1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ነገር

ዓርብ፣ ሐምሌ 13 2010

የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ ቢያንስ ከአንድ ዶላር ጀምሮ ገቢ የሚያደርጉባቸውን የባንክ ቁጥሮች አሳውቋል። የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ የሚያስተዳድረው አካል ማንነት ሆነ ሥራ ላይ የሚውልባቸው ዘርፎች አልተለዩም ። 

https://p.dw.com/p/31qF2
Abiy Ahmed Äthiopien
ምስል Reuters/T. Negeri

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ነገር

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ በጠየቁት መሠረት መንግሥታቸው በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የልማት ሥራዎችን የሚደግፉበት የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ መቋቋሙን አስታውቋል። በትናንትናው ዕለት የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ አሕመድ ሽዴ "ሐገራዊ ለውጡን እና የሽግግር ሒደቱን ለመደገፍ የሚያስችል የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ተቋቁሟል። ይኸ ትረስት ፈንድም የተቋቋመው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ነው" ብለዋል።

 አዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ጊና "የዲያስፖራውን ሥራ ለማቀናጀት እና የልገሳውን ገንዘብ ለማሰባሰብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ የሚል ሒሳብ" መከፈቱን ገልጸዋል።  

አቶ አሕመድ ሽዴም ይሁኑ አቶ ባጫ ጊና በጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ተማፅኖ የተቋቋመው የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ማን እንደሚያስተዳድረው፣ ገንዘቡ ለየትኞቹ የልማት ሥራዎች በየትኞቹ አካባቢዎች ጥቅም ላይ እንደሚውል ማብራሪያ አልሰጡም።

ዴሎይት የተሰኘው የኦዲት እና ማማከር ሥራ ኩባንያ የምስራቅ አፍሪቃ አገሮች ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ሲሳይ "ዓላማው መቀመጥ መቻል አለበት። በመጀመሪያ ደረጃ ፈንዱ ለምንድነው የሚውለው? እንዴት ነው የምንጠቀምበት? እንዴት ነው የሚሰበሰበው የሚያስተባብረው አካል ማነው?" የሚሉ ጥያቄዎች መመለስ እንደነበረባቸው ይናገራሉ። አቶ ቴዎድሮስ እንደሚሉት የገንዘብ ሒሳቡን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጣቸው ባለሙያዎች ሊኖሩ ይገባ ነበር። 

ጠቅላይ ምኒስትሩ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ጥያቄውን ሲያቀርቡ በቀን ቢያንስ አንድ ዶላር ለመስጠት ፈቃደኛ ከሆኑ ሰዎች የሚሰበሰበው ገንዘብ "በመንግሥት በጀት አይገባም። የራሱ ቦርድ ይቋቋምለታል" ብለው ነበር። ቦርዱ ለመቋቋሙ እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። 

የጠቅላይ ምኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ፍጹም አረጋ በትዊተር ገፃቸው ባጋሩት ደብዳቤ በንግድ ባንክ ከተከፈተው የሒሳብ ቁጥር በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ይፋ በሚያደርገው ድረ-ገፅ ጭምር የገንዘብ ድጋፉን ለማሰባሰብ መታቀዱን ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በትብብር ይሰራሉ በተባሉ 20 ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊዎች ጭምር እገዛውን ማድረግ ይቻላል።

አቶ ቴዎድሮስ የጠቅላይ ምኒስትሩ ሐሳብ በአግባቡ ገቢራዊ ከሆነ ከፍ ያለ ፋይዳ የሚኖራቸው ሥራዎች ለመከወን እገዛ እንደሚኖረው ያምናሉ። ባለሙያው እንደሚሉት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ "የሚያስተዳድር፣ ተጠያቂ የሆነ ተቋም" ያስፈልገዋል። አቶ ቴዎድሮስ የባንክ ቁጥር ይፋ ከመሆኑ በፊት "አወቃቀሩ ይኸ ነው። ተጠያቂነቱ ለዚህ ነው፤ ገንዘብ ስታስገቡ ደግሞ ይኼ ኩባንያ ይኼን ያደርጋል" የሚለው ጉዳይ ሊቀድም ይገባ እንደነበር ገልጸዋል። 

እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ