1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ጦር ላሊበላን መልሶ ተቆጣጠረ

ረቡዕ፣ ኅዳር 22 2014

ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ እና ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዋም በዛሬው ዕለት ማምሻውን በተባበሩት የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሽያ እና ፋኖ ቁጥጥር ስር መግባታቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/43iFy
Äthiopien Lalibela | Orthodoxe unterirdische monolithische Kirche Bete Giyorgis
ምስል picture alliance / Sergi Reboredo

ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ እና ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዋም ዛሬ ማምሻውን በተባበሩት የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሽያ እና ፋኖ ቁጥጥር ስር መግባታቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ። መስሪያ ቤቱ ዛሬ ማምሻውን በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙባትን የላሊበላ ከተማና የአውሮፕላን ማረፊያዋን መልሶ የተቆጣጠረው የኢትዮጵያ ጦር ፣ የላሊበላ አካባቢን በማጽዳት የሰቆጣ ከተማን ለመቆጣጠር ወደዚያው ማምራቱን አስታውቋል። ሮይተርስ የጠቀሳቸው በአንድ የላሊበላ መንደር የሚገኙ ነዋሪ የህወሓት ሀይሎች መንደራቸውን ለቀው መውጣታቸውን ተናግረዋል። ከላሊበላ በስተደቡብ ምዕራብ 25 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ባለችው «ግራኝ አምባ» የሚገኙት እኚሁ ነዋሪ እንዳሉት የትግራይ ተዋጊዎች መንደራቸውን ጥለው የወጡት ትናንት ነው። ሲወጡም «የዐቢይ ወታደሮች እየመጡ ነው።» ብለው ነግረዋቸዋል። ነዋሪዋ እንደተናገሩት የህወሓት ኃይሎች ዛሬ ጠዋት ወደ ላሊበላ አቅጣጫ ሲሸሹ አይተዋል። ከላሊበላ የሚመጡ ነዋሪዎችም ተዋጊዎቹ ላሊበላን ጥለው መሄዳቸውን ነግረዋቸዋል። ዛሬ ጠዋት የአማራ ልዩ ኃይሎች መንደራቸው ገብተው እናንተን ለመጠበቅ ነው የመጣነው ሲሉ  አጽናንተውናልም ብለዋል ነዋሪዋ። 

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ