1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤሌክትሮኒክ ግብይት በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 27 2013

በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ግብይት የተሰማሩ ጀማሪ ኩባንያዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ከእነዚህ አንዱ የሆነው አስቤዛ መተግበሪያውን ወይም ድረ-ገጹን በመጠቀም ከመደብሮች እንጀራና የባልትና ውጤቶችን ጨምሮ የተለያዩ ነገሮች ለሚገዙ ደንበኞች ካሉበት ያደርሳል። የኩባንያው መሥራች በረከት ታደሰ አስቤዛ እንደ አማዞን የራሱ መደብር እንዲኖረው ይመኛል

https://p.dw.com/p/3t0J1
Äthiopien Bereket Tadesse, Chef des Online-Lebensmittelhandels "asbeza"
ምስል Bereket Tadesse

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የኤሌክትሮኒክ ግብይት በኢትዮጵያ

በረከት ታደሰ ከስድስት አመታት ገደማ በፊት የመጀመሪያ ልጁን ሲወልድ ለቤተሰቡ አስቤዛ የመሸመት ኃላፊነት ከእርሱ ትከሻ ላይ የወደቀ ነበር። በወቅቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ የነበረው በረከት "ብዙ ጊዜ በጣም በሥራ ከመወጠሬ የተነሳ እየረሳሁ ቤት እገባለሁ፤ ወይ አምሽቼ እገባለሁ፤ ወይም መደብር ተዘግቶ ነው የምደርሰው" ሲል ሁኔታው የፈጠረበትን ጫና ለዶይቼ ቬለ መለስ ብሎ እያስታወሰ ይናገራል።

"የሆነ ጊዜ በጣም ባለቤቴ ከመማረሯ የተነሳ ቢሮ የሚያመጣልኝ አገልግሎት ቢኖር ብዬ መፈለግ ጀመርኩ። የዚያን ጊዜ ምግብ ከሬስቶራንቶች የሚያደርስ ዴሊቨር አዲስ የሚባል አዲስ ቢዝነስ ነበረ። እሱ ካለ ከሱፐር ማርኬቶች ሊያመጣ የሚችል አገልግሎት የሰራ ሰው ይኖራል ብዬ መፈለግ ጀመርኩ። አንድም አልነበረም" ይላል በረከት።

የአስቤዛ ምስረታ ጥንስስ የተጣለው እንዲህ አስቤዛ መሸመት ከፈጠረው ችግር ነው። "እንደ እኔ የተቸገሩ ሰዎች ይኖራሉ" ከሚል ሐሳብ በበረከት የተጀመረው ውጥን ዛሬ ደንበኞች በኤሌክትሮኒክ ግብይት አስቤዛ የሚሸምቱበት ኩባንያ እንዲቋቋም መሠረት ሆኗል።

አስቤዛ ወደ ገበያው ከገባ ገና ሁለት አመታት ገደማ ቢሆነው ነው። በድረ-ገጽ እና ለእጅ ስልኮች በተዘጋጀው መተግበሪያ አማካኝነት ደንበኞች ከተመረጡ መደብሮች ያሻቸውን መሸመት ይችላሉ። ዳቦ እና እንጀራ የመሰሉ የበሰሉ ምግቦች ወይም ሽሮ እና በርበሬን የመሳሰሉ የባልትና ውጤቶች የሚፈልጉ ከመኖሪያ ቤታቸው ወይም ባሉበት ሆነው ያዛሉ። አስቤዛ ደንበኞቹ ያዘዙትን ከመረጡት የገበያ መደብር ተቀብሎ ካሉበት ያደርሳል። ፍራፍሬዎች፣ የዶሮ ምርቶች፣ የወተት ተዋጽዖዎች ሥጋ እና የአሳ ምርቶችንም አስቤዛ አብሯቸው ከሚሰራቸው መደብሮች መሸመት ይቻላል። 

በረከት "አስቤዛ መተግበሪያ ወይም ድረ-ገጽ ላይ ሲገቡ ፍሬሽ ኮርነር፣ ኦልማርት፣ ታፑ የሚባሉ መደብሮች አሉ። የእነሱን ሸቀጦች ወይም ምርቶች አስቤዛ ላይ እናስቀምጣለን። መሠረታዊ ሥራው ሰው አስቤዛን ተጠቅሞ ሲገዛ ከመደብሮቹ ተቀብሎ ለደንበኛው ማድረስ ነው" ሲል የኩባንያውን ሥራ አስረድቷል።

Äthiopien Bereket Tadesse, Chef des Online-Lebensmittelhandels "asbeza"
የአስቤዛ መስራች በረከት ታደሰምስል Bereket Tadesse

ይኸ ጀማሪ ኩባንያ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ገበያውን በማጥናት፣ አብረው ሊሰሩ የሚችሉ መደብሮችን በመለየት፣ ደንበኞች የሚሸምቱትን ሸቀጥ ለማድረስ የሚያገለግል አቅጣጫ ጠቋሚ ማፕ በማዘጋጀት ግፋ ሲልም ሥራውን ለመልመድ ጊዜ ፈጅቷል። ኩባንያው የራሱ የገበያ መደብሮች የሉትም። በአስቤዛ በኩል ለሽያጭ የሚቀርቡት ሸቀጦች ዋጋ የሚተመነውም በራሳቸው በመደብሮቹ አማካኝነት ነው። አንድ ሰው የሚሻውን ሸቀጥ ለመግዛት ትዕዛዝ በሰጠ በሁለት ሰዓታት ውስጥ ለማድረስ አስቤዛ ቃል ይገባል።

"ኮሮና እስኪመጣ ድረስ 95 በመቶ የሚደርሱ ተጠቃሚዎች ከውጭ አገር የመጡ ነዋሪዎች ነበሩ። በቀን 10 ትዕዛዝ ቢኖር ዘጠኙ ከውጭ መጥተው እዚህ አገር የሚኖሩ ዲፕሎማቶች ወይም የውጭ አገር ዜጎች ነበሩ። ምክንያቱም ሥራውን ሌላ አገር ያውቁታል። ልክ እዚህ ሲመጡ እንዲህ አይነት አገልግሎት ሲፈልጉ ብቸኛ የነበረው የእኛ ነበር። ከኮሮና በኋላ ግን በጣም በሚገርም ሁኔታ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ መቀላቀል ጀመረ። በቀን አስር እና አስራ አምስት ትዕዛዝ ከኖረ ግማሹ ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ግማሹ የውጭ አገር ዜጎች ናቸው" ይላል በረከት የኩባንያው ሥራ በገበያው የገጠመውን ሲያስረዳ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የዓለምን ምጣኔ ሐብት ሲደቁስ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚካሔደውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት ግን አጧጡፎታል።  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና ልማት ጉባኤ (UNCTAD) ባለፈው ሰኞ ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየው በጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ.ም. በመላው ዓለም የችርቻሮ ግብይት ውስጥ የኤሌክትሮኒክ ንግድ የነበረው ድርሻ 16 በመቶ ገደማ ብቻ ነበር። ይሁንና በአመቱ ማለትም በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም. ይኸ ወደ 19 በመቶ አድጓል። ደቡብ ኮሪያ፣ ብሪታኒያ፣ ቻይና፣ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ሲንጋፖር እና ካናዳ እንደ ቅድም ተከተላቸው የኤሌክትሮኒክ ግብይት በከፍተኛ ፍጥነት ያደገባቸው አገሮች ናቸው።

ዓለም አቀፉ የኤሌክትሮኒክ ግብይት በጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ.ም. ወደ 26.7 ትሪሊዮን ዶላር አድጓል። ይኸ ከቀደመው አመት ሲነፃጸር በ4 ከመቶ ከፍ ያለ ነው። በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም. ከፍተኛ ሽያጭ ካከናወኑ 13 ኩባንያዎች መካከል ከአመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ያማተረው የቻይናው አሊባባ እና የአሜሪካኑ አማዞን ቀዳሚ ናቸው። 

መንግሥት ገቢራዊ ከሚያደርጋቸው ማሻሻያዎች መፍትሔ የሚጠባበቀው የኢትዮጵያ ገበያ በዚህ ረገድ እጅጉን ኋላ ቀር ሆኖ ይታያል። የዓለም አገራት እና ሕዝቦቻቸው የኢንተርኔት አጠቃቀም በሚሰንደው ኢንተርኔት ወልድ ስታትስ (Internet World Stats) መሠረት በተያዘው የጎርጎሮሳውያኑ 2021 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ሕዝብ የኢንተርኔት ግልጋሎት የሚያገኘው 10 በመቶው ገደማ ብቻ ነው። የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከአመት አመት እየጨመረ ሲሔድ ስማርት ስልክ ያላቸው ዜጎች ቁጥር ግን አሁንም አነስተኛ ነው።

ኢትዮጵያ በኤሌክትሮኒክ ግብይት ረገድ ከኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ እንኳ ስትወዳደር አሁንም ኋላ ቀር መሆኗን የሚናገሩት በኢንተርኔት ሶሳይቲ የአፍሪካ ቀጠና ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳዊት በቀለ ለግብይቱ አስፈላጊ የሆኑ ተያያዥ መሠረተ-ልማቶች ጉድለት መኖሩን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ዶክተር ዳዊት በቀለ "ኢ-ኮሜርስ ኢንተርኔት ብቻ አይደለም የሚያስፈልገው። ኢንተርኔት ያስፈልገዋል። ነገር ግን በተጨማሪ ለምሳሌ ገንዘብ መቀያየር ያስፈልጋል። ለዚህ ኦን ላየን ያንን ገንዘብ የምንቀያየርበት መንገድ መኖር አለበት። ከሱም በተጨማሪ ደግሞ መተማመን ይኖርብናል። በተለይ ዋጋቸው ከፍ ላሉ ነገሮች በሕግ የታወቀ ነገር መሆን አለበት። እኔ አንድ ነገር ገዝቼ ስከፍል፤ ያንን የከፈልኩትን ቢክደኝ ፍርድ ቤት ሔጄ ማስመለስ ወይም አገልግሎቱን ማግኘት ይኖርብኛል። እንደገና ደግሞ አብሮት መምጣት ያለበት መሠረተ-ልማት አለ። አንድ ዕቃ ብገዛ፤ ያ ዕቃ ወደ እኔ መምጣት አለበት። በበለጸጉት አገሮች የፖስታ አገልግሎታቸው ቤት ድረስ ስለሚያመጣ ያንን መሠረተ-ልማት ይጠቀማሉ። ስለዚህ ምንም እንኳ ኢንተርኔት ቢኖርም አብዛኛው ነገር ኢንተርኔት ውስጥ አያልቅም። ዞሮ ዞሮ የአገሪቷ ሌላኛው መሠረተ-ልማት ያስፈልገዋል። እዚያም ላይ ትንሽ ወደ ኋላ ቀርተናል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ጁሚያ፣ ቀፊራ፣ ሸገር፣ ሼባ እና ደላላ የተባሉትንጨምሮ በርከት ያሉ ጀማሪ ኩባንያዎች በኢንተርኔት አማካኝነት የኤሌክትሮኒክ ግብይት አገልግሎት ያቀርባሉ። አብዛኞቹ ገዢ እና ሻጭ የሚገናኝባቸው ናቸው። ሻጮች የሸቀጦቹን ዋጋ እና ዝርዝር መረጃዎች በድረ-ገፆች በኩል ያቀርባሉ፤ ሸማቾች ደግሞ መርጠው ይገዛሉ። ከነጋዴዎቹ መካከል የተሸጠውን ዕቃ ለደንበኛ በነፃ ለማድረስ ቃል የሚገቡም ይገኙበታል።

Symbolbild Online Shopping
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ጁሚያ፣ ቀፊራ፣ ሸገር፣ ሼባ እና ደላላ የተባሉትንጨምሮ በርከት ያሉ ጀማሪ ኩባንያዎች በኢንተርኔት አማካኝነት የኤሌክትሮኒክ ግብይት አገልግሎት ያቀርባሉ።ምስል Colourbox

ለኤሌክትሮኒክ ግብይት የሚመጥን የተሸጠን ዕቃ ለሸማች የሚያደርስ ጠንካራ የፖስታ አገልግሎት አለመኖር ለእነዚህ ጀማሪ ኩባንያዎች አንዱ ፈተና ነው። በረከት "ሌላ አገር መንገዱ ስም እና ቁጥር አለው። [ዕቃ] ለማድረስ በጣም ቀላል ነው። እኛ አገር ግን የታዘዝንውን ለማድረስ አድራሻ በጣል ግልጽ አይደለም። ለዚህ መፍትሔ ያበጀንው የጎግልን ጂፒኤስ ተጠቅመን ነው" በማለት እንዴት ለገጠማቸው ችግር መላ እንደዘየዱ አስረድቷል።

ኢትዮጵያ የኤሌክሮኒክ ግብይት የሚገዛበት አዋጅ ያጸደቀችው ባለፈው ግንቦት 2012 ዓ.ም. ነው። የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽ አዋጅ "ኢንተርኔትን ወይም ሌሎች የመረጃ መረብን በመጠቀም የሚደረግ የሸቀጦች እና የአገልግሎቶች ግብይት ወይም ልውውጥን" ሕጋዊ ማዕቀፍ ሰጥቷል። አዋጁ በግብይቱ የሚሳተፉ ወገኖችን ማንነት፣ ግብይት ወይም የአገልግሎት ልውውጥ የሚደረግበትን አኳኋን፣ የክፍያ አፈጻጸምን በዝርዝር ይበይናል። ይኸ አዋጅ ለኤሌክትሮኒክ ግብይት ዕድገት ከፍ ያለ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። በአዋጁ "የኤሌክትሮኒክ ንግድ ፕላትፎርም አንቀሳቃሽ" የሚል ስያሜ የተሰጣቸው አስቤዛን የመሳሰሉ ኩባንያዎች ለጊዜው ባለው የክፍያ ሥርዓት ሥራቸውን ለማቀላጠፍ እየታተሩ ነው።

የአስቤዛ መሥራች በረከት "ኢንተርኔት ተጠቅሞ ሰው ክፍያ መፈጸም ይችላል። ነገር ግን አሁንም ይኸ ኦን ላይን ክፍያ ነው ማለት ያስቸግራል። ነገር ግን እየመጡ ያሉ ኩባንያዎች አሉ። አሞሌ ከዳሽን ባንክ ጋር ጥሩ የክፍያ ሥርዓት አላቸው። ብዙ ሰው ይጠቀማል። እኛ እንዲያውም ከጠበቅንው በላይ ሰው በአሞሌ ይጠቀማል። ሌላው ዳሸን ባንክ እና አቢሲኒያ ባንክ ሳይበር ሰኪዩር ከሚባል የውጭ ኩባንያ ጋር ሥምምነት ፈጽመው በቪዛ ካርድ እና በማስተር ካርድ ሰዎች መክፈል እንዲችሉ አማራጭ አዘጋጅተዋል" ብሏል።

ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ኤሌክትሮኒክ ግብይት ካዞረችበት ጊዜ ጀምሮ ዘርፉን በቅርበት የሚያውቁት ዶክተር ዳዊት በርከት ያሉ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ወደ ጥቅም ሊለወጡ የሚችሉ ናቸው የሚል ዕምነት አላቸው።

"አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የባንክ አገልግሎት ውስጥ የለም። ክሬዲት ካርድ የሚባል ነገር የለውም። አብዛኞቹ የበለጸጉት አገሮች የሚሰሩት በክሬዲት ካርድ ነው። እኛ አገር ግን የሞባይል የክፍያ ሥርዓቶችን ተጠቅመን [ግብይቱን ለማሳደግ] ትልቅ አቅም አለ። ያ ደግሞ ጥቅም የሚኖረው ለንግዱ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ሰው የባንክ አካውንት ባይኖረውም የፋይናንስ አገልግሎት ውስጥ እንዲካተት ያደርገዋል። የፖስታ አገልግሎትም በየቤታችን ላያደርስ ይችላል። ነገር ግን እሱን የሚተኩ ሌሎች አገልግሎቶች እየተቋቋሙ ነው። በሞተር ሳይክል ቤት ድረስ የሚያመጡ አሉ" የሚሉት ዶክተር ዳዊት "በኢ-ኮሜርስ ውስጥ የዛሬ 22 አመት ነው የገባሁት። በዛን ጊዜ አንዳንድ ችግሮች በምንም አይነት መፍትሔ የማያገኙ መስሎ ነበር የሚታዩኝ። በዛሬ ዘመን ጥሩ ነገር ያለው ለሁሉም ችግር መፍትሔ ይገኛል" ሲሉ ያስረዳሉ።  

ጀማሪዎቹ ኩባንያዎች ለሚገጥማቸው ፈተና መፍትሔ እያፈላለጉ ሥራውን ለማቀላጠፍ የሚያደርጉት ጥረት ግን በዋናነት አዲስ አበባ ላይ ያተኮረ ሆኖ ይታያል። በእርግጥ ከአዲስ አበባ ዋና ዋና ወደሚባሉ ከተሞች ደንበኞች የሸመቷቸውን ዕቃዎች ለመላክ የሚሞክሩ አይጠፉም። ይኸ ግን ወጥ ሥርዓት ያልተበጀለት እና በግለሰቦች ጥረቶች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ነው።

"ይኸ በግምት ስናገር ትልቅ ስላልሆኑ ነው። በአብዛኛው ትንሽ በሚሆኑበት ጊዜ በብዛት ሰው የተከማቸበት ቦታ በመስራት ያለችው ገበያ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። ባደጉ ቁጥር ይኸ ገበያ ስለማይበቃቸው ወደ ሌላም ይሔዳሉ ብዬ እገምታለሁ። ሌላውም ጋ የሆነው ይኼ ነው። ወደ ገጠር የሚሔዱት በአብዛኛው መሀል ከተማ ያለው ዕድል ሲያልቅባቸው ነው" ሲሉ ቀስ በቀስ ሥራው ትኩረቱን ሊቀይር እንደሚችል ዶክተር ዳዊት ገልጸዋል።

Symbolbild E-Commerce in Afrika
በበለጸጉት አገሮች የኤሌክትሮኒክ ንግድ ጥቅም ላይ የሚውለው ክሬዲት ካርድ በኢትዮጵያ ሥራ ላይ አለመዋል ለዘርፉ እንደ ችግር ከሚጠቀሱ መካከል ይገኝበታልምስል imago images/Westend61

"ከዚህ በተጨማሪ ከኢንተርኔት ሶሳይቲ ጋር እየሰራንው ያለንው ነገር ገጠሩ ራሱ ፈጠራ ላይ እንዲሰማራ ማድረግ ነው። በአሁኑ ጊዜ ብዙ የተማሩ ኢትዮጵያውያን በገጠር አሉ። ሥራ አጥተው ሲቸገሩ ወደ ገጠር ሔጄ ለመመልከት ችያለሁ። ያ የሚባክን የሰው ኃይል ነው። እነዚያን ሰዎች፤ እነዚያን ወጣቶች የማይሆን ሥራ ላይ፤ አንዳንድ ጊዜም ሥራ አጥተው ቁጭ ከሚሉ ዕድል ሰጥቶ የአካባቢያቸውን ችግር ለመፍታት እንዲችሉ ማድረግ ይቻላል" ሲሉ ሊሰራ ይገባል የሚሉትን ጠቁመዋል።

የበረከት ታደሰ አስቤዛ አብሯቸው የሚሰራቸው መደብሮች በመደርደሪያቸው የሚገኙ ሸቀጦችን ትክክለኛ ዝርዝር በወቅቱ ማግኘት ይፈትነዋል። ደንበኞች መሸመት የሚፈልጉትን ሸቀጥ ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ "አልቋል" የሚል መልስ ይመጣል። የሸቀጦች ዋጋ መዋዠቅ ሌላው ፈተና ነው። በረከት ፈገግ እያለ "ጠዋት የነበረው የቲማቲም ዋጋ ከሰዓት ይጨምራል" ሲል የገጠመውን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።

በሥራው ላይ የሚገጥሙት ፈተናዎች ግን እንዲያፈገፍግ የሚያስገድዱት አይመስሉም። "ከእርሻ ቦታ መጥቶ እስከ ሚሸጥበት ወይም ከአስመጪው ቦታ መጥቶ እኛ እስከምንሸጥበት ድረስ ያለው የዋጋ ልዩነት በጣም ሰፊ ነው። ከምንጩ በቀጥታ ወደ ደንበኞቻችን ማምጣት የምንችልበትን ሥርዓት መፍጠር እንፈልጋለን። ገበሬው ነገ ራሱን ምርቶቹን ማቅረብ እንዲችል፤ መሀል ላይ ያሉትን ደላሎች በተወሰነ ቀንሶ ዕቃዎችን በማቅረብ ደንበኞች በጣም በቅናሽ ዋጋ ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ ቢቻል ብለን እናስባለን" በማለት የረዥም ጊዜ ዕቅዱን ይናገራል። በረከት አስቤዛ እንደ አሜሪካኑ አማዞን እና እንደ ቻይናው አሊባባ ሁሉ የራሱ የግብይት መደብር ቢኖረው የሚል ምኞት ጭምር አለው።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ