የኢዜማ ጉባኤ በባሕር ዳር
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 18 2012የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ዛሬ በባሕር ዳር ባደረገው ውይይት ኢትዮጵያ ቀዳሚ ነፃነቷን ያስከበረች የአፍሪካውያን ምሳሌ ብትሆንም አሁን አሁን የሕዝቦች በሰላም ውሎ መግባት ፈተና የሆነባት አገር አንደሆነች በውይይቱ ተነስቷል። የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እንዳሉት አገሪቱ አሁን በዲሞክራሲ እጦት ችግር ውስጥ ብትሆንም ብሩህ ተስፋ ግን ከፊቷ እንዳለ አመልክተዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ፓርቲቸው በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ሰፊ የምርጫ ወረዳ መሸፈን መቻሉን የተናገሩት አቶ የሺዋስ ለዚህም በፓርቲው ውስጥ ጠንካራና ኢትዮጵያን የሚያስቀድሞ አመራሮች በመኖራቸው መሆኑን አመልክተዋል።
በቀጣዩ ምርጫ የዴሞክራሲ መሰረት መጣል አንዳለበት የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ ለዚህም ሰላማዊ የምርጫ ሂደት፣ ምርጫውን ሊሸከም የሚችል ዲሞክራሲያዊ ተቋማት መዘርጋትና አማራጭ ፓርቲ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አቶ ንጉሴ ዳኛው የተባሉ የውይይቱ ተካፋይ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት በተናጠል መደራጀት አገሪቱን ቁልቁል ወስዷታል፣ አንድነትን በሚያጠናክሩ አደረጃጀቶች ህዝቡ መሰባሰብ አለበት ነው ያሉት፡፡ ወ/ሮ ገነት አሰፋ በበኩላቸው የተለያዩ የዓለም አገራትን ተሞክሮ በማንሳት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ብዛት ከጥንካሬ ይልቅ ድክመትን የሚያሳይ በመሆኑ ውህደት መፍጠር አለባቸው ብለዋል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) 10 የፖለቲካ ድርጅቶችን በማዋሃድ በቅርቡ የተደራጅ የፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡ በስፍራው የሚገኘው ዘጋቢያችን ዓለምነው መኮንን ዝርዝሩን ልኮልናል።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ