1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያን ወዳጁ መታሰብያ ከቦታዉ ተነሳ

ዓርብ፣ ጥር 19 2015

በኢትዮጵያ ትልቅ እውቅናና ክብር የተቸረው የበጎ ሥራ አገልግሎት የሰጡት የሰዎች ለሰዎች ድርጅት መሥራች የካርልሄንዝ በም መታሰቢያ ሐውልት በስማቸው ከተሰየመበት አደባባይ ለትራፊክ ፍሰት ሲባል ከቦታዉ ተነሳ። ካርል በኢትዮጵያ ላበረከቷቸው በጎ ሥራዎች የተሰየመላቸዉ አደባባይ ተነስቶ በትራፊክ መብራት የመተካት ሥራ መጀመሩ ባለስልጣን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4MoJi
Äthiopien, Addis Abeba | Karl-Heinz Böhm Statue
ምስል Tobias Hase/dpa/picture alliance

በኢትዮጵያ ትልቅ እውቅና እና ክብር የተቸረው የበጎ ሥራ አገልግሎት የሰጡት የሰዎች ለሰዎች ድርጅት መሥራች የካርልሄንዝ በም መታሰቢያ ሐውልት በስማቸው ከተሰየመበት አደባባይ ለትራፊክ ፍሰት መሳለጥ ሲባል ከቦታዉ ተነሳ።
ዶክተር ካርልሄንዝ በም በኢትዮጵያ ላበረከቷቸው ዘመን ተሻጋሪ በጎ ሥራዎቻቸው በስማቸው ተሰይሞላቸው የነበረው አደባባይ ተነስቶ በትራፊክ መብራት የመተካት ሥራ ካለፈው ቅዳሜ ምሽት ጀምሮ የመንገድ ሥራ መጀመሩን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታውቋል።

"ካርል ሄንዝ በም፣ ሀገራችን በተፈጥሮ አደጋ በተፈተነችበት ወቅት በሰብዓዊነት ያከናወኑት ሰናይ ተግባር ምንጊዜም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሲዘከር ይኖራል" ያለው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን "በመንገድ ሥራው መክንያት የተነሳው ሐውልት በተመረጠ ሥፍራ ላይ መልሶ የሚቆም ከመሆኑም በተጨማሪ ከብስራተ ገብርኤል ወደ ልደታ ፍርድ ቤት የሚወስደው መንገድ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል በስማቸው የሚሰየም ይሆናል" በማለት አስታውቋል

የዶቼ ቬለ የአዲስ አበባ ዘጋቢ ሰለሞን ሙጬ ያነጋገራቸዉ፤ በኢትዮጵያ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ተወካይ ፤ አቶ ይልማ ታዬ፤ ሐውልቱ ሌላ ቦታ ላይ መልሶ እንደሚቆም ከከተማ አስተዳደሩ እንደሰሙ ለዶቼ ቬለ ( DW ) ተናግረዋል።

በካርል ሄንዝ በም የተመሰረተውና ከ 45 ዓመታት በላይ አያሌ ኢትዮጵያዊያንን በተለያዩ ዘርፎች ያገለገለው ሰዎች ለሰዎች ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት፣ በጤና ፣ በግብርናና ሌሎች ግብረ ሰናይ ተግባራት ከፍተኛ ሥራዎችን አከናውኗል።
በድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አርባ አመታት 460 ትምህርት ቤቶች፤ ስምንት የሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ተገንብተዋል። በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅና ከፍተኛ ከበሬታ ያላቸው የሰዎች ለሰዎች ድርጅት መሥራቹ አውስትሪያ ጀርመናዊው የፊልም ባለሙያ እና በጎ አድራጊ ዶክተር ካርልሄንዝ በም የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ግድም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉ ይታወሳል።   የኢትዮጵያ ወዳጅ ነበሩ።

Äthiopien, Addis Abeba | Karl-Heinz Böhm Statue
ካርልሃይንዝ በም እና ባለቤታቸዉ ወይዘሮ አልማዝ በም ምስል Tobias Hase/dpa/picture alliance

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ