1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ፈተናዎችና አዲሱ መንግስት

ሰኞ፣ መስከረም 24 2014

የኢትዮጵያ ግማሽ አካል እየነፈረ አዲስ አበባ በጭፈራ-ድግስ ስትንበሸበሽ በርግጥ አዲሷ አይደለም።በ1966 ትግራይ፣ ወሎና ኦጋዴን ላይ ረሐብ የጠናበት ዜጋዋ አጥንት ሲቆጠር በንጉሷ 80ኛ ዓመት ልደት ስትፈነጥዝ ነበር።በ1977 አብዛኛዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በረሐብ ያለቀ ወገኑን ሲቆጠር አዲስ አበባ ለኢሠፓ ምሥረታ ዳንኪራ ሲረገጥባት ነበር።ዛሬም።

https://p.dw.com/p/41FLz
Äthiopien | Vereidigung Abiy Ahmed
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያን ዉስብስብ ችግሮችን የመፍታት መርሕ ----

041021

 

ኢትዮጵያ ከተወሳሰበ አሮጌ ችግሯ ጋር የ3ዓመት ከመንፈቅ ነባር ጠቅላይ ሚንስትሯ አዲስ መንግስት እንዲመሰርቱ በአዲሱ የስራ ዘመን በድጋሚ ተሾሙላት።የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ሳሕለወርቅ ዘዉዴ ዛሬ ለሕዝብና ለፌደሬሽን ምክር ቤቶች አባላት ባደረጉት ንግግር ለኢትዮጵያዉያን ዉቧ ፅጌረዳ ቅርብ ናት።ጦርነት፣የጎሳ ግጭት፣ የዘር ጥቃት፣የመብት ረገጣ፣ ረሐብ፣ ግዞት፣ የኑሮ ዉድነት፣ ሥርዓተ-አልበኝነት ከሚሸከመዉ በላይ ለጠናበት ኢትዮጵያዊ በርግጥ የበጎ ተስፋ ጭላንጭል ይፈነጥቅ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

አንዳዱ ችግር ለምዕተ-ዓመታት የደደረ፣ ሌላዉ ለ30ና 40 ዓመታት ሥር-የሰደደ፣ የተቀረዉ ባለፉት 3ና 4 ዓመታት ያጎነቆለ፣ ወራት ያስቆጠረም ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚገምተዉ እስካለፈዉ የካቲት ድረስ ብቻ 23.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ በሕይወት እንዲኖር አስቸኳይ ሰብአዊ ርዳታ ያስፈልገዋል።ከየካቲት እስካሁን በተቆጠረዉ 7 ወር ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ በኒ ሻንጉል ጉሙዝን ባወደመና በሚያወድመዉ ጦርነት፣ግጭት፣የጎሳ ጥቃት ከሰባት ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ተፈናቃይ፣ስደተኛና ተመፅዋች ሆኗል።

በየስፍራዉ የሞተ፣የቆሰለ፣ ሐብት ንብረቱ የጠፋበትን ሰዉም ሆነ የጠፋዉን ሐብት መጠን እስካሁን በትክክል የቆጠረዉ የለም።ሥራ አጥነት፣ የኑሮ ዉድነት፣ የመሥራትና የመንቀሳቀስ ነፃነት እጦት ቀፍድዶ የያዘዉ ሕዝብ፣ የአንበጣ መንጋ ሰብሉን ያወደመበት ገበሬ፣የኮሮና ወረርሽኝ የገደለና ያከሰረዉ ሰዉ ብዛትም በዉል አይታወቅም።የችግሩ ጥልቀት፣ዓይነትና ስብጥር ብዙ ነዉ።የፖለቲካ አስተያየት ሰጪ ሚስጥረ ስላሴ ግን ባንድ ቃል ይገልፁታል- «ፈታኝ» ብለዉ።

Äthiopien | PM Abiy Einweihungszeremonie in Addis Abeba
ምስል Solomon Muche/DW

ኢትዮጵያ የዉስጥ ችግሮቿ አልበቃ ያላት ይመስል ከሱዳን ጋር  በድንበር ግዛት ይገባኛል ሰበብ፣ከሱዳንና ግብፅ ጋር ደግሞ በግድብ ግንባታ ምክንያት እየተወዛገበች፣ መንግስት እንደሚለዉ የድንበር ግዛትዋም በሱዳኖች እንደተያዘባት ነዉ።

ባለፈዉ ጥቅምት ማብቂያ ትግራይ ላይ የተጫረዉ ጦርነት በሐገሪቱ ሕዝብ፤ ሐብትና ንብረት ላይ ካደረሰዉ ጥፋት በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ መንግስትን ከምዕራባዉያን መንግስታትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ከዲፕሎማሲ እሰጥ አገባ ዶሎታል።

መንበሩን ብራስልስ-ቤልጂግ ያደረገዉ የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል የበላይ ኃላፊ ያሬድ ሐብተማሪያም እንደሚሉት ኢትዮጵያን ተብትቦ የያዛትን ተደራራቢ፣ ዉስብስብና መጠነ-ሰፊ ችግርን እስከዛሬ የነበረዉ የሽግር ሥርዓት  ባያስወግድ እንኳ ማቃለል ነበረበት።ግን አልሆነም። ዉስብስቡ  ችግር ይበልጥ ተቆላለፈ እንጂ አልቀነሰም።በዚሕም ምክንያት በልማዱ «የሽግግር» ይባል የነበረዉ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ መንግሥት መፍታት ወይም ማቃለል የነበረበት ችግር ዛሬ እንዳዲስ ለተዋቀረዉ መንግሥት ዕዳ አትርፏል-አቶ ያሬድ እንደሚሉት።

                                                

የራሱን ዕዳ-ለራሱ ያቆየ መንግስት።ፕሬዝደንት ሳሕለወርቅም ባለፉት የሽግግር ዓመታት የተከሰቱ ችግሮችን ጠቃቅሰዋል።ዕዳ።እንደገና አቶ ያሬድ።ፕሬዝደንት ሳሕለ ወርቅ ችግሮቹን ጠቃቀሱ እንጂ በንግግር የከፈቱት ምክር ቤት ወይም የሚመሰረተዉ አዲስ መንግስት መስጠት የሚገባዉን መፍትሔ አልጠቆሙም።የፖለቲካ አስተያየት ሰጪ ሚስጥረ ስላሴ «ፈታኝ» ያሉት ችግር አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚሻ ያምናሉ።ከየት እንደሚጀመር ግን አያዉቁም።

 አቶ ያሬድ ከጦርነት-በአዲስ አበቦች አገላለፅ እስከ «የቀሚስ ዉስጥ ረሐብ»፣ ከዲፕሎማሲ እሰጥ አገባ እስከ ሥርዓተ-አልበኝነት ለደረሰዉ «ዕዳ» ላሉት ችግር አዲሱ መንግስት አስቸኳይ መፍትሔ የሚሰጥ፣ ሁሉንም የሚያሳትፍ መርሕ ወይም ፖሊስ መከተል አለበት።

                                             

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ዛሬ አብዮት ወይም መስቀል አደባባይ በተከበረዉ በዓለ ሲመታቸዉ ላይ ያደረጉት ንግግር ለዚሕ ዝግጅት አልደረሰም።ይሁንና ንግግሩ ወይም መልዕክቱ ምንም ሆነ ምን አዲሱ መንግስት አሮጌ ችግሮቹን ለማቃለል በገቢር የመጣር ቁርጠኝነት እንጂ የዲስኩር ጋጋታ፣ አማላይ ቃላትና ተስፋ አስፈሪዉን ዕዉነት አይለዉጠዉም።

Äthiopien | PM Abiy Einweihungszeremonie in Addis Abeba
ምስል Solomon Muche/DW

ኢትዮጵያ ባለፈዉ 3 ዓመታት ከመንፈቅ በተጓዘችበት የቁልቁለት ጎዳና  ለመቀጠል ሐገሪቱም ሕዝቡም አቅሙ ያላቸዉ አይመስልም።ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዉያን ሁሉ እንጂ የገዢዎችዋ የግል ርስት ጉልት አይደለችምም።አቶ ሚስጥረ አዲሱ መንግስት «የሽግግር» ከሚባለዉ ጊዜ የተሻለ ሥልጣንና መብት ያለዉ፣ በሕዝብ የተመረጠ በመሆኑ ሕዝብን የሚከብርና ጥያቄዎቹን የሚመልስ  ይሆናል የሚል ተስፋ አላቸዉ።

መጨረሻ የሚሞተዉ ተስፋ ነዉ-እንዲሉ አቶ ያሬድም በጎዉን መመኘቱን-ይመርጣሉ።ያዉ  ተስፋ ነዉ።የሩቅ ተስፋ።አዲስ አበባ ግን ከሩቅ ተስፋዋ በላይ አሸብርቃለች።በጥቂት ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ የደረሰና የሚደርሰዉን ጥፋት፣ረሐብ፣ ስደትና መፈናቀል ዘንግታ፣ የመሪዎችዋን ሹመት ለማክበር ዘፈን፣ መዝሙር ታስተጋባለች።የተዋቡ ወይዛዝርት፣መኳንትዋን፣ ታላላቅ እንግዶችዋን ለማስተናገድ ጠብ ርግፍ ትላለች። የጦር ኃይል ሰልፍ፣ ትርዒት የሙዚቃ ድግስ ይንቆረቆርበታል።

Äthiopien | Addis Abeba
ምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ ግማሽ አካል እየነፈረ አዲስ አበባ በጭፈራ-ድግስ ስትንበሸበሽ በርግጥ አዲሷ አይደለም።በ1966 ትግራይ፣ ወሎና ኦጋዴን ላይ ረሐብ የጠናበት ዜጋዋ አጥንት ሲቆጠር በንጉሷ 80ኛ ዓመት ልደት ስትፈነጥዝ ነበር።በ1977 አብዛኛዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በረሐብ ያለቀ ወገኑን ሲቆጠር አዲስ አበባ ለኢሠፓ ምሥረታ ዳንኪራ ሲረገጥባት ነበር።ዛሬም።አቶ ያሬድ።አቶ ሚስጥረ ታሪክ እራሱን ይደግማል ይላሉ።የሆነ ሆኖ ፅጌረዳዋ ስንት ኪሎ ሜትር ትርቅ ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ