1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ጉዳይ በአውሮጳ ፓርላማ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 2 2009

በውይይቱ ላይ የፓርላማ አባላት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግር አለበት ባሉት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ኮሚሽኑ ለዘብተኛ አቋም ይከተላል ሲሉ ወቅሰዋል ።

https://p.dw.com/p/2RAO7
Brüssel Europäische Kommission Außenansicht
ምስል picture-alliance/dpa/D. Kalker

M M T/ Beri Brussels(Exchange of views on Ethiopia at the EP 2016 - MP3-Stereo

በአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት የልማት ኮሚቴ እና የሰብአዊ መብቶች ንዑስ ኮሚቴ አባላት ዛሬ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል። በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ያወጀዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተም ተሳታፊዎች ንግግር አሰምተዋል።  የፓርላማ አባላት፣ የኮሚሽኑ እና የልዩ ልዩ ድርጅቶች ተወካዮች በተካፈሉበት በዚሁ ውይይት ላይ በብራሰልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተወካዮችም ተገኝተዋል ።በውይይቱ ላይ የፓርላማ አባላት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግር አለበት ባሉት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ኮሚሽኑ ለዘብተኛ አቋም ይከተላል ሲሉ ወቅሰዋል ። የአውሮጳ ምክር ቤት አባል የኾኑት ወ/ሮ አና ጎሜሽ በኢሬቻ በአል ላይ የደረሰዉን ጭፍጨፋን ጨምሮ በሀገሪቱ የሚከናወነውን ጭቆና የሚከታተል ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ሊኖር ይገባል ብለዋል። ኢንተርኔትን እና ሚዲያን የሚገድበው  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳም ጠይቀዋል። የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጥሪ በማስተላለፍ እስሩ አሁንም እንደቀጠለ ነው ያሉት ወ/ሮ አና ጎሜሽ የአውሮጳ ኅብረት ጠንካራ ርምጃ ባለመውሰዱ ወቅሰዋል። የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የኢትዮጵያ ጉብኝትንም አጥብቀው ተችተዋል።
«ሌላው ቢቀር ትናንት ወ/ሮ ሜርክል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጎም ሀገሪቱን መጎብኘታቸው የሁላችንም የጋራ ሐፍረት ነው።»
በስብሰባው ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክለው የተናገሩት በቤልጂግ የኢትዮጵያ  አምባሳደር የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ አማካሪ አቶ ዮሐንስ አብራኃ በበኩላቸው ከ80 ብሔሮች በላይ ባላት ሀገር ዲሞክራሲን ተግባራዊ ከማድረግ ውጪ ሌላ የተሻለ አማራጭ የለንም ሲሉ ተናግረዋል።
«ክብርት ሊቀ መንበር፣ እንዲሁም ክቡራን  እኛ ዲሞክራሲን ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ እያደረግን ነው  ብለን እናምናለን። ይኼን የምናደርገውም ሌሎችን ለማስደሰት ሳይሆን፤ የምናደርገው ሕዝባችን እና ሀገራችን ስለሚፈልጉት ነው።»

EU Parlamentarier - Ana Maria Gomes
ወ/ሮ አና ጎሜሽምስል CC-BY-Security & Defence Agenda

አምባሳደሩ በስብሰባው ላይ በኦሮምያ የዘረኝነት ችግር አለ መባሉን እንዳስተባበሉ ውይይቱን የተከታተለው የብራሰልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ ዘግቧል ።

ገበያው ንጉሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ