1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ስለ ኤምፔሳ ፋይዳ ምን ይላሉ?

ቅዳሜ፣ ግንቦት 5 2015

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በእጅ ስልኮች አማካኝነት ገንዘብ የማንቀሳቀስ አገልግሎት የሚሰጥበትን ኤምፔሳ ሥራ ለማስጀመር የሚችለውን ፈቃድ ከሁለት ቀናት በፊት ከብሔራዊ ባንክ ተቀብሏል። አገልግሎቱ ገንዘብ በቀላሉ እንዲዘዋወር፣ ቁጠባ እንዲበረታታ እና እንዲያድግ ብሎም በረጅም ጊዜ ሂደት ዜጎች የብድር አማራጭ እንዲያገኙ እድል የሚያሰፋ ስለመሆኑ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4RJ0Q
 Kenia, Nairobi | Mobiles Bezahlsystem M-PESA
ምስል Daniel Irungu/EPA/dpa/picture alliance

የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ስለ ኤምፔሳ ፋይዳ ምን ይላሉ?

ኢትዮጵያ ውስጥ በተሰማራበት የቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደንበኞችን ማፍራቱን እያስታወቀ ያለው ሳፋሪ ኮም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገንዘብን በሞባይል ማስተላለፍ የሚችልበትን ፈቃድ ማግኘቱ "የፋይናንስ ቴክኖሎጂ እድገት የሚያስገድደው የዘመናዊነት ባህሪ" ማሳያ መሆኑን የምጣኔ ኃብት ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ ይገልፃሉ።
ባንክ ባልሆኑ ኩባንያዎች የተወሰነው የባንኮች አገልግሎት የሚሰጥበት ይህ አገልግሎት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚንሸራሸርበት ሥርዓት መፍጠር የሚያስችል በመሆኑ በበጎ የሚታይ እርምጃ መሆኑንም ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋውን ቴሌ ብር የተባለውን ሥርዓት በአብነት በመጥቀስ ያስረዳሉ። "ሳፋሪኮም ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ይህንን አገልግሎት እንደሚጀምር ይጠበቅ ነበር" ሲሉ ተናግረዋል። 
ግብይት ለመፈፀም ብዙ ብር ይዞ መንቀሳቀስ የሚፈጥረውን ሥጋት ከማስቀረት በላይ ይህ አገልግሎት በዓለም የገንዘብ እና የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ እየተሰራበት የቆየ መሆኑን የሚገልፁት ሌላኛው የምጣኔ ኃብት ባለሙያ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ፈቃዱን ያገኘው ኩባንያ ኬንያ ውስጥ በትሪሊየን የሚቆጠር ሽልንግ የሚያንቀሳቅስ የገንዘብ ዝውውር መላ ነው ብለዋል። "መጥፎ ጎን" ብለው የሚጠቅሱት ችግር እንደማይታያቸውም አክለው አብራርተዋል።
ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ሳፋሪ ኮም ገንዘብን በሞባይል ለማዘዋወር እንዲችል የተሰጠውን ፈቃድ ተከትሎ የሚደረገው የሥራ እንቅስቃሴ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግበት የሚገባ መሆኑን አቶ ዋሲሁን ያስታውሳሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የሰጠው የኬንያው ሳፋሪ ኮም ኤምፔሳ የቴሌ ኮም ኩባንያ በኢትዮጵያ ዘርፉን የተቀላቀለ ቀዳሚው የውጪ ኩባንያ ነው።

ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ