘዉ። ሌላዉ ደግሞ በዋናነት አዲስ ትዉልድ « የዳግማዊ ምኒልክ ወዳጆች » በሚል በማኅበር መልኩ የተደራጁ ናቸዉ። አዲስ አበባ ዉስጥ ፤ የአድዋ ድልም ሲከበር፤ የድል ቀንም ሆነ ሌሎች በአላት ሲከበሩ፤ እነዚህ ወጣቶች በተለየ ሆኔታ ሃገራዊ አልባሳትን አድርገዉ፤ የእናት አባቶቻችን ዘመን የሚያስታዉስ ቱፊት የሚያስታዉስ ነገር ያደርጋሉ። ወጣቶቹ በጣም የተደራጁ ናቸዉ። የዘንድሮዉን በዓል ልዩ ያደረገዉ እነሱ በስፋት ተሳትፈዉበታል። ከዚህ ባሻጋር ኣካባቢዉ ላይ «ማኅበረ ሸዋ» የሚባሉ ወጣት ማኅበር ይገኛል፤ ይህ ማኅበር የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ይሰራሉ፤ ይህ ማህበር አንዱ የበዓሉ አድማቂ ነበር። በበዓሉ ላይ በብዙ ሽህ የሚቆጠር ተሳታፊ ተገኝቶአል። አካባቢዉ ላይ የሚኖሩ የኦሮሞ ፈረሰኞች የፈረስ ትርኢትን በማድረግ ፤ ዳግማዊ አጼ ምኒልክን የሚያወድስ፤ የሚዘክር  አባት አርበኞችን የሚያወድስ ፉከራ እና ቀረርቶ በማሰማት ለበዓሉ ድምቀት ሰጥተዉታል። ዝግጅቱ በእምቢልታ፤ በነጋሪት የታጀበ ነበር።»           

በየዓመቱ እንግዲህ ስለ አንድነታችን፤ አብረን ስለመሆናችን፤ ሃገር ስለመስራታችን፤ የበለጠ ቃል የምንገባበት በዓል እንደሆን አይቻለሁ ሲል ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ተናግሮአል። የእምዬ ምኒልክ ወዳጆች ማህበር አባል እና ከአዛጋጆቹ መካከል አንዱ የሆነዉ ያሬድ ኃይሉ እንደነገረን አንጎለላ ላይ የከነገስታቱ የልደት በዓል ዝግጅት በተጨማሪ ፤ አጼ ምኒልክ የጦር ምኒስትር የነበሩት የፊታዉራሪ ገበየሁም የትዉልድ ቀንም ታስቦ ዉሎአል።  መከበሩን ነግሮናል።

Addis Abeba Geburtstagsfeier von Kaiserin Taitu und Kaiser Menelik
ምስል DW/S. Mushie

 «ዘንድሮ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ 175ኛ ፤  የእቴጌ ጣይቱ  179ኛ የትዉልድ ቀንን በማስመልከት ነበር የተከበረዉ ። ሁለቱም ነገስታቶች የተወለዱበት ዓመት ቢለያየም ፤ ቀኑ ግን አንድ ቀን ነዉ። ሁለቱም የተወለዱት ነሐሴ 12 ቀን ነዉ። ከነሱ በተመሳሳይ ቀን የአጼ ምኒልክ የጦር ምንስቴር የነበሩት ፊታዉራሪ ገበየሁም ተወልደዋል ተብሎ ይታመናል። ዝግጅቱ የሦስቱም ጀግኖች ኢትዮጵያዉያን መታሰብያ ነበር። አጼ ምኒልክ የተወለዱበት ቦታ ደብረ ብርኃን አንጎለላ እንቁላል ኮሶ ይባላል። ይህ ቦታ የሚገኘዉ ከደብረብርሃን ወደ ጅሩ በሚወስደዉ መንገድ አምስት ኪሎሜትር ላይ ነዉ። በቦታዉም ላይ ለማስታወሻ ተብሎ የአጼ ምኒልክ ሐዉልት ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ እዚህ ቦታ ላይ በደርግ ዘመነ መንግሥት የተሰራ ጤና ጣብያ ነበር፤ ይህ የጤና ጣብያ ለአስር ዓመት አካባቢ እንዲዘጋ ተደርጎ ነበር፤ ከሆለት ዓመት በፊት ግን ተከፍቶአል። ከሁለት ዓመት በፊት  « የዳግማዊ ምኒልክ ወዳጆች ማኅበር»  የዳግማዊ ምኒልክን ልደት ለማክበርና እሳቸዉንም ለመዘከር ትዉልድ ቦታቸዉ ላይ በሄድንበት ጊዜ፤ ክሊኒኩን ተዘግቶ አገኘዉ፤ ክሊኒኩ ለምን እንደተዘጋ የአካባቢዉን ነዋሪ ጠይቀን አጥጋቢ መልስ ባለማግኘታችን፤ የወቅቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴየታ ፤ የአሁኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር አሚን አማንን የማግኘት እድሉ ስለነበር፤  ስለ ጉዳዩ ስናናግራቸዉ ችግር የለም እናጣራለን ብለዉ፤ በነገርናቸዉ በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ዳግሚ እንዲከፈት አድርገዋል። ጤና ጣብያዉ አሁን ዳግማዊ ምኒልክ በተወለዱበት ስፍራ ላይ አገልግሎት ጀምሮአል። 

Addis Abeba Geburtstagsfeier von Kaiserin Taitu und Kaiser Menelik
ምስል DW/S. Mushie

ከተቋቋመ ወደ አምስት ዓመት የሆነዉ «የእምዬ ምኒልክ ወዳጆች ማህበር»  የተሰባሰበዉ በመጀመርያ በፊስ ቡክ እንደሆን የነገረን ያሬድ ኃይሉ ቡድኑ አላማዉ ታሪክን ለትዉልድ ለማስተላለፍ አላማ ይዞ የተነሳ ነዉ ። ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በበኩሉ እንደተናገረዉ እንደ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የትልቅ ሃገር ባለቤት የትልቅ ሕዝብ አካል ሆነን ትልቅ ሆነን እንቀጥል ሲል አስተያየቱን ሰጥቶአል። ለዝግጅቱ መሳካት ቃለ ምልልስ የሰጡንን በማመስገን ሙሉ ስርጭቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።   

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ