1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የኢዘዲን ከሚል የፈጠራ ስራዎች 

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 21 2012

በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት እያጋጠመ ያለውን እጥረት ለመፍታት የመተንፈሻ መሳሪያ ወይም ቬንትሌተርን ጨምሮ ሶስት የፈጠራ ስራዎችን ሰርቷል።ለበሽታው ሊያጋልጡ የሚችሉ ድርጊቶች ለፈጠራ ስራዎቹ መነሻ ሆነውታል። 

https://p.dw.com/p/3bYnp
Äthiopien | Erfinder Ezedin Kamil baut improvisierte Coronahilfsmittel
ምስል Ezedin Kamil

ወጣቱ የብዙ ፈጠራ ባለቤት

የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ላይ ከተከሰተ ወዲህ የህክምና መሳሪያዎችና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ከምን ጊዜውም በላይ አንገብጋቢ ጉዳዮች ሆነዋል።ይሁን እንጅ ወረርሽኙ በድንገት የተከሰተ በመሆኑ ጥሩ የህክምና አቅርቦት ላላቸው  ሀገራት ጭምር አቅምን የሚፈትን ሆኗል።

Äthiopien | Erfinder Ezedin Kamil baut improvisierte Coronahilfsmittel
ምስል Ezedin Kamil

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ቀድሞውንም ደካማ የጤና ስርዓትና የህክምና ቁሳቁስ እጥረት ላለባቸው ሀገራት ደግሞ ችግሩ የበለጠ ነው የሚሆነው። ወቅቱ ለጋሾች በራቸውን የዘጉበትና ሙሉ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ወረርሽኙን በመከላከል ላይ የሆኑበትና ፤መሳሪያዎቹን ገዝቶ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባትም ብዙ ወጭ የሚጠይቅ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ያለው አማራጭ የሀገር ውስጥ አቅም፣ፈጠራና ሀብትን መጠቀም ነው።ይህንን በመገንዘብ ይመስላል ወረርርሽኑን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አንዳንድ የፈጠራ ባለሙያዎች ችግር ፈቺ ስራዎችን ይዘው መምጣት ጀምረዋል። ከነዚህም መካከል ወጣት ኢዘዲን ከሚል አንዱ ነው።ኢዘዲን በውልቂጤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ሲሆን በርካታ የፈጠራ ስራዎች አሉት። 

«ከፈጠራ ስራዎቼ ለመጥቀስ ያህል በፀሀይ ብርሃንና በኤለክትሪክ የሚሰራ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ ሰርቼ ነበር።ምንም አይነት ነዳጅ አይጠቀምም።ለአየር ንብረት ተስማሚ ነው ።በስዓት 60 ኪሎ ሜትር ይሄዳል።» ከዚህ በተጨማሪ በኤለክትሪክና በፀሀይ ብርሃን የሚሰራ ብስክሌት ሽልማት አግኝቷል። 
«በኤለክትሪክና«በሶላር» ብርሃን «ቻርጅ» አድርጎ የሚሰራ ብስክሌት ሰርቼ ነበር በሱም ዩንዲፒ ባዘጋጀው «የሩራል ኢነርጅ ቴክኖሎጅ» የፈጠራ ውድድር በሀገር አቀፍ ደረጃ አሸናፊ ሆኜ የ8 ሺህ ዶላር አሸናፊ ሆኘ ነበር።» 

Äthiopien | Erfinder Ezedin Kamil baut improvisierte Coronahilfsmittel
ምስል Ezedin Kamil

ለደህንነት መጠበቂያ የሚሆኑ እንቅስቃሴን በማጥናትና በመለየት ንብረትን ከስርቆት ለመጠበቅ የሚያስችል ደወል፣በይለፍ ቃል ወይም «በፓስወርድ» በየትኛውም ቦታ ሆኖ የሚከፈት፣ የሚዘጋና የሚቆጣጠር የቤት በር ፣ ለአካልጉዳተኞች ተስማሚ የሆነ መብራትን ከርቀት ማብራትና ማጥፋት የሚችል የአንሮይድ መተግበሪያ መስራቱንም ይናገራል። 
ኢዘዲን የ18 ዓመት ወጣትና ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆን ስራውን የጀመረውም የ4ተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ነው። እስካሁን 30 የሚሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን መስራቱንም ይናገራል። ከነዚህም ውስጥ 7 ቱ የአንድሮይድ መተግበሪያዎች ሲሆኑ 13ቱ የፈጠራ ሥራዎቹ ደግሞ «ሴቭ አይዲያስ ኢንተርናሽናል» በተባለ ድርጅት የባለቤትነት መብት ማግኘቱን ገልጾልናል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት እያጋጠመ ያለውን እጥረት ለመፍታት የመተንፈሻ መሳሪያ ወይም ቬንትሌተርን ጨምሮ ሶስት የፈጠራ ስራዎችን ሰርቷል።ለበሽታው ሊያጋልጡ የሚችሉ ድርጊቶች ለፈጠራ ስራዎቹ መነሻ ሆነውታል። 

Äthiopien | Erfinder Ezedin Kamil baut improvisierte Coronahilfsmittel
ምስል Ezedin Kamil

በግል በተወሰነ መልኩ በገንዘብና በቴክኒክ የሚደግፉት እንዳሉ የሚናገረው ኢዘዲን በቂ የገንዘብ ድጋፍ ከተገኘ የመተንፈሻ መሳሪያውን በስፋት ማምረትና ለህብረተሰቡ ማድረስ ይቻላል ይላል።ከዚህ በተጨማሪም ማህበራዊ ርቀትን ለመጠበቅና የዕጅና የፊት ንክኪ ለመቀነስ የሚያግዝ የፈጠራ ስራም አለው። 
ለፈጠራ ስራዎቹ በአካባቢው በቀላሉ የሚገኙ የወዳደቁ ቅሳቁሶችን፣መስራት ያቆሙ የኤለክትሪክ መሳሪዎችን በተለይ ተጥለው ቶሎ ወደ አፈርነት የማይለወጡና የአካባቢ ብክለትን ሊያመጡ የሚችሉ የፕላስቲክ ዕቃዎችን ይጠቀማል።በአካባቢው የሚያየው ችግር ለፈጠራ ስራዎቹ መነሻ እንደሆነው ይናገራል። 

Äthiopien | Erfinder Ezedin Kamil baut improvisierte Coronahilfsmittel
ምስል Ezedin Kamil

ያምሆኖ የፈጠራ ስራዎቹ ተባዝተው ለህብረተሰቡ መድረስ አልቻሉም።ከበርካታ ስራዎቹ መካከል የእሳት አደጋ መጠቆሚያ ደወሉ ና ከሰው ንክኪ የሆነ የእጅ መታጠቢያ ስራ ላይ ውሏል።ከነዚህ ስራዎች ውጭ አብዛኛዎቹ ወደ ምርት አልገቡም ለዚህም ትልቁ ችግር የገንዘብ አቅም መሆኑን ያስረዳል። 
የፈጠራ ስራውን አይቶ የጤና ጥበቃ ምንስቴር የድጋፍ ደብዳቤ የሰጠው ሲሆን የሳይንስና የኢኖቬሽን ምንስቴር ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ የፈጠራ ስራዎችን ለማወዳደር ባወጣው አስቸኳይ መርሃ- ግብር ላይ ተመዝግቦ ውጤት እየተጠባበቀ መሆኑን አጫውቶናል።ኢዘዲን ሙያውን በትምህርት በመደገፍ የፈጠራ ስራዎች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ማድረግ ወደ ፊት ሊያሳካ የሚፈልገው ህልሙ ነው። 


ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሐመድ