1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያዉን ፈተና በሳዑዲ አረቢያ

ሰኞ፣ ሐምሌ 19 2013

እስካሁን የሚደረገዉ አሰሳ በየአዉራጎዳናዉ እንጂ ቤት እየተሰበረ አልነበረም-አንድ።በኢትዮጵያዉያን ላይ ብቻ ያነጣጠረም አይደለም።ከሁሉም በላይ ሕጋዉ ፍቃድ ያላቸዉን አይመለከትም።በዚሕም ሰበብ ብዙ ኢትዮጵያዉያን ያሁኑ ዘመቻ፣ በሕዳሴ ግድብ መገንባት ሰበብ ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገበዉ የግብፅ ረጅም እጅ ዉጤት ነዉ ብለዉ ያምናሉ

https://p.dw.com/p/3y5KY
ፎቶ፣ የ2019ምስል picture-alliance/AP/E. Asmare

ማሕደረ ዜና፦ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ አረቢያ «ሐበሻ ከሆኑ አራስ፣ ሕፃን፣ ሸማግሌም... ይታሰራሉ»

የዓለምን የመረጃ ልዉዉጥ የሚቆጣጠሩት የምዕራባዉያን ግዙፍ መገናኛ ዘዴዎች እስካሁን ከቁብ አልቆጠሩትም።ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ እስከሚባሉት የመብት ተሟጋች ተቋማት ከመብት ጥሰት መለኪያቸዉ አልጣፉትም።ሌላዉ ቀርቶ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች (የመንግሥት ይሁኑ ተቃዋሚ) ባለፍ አገደም እያነሱ ከመጣል በላይ የስቃይ-ሰቆቃዉን መጠን በግልፅ አይናገሩትም።ድሕነትን ሽሽት፣ ጉርስ፣ልብስ ፍለጋ የተሰደዱ ኢትዮጵያዉያን ግን በሳዑዲ አረቢያ ፀጥታ አስከባሪዎች በገፍ ይታፈሳሉ፣ ይደበደባሉ፣ ይዘረፋሉ፣ ሲከፋም አንድም በየእስር ቤቱ ይሞታሉ፤ አለያም በየአስፋልት-ሕንፃዉ እራሳቸዉን ያጠፋሉ።ምናልባትም የመቶ ሺዎች ድምፅ።ሰሚ ያገኝ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ጊዜና የማወቅ ጉጉቱ ካለዎት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠብአዊ መብት ምክር ቤትን ይፋ አምደ መረብ ይክፈቱ።ዜና የሚለዉን ገፅ ይመልከቱ።ምክር ቤቱ ከኃምሌ 9 እስከ 22፣ 2021 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ካሳለፋቸዉ 10 ዉሳኔዎች አንዱ ኢትዮጵያን ይመለከታል። ምክር ቤቱ ትግራይ ክልል ዉስጥ ይፈፃማል ያለዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማስወገድ ይረዳል ያለዉን ሶስት ረቂቅ ዉሳኔዎች ማፅደቁን ያትታል-ዜናዉ።ምክር ቤቱ 3 ዉሳኔዎችን ባሳለፈበት ዕለት የሳዑዲ ረቢያ ፀጥታ አስከባሪዎች በኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ላይ የከፈቱትን የማሰር፣ማንገላታት አንዳዴም የድብደባና ግፍ ዘመቻን ለሁለተኛ ሳምንት ቀጥለዉ ነበር።አይማን በሚል ስሙ ብቻ መጠራቱን የመረጠዉ ኢትዮጵያዊ፣ ሳዑዲ አረቢያ ተወልዶ አድጎ፣ ኢትዮጳያ ጋዜጠኝነት ተምሮ አሁን ጂዳ ሳዑዲ አረቢያ ይኖራል።እንዲሕ አለን።

የሳዑዲ አረቢያ ፀጥታ አስከባሪዎች ሕጋዊ  የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸዉን የዉጪ ሐገር ዜጎች በዘመቻ እያሰሱ ሲይዙ፣ሲያስሩና ወደየሐገራቸዉ ሲሊኩ ያሁኑ የመጀመሪያቸዉ አይደለም።አይማን እንዳለዉ እስካሁን የሚደረገዉ አሰሳ በየአዉራጎዳናዉ እንጂ ቤት እየተሰበረ አልነበረም-አንድ።በኢትዮጵያዉያን ላይ ብቻ ያነጣጠረም አይደለም።ከሁሉም በላይ ሕጋዉ ፍቃድ ያላቸዉን አይመለከትም።በዚሕም ሰበብ ብዙ ኢትዮጵያዉያን ያሁኑ ዘመቻ፣ በሕዳሴ ግድብ መገንባት ሰበብ ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገበዉ የግብፅ ረጅም እጅ ዉጤት ነዉ ብለዉ ያምናሉ።በጂዳ የኢትዮጵያ ቆስላ ምክትል ኃላፊ (ኮንሱል ጄኔራል) ነብዩ ተድላ ግን «ፖለቲካዊ» የሚለዉን ምክንያት አይቀበሉትም።

Jeddah in Saudi Arabien
ምስል Getty Images/K. Sahib

                                                                               

ምክንያቱ ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ ሊሆን-ላይሆንም ይችላል።ኢትዮጵያዉያን ከሌሎች ተመርጠዉ መያዝ፣መደብደብ፣መሰቃየት፣ መንገላታት፣ መዘረፍ፣ መጋዛቸዉ ግን በየትኛዉም መመዘኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት አይደለም ሊባል አይችልም።እንዳዶች እንደሚሉት የዘመቻ-እስራት፣ በደል ግፉ ልክ፣ በሌላዉ ሕዝብ ዘንድ እንደወንጀለኛ የመቆጠራቸዉ ዉርደት አንዳዶችን እራስን እስከ ማጥፋት ለደረሰ ጭንቀት ዳርጓቸዋል።

አይማን «ሐበሻ ከሆነች አራስም አልቀረች» ይላል።ብሎገር ግራዝማች ሻፊ ሕጋዊ የስራና የመኖሪያ ፈቃድ አለዉ።ኢጋማ ወይም ኢቃማ።ሕጋዊ ፍቃዱ ግን ከመታሰር አላደነዉም።ሐበሻ ነዋ።ማን ይናገር የታሰረ።

ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል ዘንድሮ  ግንቦት 4፣ ሰኔ 29 እና ኃምሌ 16 ኢትዮጵያ ዉስጥ እና በኢትዮጵያዉያን ላይ የሚደርስ «የሰብአዊ መብት ጥሰት» ያለዉን ዘገባ አዉጥቷል።የሳዑዲ አረቢያን የመብት ጥሰት በሚመለከት እስካሁን የመጨረሻ ዘገባዉ የሐገሪቱ  መንግስት «ወንጀለኛ» ያለዉን አንድ ወጣት ዜጋዉን እንዳይገድል የሚጠይቅ ነዉ።የሳዑዲ አረቢያ ፀጥታ አስከባሪዎች ወንጀለኛዉን ከሕጋዊዉ ሳይለዩ ሐበሻ በመሆናቸዉ ብቻ በኢትዮጵያዉያን ላይ ስለሚያደርሱት ግፍና በደል ግን ዕዉቁ የመብት ተሟጋች ድርጅት እስካሁን ያለዉ የለም።ዩሑማን ራይትስ ዋች የተባለዉ ሌላዉ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች በሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ላይ ሥለሚፈፀመዉ ግፍ ለመጨረሻ ጊዜ የዘገበዉ ባለፈዉ መጋቢት ነበር።በጂዳ የኢትዮጵያ ቆስላ ምክትል ኃላፊ ነብዩ ተድላ በየእስር ቤቱ በየጊዜዉ ኢትዮጵያዊ ይሞታል የሚለዉን አስተያየት አይቀበሉትም።የሳዑዲ አረቢያ ፀጥታ አስከባሪዎች በኢትዮጵያዉያን ላይ ስለሚያደርሱት የሰብአዊ መብት ጥሰት ግን ቆስላዉ «ጥቆማ እየተቀበለ እየመዘገበ» ነዉ።ይላሉ።የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከሳዑዲ አረቢያ አቻዎቻቸዉ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ኢቃማ ያላቸዉ ኢትዮጵያዉያን መያዛቸዉ ቆሟል።ድብደባዉም ቀንሷል።የተጠርጣሪዎችን ቤት መሰበር፣ማንገላታት ማሰር-ማጋዙ ግን ብዙዎች እንደሚሉት አሁንም ቀጥሏል።

Illegale aus Äthiopien in Saudi-Arabien
ፎቶ፣2017ምስል DW/Sileshi Sibiru

አቶ ነብዩ እንደገለፁልን ባዲሱ ዘመቻ፣ ቆስላቸዉ በሚወከልበት በጂዳና በምዕራብ ሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ከተሞች ብቻ ከሐምሳ ሺሕ የሚበልጡ ኢትዮጵያዉያን ተይዘዋል።ገሚሶቹ ወደ ሐገራቸዉ ገብተዋል።ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ጉዳይ ድርጅት IOM እንደሚለዉ፣ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት «ሑከት የሌለባት ሐገር» ባለዉ ዘመቻ የዉጪ ሐገር ዜጎችን ማስወጣት ከጀመረበት ከመጋቢት 2017 እስከ ታሕሳስ 2020 ድረስ ከ352 ሺሕ የሚበልጡ ኢትዮጵያዉን ስደተኞች ከሳዑዲ አረቢያ አዲስ አበባ ገብተዋል።ባዲሱ ዘመቻ የሚያዙ ኢትዮያዉያንን ማገዙ ቀጥሏል።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ