1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በ2012

ሰኞ፣ ጳጉሜን 2 2012

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከ15 ዓመታቸዉ ጀምሮ ያገለገሉትን ግን ደግሞ ከተራ ወታደርነት-እስከ ኮሎኔልነት፣ከመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪነት እስከ ዶክተርነት፣ከተራ ካድሬነት እስከ ሐገር መሪነት ያደረሳቸዉን ኢሕአዲግን በሌላ መተካታቸዉ ወትሮም ካኮረፉት የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት (ሕወሓት) ባለስልጣናት ጋር የገቡትን አተከራ ይበልጥ አንሮታል።

https://p.dw.com/p/3i7xM
Äthiopien Fernsehansprache Abiy Ahmed, Ministerpräsident
ምስል Ethiopian Broadcasting corporation

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በ2012

ኢትዮጵያ ለመሪዋ ጅምር የሠላም ጥረት  ማረጋገጪያ ኖቤልን እያስጠለቀች-ለግጭት፣ሁከት ቆሌዋ የመቶዎችን ሕይወት፣ የገበረችበት፤ ሺዎችን ያፈናቀለችበትን፣ገዢ ፓርቲዋ በመበልፀግ  ስም እየተሰየመላት፣ ዜጎችዋ በድሕነትና በሽታ የተደፈቁበትን፤ የመደመር  መርሕ እየተቀነቀነባት፣ ፖለቲከኞቿ  የዘር፣የኃይማኖት፣ክፍፍልን ያነገሱበትን፣ የለዉጥ አርበኞች በአሳሪና ታሳሪነት ጠላትነታቸዉን ያስመሰከሩበት፤  ሹመት አሳልፎ ሰጪዉ-የተሻሪበት፣ ሹመት ተቀባዩ-የሻረባት፣  ምርጫ ታልሞባት-ምርጫ ተራዝሞባት፣ ሰሜኗ  ምርጫ ተጠርቶባት፤ ምርጫ አራዛሚ-ከምርጫ አሳዳሚዎች ጋር የሚናጩበትን፣ በዉኃ ሰበብ ከጎረቤቶችዋ እየተናቆረች ዉኃ ሺዎችን ያፈናቀለበትን  ዘንድሮን-አምና ልትል ሶስት ቀን ቀራት።አርብ ዘንድሮ የምንለዉ ዓመት ከእስከ ሐሙሱ  ዘንድሮ ይለይ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

2012 የባተዉ፣ ከአዲስ አበባ እስከ አስመራ፣ ከዋሽግተን እስከ ፍራንክፈረት ኢትዮጵያዉያን፣ ኤርትራዉያን፣ አሜሪካ አዉሮጳዉያንን ባደባባይ ያሰለፈ፣ ያስጨፈረ፣ ያስዘመረዉ፣ ለድፍን አፍሪቃ አብነት እየተባለ የተወደሰዉ ፖለቲካዊ ለዉጥ በግጭት፣ሁከት፣ ግድያ መፈናቀል እንደደበዘዘ ነበር።

ይሁንና «ተስፋ የሚሞተዉ መጨረሻ ላይ ነዉ» እንዲሉ ጀርመኖች ሆኖ  አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ዓመቱን የተቀበለዉ ከርዕሠ-መስተዳድር እስከ ዩኒቨርስቲ ተማሪ፣ ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ አታማዦር  ሹም እስከ ተራ ወታደር ያጋደለዉ የስልጣን ሽኩቻ-ሴራ፣ ሺዎችን የገደለ፣ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለዉ የጎሳ ግጭት፣ሁከት ካለፈዉ ዓመት ጋር ያልፋል በሚል ተስፋና ምኞች ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ ዓሕመድም ለዝሕባቸዉ ከሚያንቆረቁሩት የሠላም፣የልማት፣ ዕድገት ተስፋ በተጨማሪ፣የቅርብም-የሩቅም ተቀናቃኞቻቸዉን ለመመንጠር እጅጌያቸዉን ሰቅስቀዉ መነሳታቸዉን፣ደንበር ገተር ለሚለዉ የለዉጥ ጉዞ ቀጥተኛ ጎዳና ለመቀየስ፣ለጋ ስልጣናቸዉን በምርጫ ለማጠናከር መወሳናቸዉን የያኔዉ አዲስ ዓመት ከመባቱ በፊት ነበር ያስታወቁት።

Äthiopien | Shashemene |  Angriffe und Zerstörungen von Immobilien
ምስል privat

 ይሁንና 2012 ዋዜማና መባቻ ላይ የተሰማዉ የጠቅላይ ሚንስር ዐብይ አሕመድ የምርጫም ሆነ  የፖለቲካ ቃል ለዓመት ከመንፈቅ በተሰጠዉ ተስፋ ላይ የችግኝ ተከላን ከማከሉ ባለፍ ሁከት፣ ግጭት፣ ሥርዓተ አልበኝነት ግራቀኝ የሚላጋትን ሐገር ቅጥ ለማስያዝ በተጨባጭ ርምጃዎች የታገዘ አልነበረም።

የፖለቲካ ተንታኝ ገረሱ ቱፋ እንደሚሉት ደግሞ የሐገሪቱ ፖለቲከኞች በተለይም ለለወጥ የተረባረቡት ወገኖች ከለዉጡ መጀመሪያ ጀምሮ ያወነካከሩትን የለዉጥ ሒደት በ2012ም ለማረቅ አልቻሉም።ወይም አልፈለጉም።

መስከረም ላይ ከወደ ሔሰን-ጀርመን የተሰማዉ ዜና ግን ጠቅላይ ሚንስትሩ ሠላም ለማስፈን ላደረጉና ለሚያደርጉት አስተዋፅኦ ከዉጪ  የሚሰጣቸዉ ድጋፍ፣ አድናቆትና ሽልማት በአዲሱም ዓመት መቀጠሉን ጠቋሚ ነበር።የሔሰን የሠላም ድርጅት ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድን ሸለመ።መስከረም ማብቂያ ኦስሎ ኖርዌ ላይ የተበሰረዉ ደግሞ ኢትዮጵያ ከዚያ በፊት አግኝተዉ የማታዉቀዉ ታላቅ ብስራት ነበር።

                                                  

«የኖርዌ የኖቤል ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ሠላም ለማስፈንና አለም አቀፍ ግንኙነትን ለማጠናከር፣ በተለይም ከኤርትራ ጋር የነበረዉን የድንበር ዉዝግብ ለማስወገድ ላደረጉት አስተዋፅኦ፣ የ2019ን ኖቤል የሰላም  ሽልማትን እንዲሸለሙ ወስኗል።

Norwegen l Verleihung des Friedensnobelpreis an Abiy Ahmed in Oslo
ምስል picture alliance/AP Photo/NTB scanpix/H. M. Larsen

በሪት ራይስ-አንደርሰን-የኖርዌ የሰላም ኮሚቴ ሊቀመንበር።ኦክቶበር 11፣ 2019።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ሽልማቱን ለጋ ስልጣናቸዉን ለመደገፍ እንደ ጠንካራ  ምርኩዝ፣ተቀናቃኞቻቸዉን  ለመሸንቆጥ እንደ  ለብላቢ ልምጭ ለመጠቀም ሽልማቱን እስኪቀበሉ አልጠበቁም።

አዲስ አበባ  የሚንተከተክባትን የስልጣን ሽኩቻ፣የፖለቲካ ሴራ፣ጠልፎ-የመጣል ደባ፣ የዘር፣ ሐይማኖት ግጭት ሁከትን  አምቃ የኖቤል ሽልማት ደጋፊ-ተቺዎችን ስታሟጋት መዘዘኛዉ ርምጃ ምርጊቱን ፈንቅሎ እምቋን አፈነዳባት።

ጥቅምትአጋማሽ ።የፀጥታ ኃይሎች የእዉቁን የኦሮሞ ፖለቲካ አቀንቃኝና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ OMN መስራችን ጀዋር መሐመድ መኖሪያ ቤትን መክበባቸዉ ሰበብ ሆኖ እራስዋ አዲስ አበባን ጨምሮ አብዛኛዉ  ኦሮሚያ፣ድሬዳዋና ሐረር በደም አፋሳሽ ግጭት፣ሁከት ግድያ ይታበጡ ያዙ።

በትንሽ ግምት  100 ያክል ሰዉ ተገደለ።ብዙ መቶዎች ቆሰሉ።ሺዎች ተፈናቀሉ።

ሕዳር ማብቂያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ታላቁን ሽልማት ለመቀበል ወደ ኦስሎ ከመሔዳቸዉ በፊት የገዢዉን ፓርቲ ኢሕዴግን ብልፅግና ወደተባለ ዉሑድ ፓርቲ መቀየራቸዉን አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከ15 ዓመታቸዉ ጀምሮ ያገለገሉትን ግን ደግሞ ከተራ ወታደርነት-እስከ ኮሎኔልነት፣ከመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪነት እስከ ዶክተርነት፣ከተራ ካድሬነት እስከ ሐገር መሪነት ያደረሳቸዉን ኢሕአዲግን በሌላ መተካታቸዉ ወትሮም ካኮረፉት የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት (ሕወሓት) ባለስልጣናት ጋር የገቡትን አተከራ ይበልጥ አንሮታል።

Unterstützer von Jawar Mohammed versammeln sich in Addis Abeba
ምስል AFP/Stringer

ከቅርብ ደጋፊ ምናልባትም ስልጣናቸዉን አሳልፈዉ ከሰጧቸዉ ከቀድሞዉ የኦሮሚያ ርዕሠ-መስተዳድር ከለማ መገርሳ ጋር መቀያያመቸዉ ይፋ የሆነዉም በብልፅግና ፓርቲ መመስረት ሰበብ ነበር።

ብልፅግና መመስረቱ በታወጀ በሳልስቱ ከደንቢዶሎ ወደየትዉልድ ቀያቸዉ ይጓዙ የነበሩ  17 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መታገታቸዉ ተሰማ።አብዛኞቹ ሴቶች ናቸዉ።ተማሪዎቹ እስካሁን ያሉበት አይታወቅም።

ተማሪዎቹ ከመታገታቸዉ በፊት ጀምሮ ሸኔ በተባለዉ የኦነግ ታጣቂ ኃይልና በመንግስት ጦር ኃይል መካከል ወለጋ ዉስጥ የሚደረገዉ ዉጊያ ማየሉ፣ደቡብ ኢትዮጵያ ዉስጥ በአስተዳደራዊ ስልጣን ሰበብ የሚካሔደዉ ዉዝግብ፣ የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት ሲታከልበት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የነበረዉ ተስፋና ምኞት ይበልጥ መነመነ።

በኮሮና ተሕዋሲ ሥርጭት ሰበብ ለነሐሴ ተይዞ የነበረዉ ብሔራዊ ምርጫ ለሌላ ጊዜ መራዘሙ ትግራይን የሚገዛዉ ሕወሓት ከፌደራሉ መንግስት ጋር ለገጠመዉ እንኪያ ሰላንቲያ ማጦዢያ ጥሩ ሰበብ ነበር የሆነዉ።ሕገ-መንግስት የሚያማዝዘዉ ዉዝግብ ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።የፌደሬሽን ምክር ቤት ትግራይ ዉስጥ ሊካሔድ ለታቀደዉ ምርጫ እዉቅና እንደማይሰጥ ባለፈዉ ቅዳሜ አስታዉቋል።ትግራይ ግን የክልል ምክር ቤት አባላትን ሮብ ለመምረጥ ዝግጅቷን አጠናቃለች።

Äthiopische Gemeinschaft USA
ምስል AFP/B. Bell

ከቀይ-ነጭ ሽብር መገዳደል ወዲሕ፣ ከሰኔ 2010 ጀምሮ ደም  የለመደችዉ አዲስ አበባ ዘንድሮ ሰኔም የዕዉቅ ድማፃዊና የፖለቲካ አንቃኝ ወጣትዋ ደም ፈሰሰባት።ሰኔ 22።ሐጫሉ ሁንዴሳ በሰዉ እጅ ተገደለ።ግድያዉ፣ አስደንጋጭ፣ አሳዛኝ፣ መዘዙ ደግሞ አሳሳቢ ነበር።

አንድ የኦሮሞ የፖለቲካ አቀንቃኝ እንዳሉት ግድያዉ በእጅጉ የኦሮሞን፣ በመጠኑም የኢትዮጵያን የእስኪያ ጊዜ ፖለቲካዊ ሒደትን የቀየረ ነዉ።የፖለቲካ ተንታኝ ገረሱ ቱፋም በከፊል ይስማማሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት ሐጫሉ በተገደለ ማግሥት ጀምሮ ከዕዉቁ የኦሮሞ የፖለቲካ አቀንቃኝ ጀዋር መሐመድ እስከ ባልደራስ ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ፣ ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር በቀለ ገርባ እስከ እዉቁ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌዉ ያሉ በርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ለቃቅሞ አስሯል።መገናኛ ዘዴዎችን ዘግቷል።እንቅስቃሴዎችን ገድቧል።

ግድያዉና የመንግስት እርምጃ ያስቆጣዉ ሕዝብ  በተለይም ወጣቱ በየስፍራዉ  አደባባይ ወጥቶ ይቃወም ያዘ።አጋጣሚ ይጠብቁ የሚመስሉ ወገኖች ደግሞ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል።ባቱን፣ሻሻመኔን፣ አርሲ ነገሌን እና ሌሎች ከተሞችን አንድደዋል።

ከአዲስ አበባ እስከ ጊኒር፣ ከአምቦ እስከ ጭሮ፣ ከሮቤ እስከ ድሬዳዋ የሚገኙ ከተሞችን ያዳረሰዉ ሑከት በሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን አፈናቅሏል።በቢሊዮን ብር የሚገመት ሐብት ንብረት አዉድሟል።ቁጣ፣ንዴት ብስጭቱ ባሕር ማዶ ተሻግሮም የዋሽግተን፣ለንደን፣ በርሊን አደባባዮችን የሰልፍ፣ ዉግዘት፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችን የግጭት ቁርቁስ መድረክ አድርጓቸዋል።እንደገና አቶ ገረሱ ቱፋ

Äthiopien Mekelle | Tsega Birhane - Tigray Wahlkomission
ምስል DW/M. Haileselassie

ሰዉ ያዉ መቼዉ ለቀመረዉ የጊዜ ስሌት ተገዢ ነዉና ኢትዮጵያዉያንም ሐሙስ እኩለ ሌት አሮጌዉን ዓመት ይሰናበታሉ።የፖለቲከኞቻቸዉ አሮጌ ሽኩቻ፣ ጠብ፣ ግጭት፣ ግድያስ ከሚያልፈዉ ዓመት ጋር ያልፍ ይሆን።እስኪ ቸር ያሰማን እንበል።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ