1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያው ጦርነት፣ የሰላም ጥረትና ተስፋው

እሑድ፣ መስከረም 8 2015

ጦርነቱ ጋል ደግሞ በረድ እያለ ሁለት ዓመት ሊደፍን ጥቂት ሳምንታት ቀርተውታል። የኢትዮጵያ መንግሥትም፣ህወሓትም በአፍሪቃ ኅብረት በሚመራ የሰላም ሂደት ለመሳተፍ ዝግጁነታቸውን ቢናገሩም፣ ውጊያውን ግን እስካሁን አላቆሙም። የጦርነቱ ማብቂያ የት ነው?የታቀደው የሰላም ሂደትስ ምን ተስፋ አለው?

https://p.dw.com/p/4GzuC
Infografik Karte Äthiopien AM

የኢትዮጵያው ጦርነት፣ የሰላም ጥረትና ተስፋው

አዲሱን ዓመት ከተቀበለች አንድ ሳምንት የሆናት ኢትዮጵያ ዛሬም እንደአምናው ከውጊያ አልራቀችም። ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓም በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰው ውጊያ፣ ወደ አዲሱ ዓመትም ተሻግሮ፣ የሰው ሕይወት መጥፋቱ ፣ንብረት መውደሙ ፣ሰዎች መፈናቀላቸውና መንገላታታቸው ቀጥሏል። ሰሞኑን በመቀሌ በተካሄዱ የአየር ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውና መቁሰላቸው ተዘግቧል። ውጊያው ዳግም በተጀመረባቸው የአማራ ክልል ከተሞችና ከአፋር ክልል በርካቶች ቀያቸውን ለቀው በየቦታዎው እንደተበታተኑ ነው። በኢትዮጵያ ኃይሎችና በኤርትራ ወታደሮች የተቀነባበረ ጥቃት ተፈጽሞብኛል የሚለው ህወሓት ቀድሞ ወደ ለቀቃቸው ትግራይን የሚያዋስኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች ተመልሶ ከገባ በኋላ አሁንም እንዳልወጣ ነው የሚነገረው ። ይዞታዬ ናቸው ከሚላቸው አወዛጋቢ አካባቢዎች ህወሓትን ለማስወጣትም ውጊያው እንደቀጠለ መሆኑ ይሰማል።በዚህ መሀል ከዚህ ቀደም የአፍሪቃ ኅብረትን አሸማጋይነት አልቀበልም ሲል የነበረው ህወሓት ተኩስ ለማቆምና በአፍሪቃ ኅብረት በሚመራ የሰላም ሂደት ተካፋይ ለመሆን ዝግጁ ነኝ ሲል አስታውቋል። የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚህ ሳምንት ከአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳዮች አገልግሎት የአፍሪቃ ክፍል ሃላፊ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት መንግሥታቸው በአፍሪቃ ኅብረት በሚመራ የሰላም ሂደት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። ሁለቱም ወገኖች ዝግጁነታቸውን ቢናገሩም፣ ውጊያውን ግን እስካሁን አላቆሙም። ጦርነቱ ጋል ደግሞ በረድ እያለ ሁለት ዓመት ሊደፍን ጥቂት ሳምንታት ቀርተውታል። የጦርነቱ ማብቂያው የት ነው? የታቀደው የሰላም ሂደትስ ምን ተስፋ አለው? ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት ለመፍታትስ ምን መደረግ አለበት? በነዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ  ላይ የሚወያዩ ሦስት እንግዶች ጋብዘናል ።እነርሱም ዶክተር ደምመላሽ መንግሥቱ በጅማ ዩኒቨርስቲ የግጭት አወጋገድ የባህል ግንኙነትና፣ የህዝብ ዲፕሎማሲ መምህር ፣አቶ በፍቃዱ ድሪባ በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህርና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እንዲሁም ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ የቀድሞ የቅንጅት መስራችና «መግባባት»የተባለው መጸሐፍ ደራሲ ናቸው።ሙሉውን ውይይት ለማዳመጥ ከታች የሚገኘውን የድምጽ ማዕቀፍ ይጫኑ።

ኂሩት መለሰ