1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበባት ባለሙያዎች ማሕበር እንቅስቃሴ በጀርመን

ሐሙስ፣ ኅዳር 2 2014

ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ የወረዳ 17 ኪነት ቡድን ውስጥ አባልና የመድረክ አስተዋዋቂ በነበረበት ወቅት የተፈጠረ ክስተት ነው:: በኪነት ቡድኑ ተወዳጅ የወላይትኛ ሙዚቃ የነበረው ድምጽዋዊ ዝግጅት በሚያቀርቡበት ዕለት እክል ገጥሞት ቀረ::

https://p.dw.com/p/42tSe
Deutschland Auszeichnung für Mohamud Ahmed
ምስል basPhotos/Biruk A. Seifegebreal

የኢትዮጵያ የኪነጥበባት ባለሙያዎች ማሕበር ሊቀመንበር ተፈሪ ፈቃደ

ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ የወረዳ 17 ኪነት ቡድን ውስጥ አባልና የመድረክ አስተዋዋቂ በነበረበት ወቅት የተፈጠረ ክስተት ነው:: በኪነት ቡድኑ ተወዳጅ የወላይትኛ ሙዚቃ የነበረው ድምጽዋዊ ዝግጅት በሚያቀርቡበት ዕለት እክል ገጥሞት ቀረ:: እናም ግጥሙን በተወሰነ ደረጃ ስለሚያውቀው እሱን ተክቶ ያን በወቅቱ በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅ የነበረ ዜማ የራሱን ፈጠራ አክሎበት በማሳየት ታዳሚውን የማስደመም ጉጉት አደረበት:: እናም ሙዚቀኞቹ ሙዚቃውን መጫወት ሲጀምሩ በዛ የምሽት ዝግጅት ማንም ሳያየው ተደብቆ የነብር ቆዳ ለብሶና ነብር መስሎ የመድረኩ ጣራ ላይ ወጥቶ ፍርሃትም ደስታም በተቀላቀሉበት ድብልቅልቅ ስሜት ተውጦ ሽቅብ ወደመሬት ዘለለ :: ነገሩ እብደትም አስገራሚም ይመስላል፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኪነጥበባት ባለሙያዎች ማህበር ሃሳብ ጠንሳሽና ከመስራቾቹም መካከል ዋናው የሆነው የዛሬው እንግዳችን ግን ይህን በተግባር አድርጎታል:: መጠነኛ የእግር ጉዳት ያስተናገደበትን ይህን ድርጊት እሱም ሆነ የሙያ አጋሮቹ ዛሬ መለስ ብለው ሲያስታውሱት በእጅጉ ይደመማሉ::  

Deutschland Auszeichnung für Mohamud Ahmed
ምስል basPhotos/Biruk A. Seifegebreal

ከሶስት አስርተ ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ የቴአትር መድረኮች ይታደም የነበረ ጥበብ አፍቃሪ በቅፅል ስሙ "ማይክል ጃክሰን" በሚል ስም ይጠራን የነበረ አንድ ወጣት ማስታወስ አይከብደውም:: ወቅቱ ታዋቂው የአሜሪካ የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጃክሰን "ትሪለር" የተሰኘውን የሙዚቃ አልበሙ ያወጣበት ሲሆን ፤ የዛሬው እንግዳችን ተፈሪ ፈቃደም በተለይም የወጣቶችን ቀልብ በእጅጉ የሳበው የዚህን ዕውቅ ከያኒ የመድረክ አልባሳት፣ ፍሪዝ የፀጉር ስታየልና ድምጻዊው ብሬክ ዳንስ በመባል ከያኒው ይታወቅበት የነበረውን ውዝዋዜ አስመስሎ በተለያዩ መድረኮች ላይ በማቅረብ አድናቆትና ዕውቅና ሊያተርፍ ችሏል:: በወታደራዊው የደርግ አስተዳደር ከየቤቱና ከየጎዳናው ወጣቶች ለውትድርና በሚታፈሱበት ዘመን አዲስ አበባ ተወልዶ ባደገበት ቦሌ መድኃኔ ዓለም አካባቢ የወረዳ 17 ኪነት ቡድንን በመቀላቀል በዳንስ፣ በሙዚቃና በመድረክ አስተዋዋቂነት ሁለገብ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረው ተፈሪ አፍታም ሳይቆይ ችሎታውን በሚገባ የተገነዘቡ የኪነጥበብ ባለሙያ ወዳጆቹ በደቡብ ዕዝ የሙዚቃ ኦርኬስትራ ከእነ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ሕይወት መኮንንና ሌሎችም ነባር ድምጻውያን ጋር በትርፍ ጊዜው አገልግሎት እንዲሰጥ የዕድል በር እንደከፈቱለት ይናገራል::በተለይም የማይክል ጃክሰን "ብሬክ" እና "ሙን ወክ" የተሰኙት ዘመናዊና ምትሃታዊ ረቂቅ የዲስኮ ዳንስ ወዝዋዜ ክህሎቱ ብሔራዊ ቴአትርን ጨምሮ በተለያዩ ትላልቅ ቴአትር ቤቶች ጭምር በትዕይንተና ዝክረ ጥበባት ዝግጅቶች በተጋባዥነት ስራውን እንዲያቀርብ ረድቶታል::

Deutschland Auszeichnung für Mohamud Ahmed
ምስል basPhotos/Biruk A. Seifegebreal

በቦሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ከቀሰመው መደበኛ የቀለም ትምህርቱ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ የሩሲያ የባህል ማዕከል የሙያ ስልጠና ሲከታተል የቆየው ተፈሪ፤ የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ግዛት አካል በነበረችው ዩክሬይን በቴአትር ጥበባት ዘርፍ ነጻ የትምህርት ዕድል ስኮላርሽፕ በማግኘቱ በባህል ጥናትና ምርምር ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ሙያ ትምህርቱን ሲከታተል ከቆየ በኋላ በመሃሉ በቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ በሩሲያ የርዕዮተ ዓለም ለውጥ መከሰቱን ተከትሎ ወደ ጀርመን በማቅናት በትራንስፖርት አገልግሎት ሙያ ተሰማርቶ ኑሮውን ዳርምሽታት በምትባለው ከተማ መሰረተ:: ጥበብ ከነፍሱ ጋር የተዋሃደችው ባለሙያው ጀርመን ከመጣ በኋላም ሃገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ መጽሔቶች ልዩ ልዩ መጣጥፎችን ሲያቀርብ  ቆይቷል:: በኋላም በጀርመን ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችንና የጥበብ ባለሙያዎችን በማስተባበር ከኪነጥበብ ሙያው ላለመራቅ አሜሪካ ውስጥ በኢትዮጵያውያን በጋዜጠኞች ለተመሰረተው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ በነጻ ዘገባዎችን በትርፍ ጊዜ እያጠናቀሩ መላክ ጀመሩ:: የአንጋፋውና ተወዳጁ ድምጻዊ ዶክተር ጥላሁን ገሰሰ ሕልፈት ሕይወት ተፈሪን አንድ ታላቅ ተግባር እንዲከውን ምክንያት የሆነ አጋጣሚን ፈጠረ:: ለአርቲስቱ ሥርዓተ ቀብርና ዜና ዘገባ ከዓመታት የውጭ ኑሮ ቆይታ በኋላ ከጀርመን ወደ አዲስ አበባ ያቀናው ተፈሪ ለኢትዮጵያ የኪነጥበብ እድገት ፈርጥ የሆኑ አብዛኛዎቹ ሥመጥርና አንጋፋ ባለሙያዎች እንዲሁም ወዳጆቹ በጉስቁልና ሕይወት ውስጥ ሆነው ማየቱ ክፉኛ ልቡን ሰበረው::  በቁም ያሉትና በየመድረኩ ሲጨበጨብላቸው የኖሩት በጡረታና በተለያዩ ምክንያቶች ከሙያው ከራቁ በኋላ በኢኮኖሚ ችግርና በኑሮ አለመሳካት አስከፊ ሁኔታ ውስጥ መገኘታቸው ብቻም ሳይሆን ፣ በጤና ዕክል ላይ የሚገኙትም እንደ የክራሯ ንግስት አስናቀች ወርቁ፣ ዕውቁ የዜማና ድርሰት አቀናባሪ ኮሎኔል ሰሃሌ ደጋጎ፣ ብዙ ተስፋ የተጣለበት አርቲስት አብርሃም አስመላሽ፣  የቀድሞው የምድር ጦር የሙዚቃ ኦርኬስትራ የመድረክ አስተዋዋቂና ድምጻዊ ታምራት ሞላ የሚታወቅባቸውን "ስንዋደድ"፣   "ታምሜ ተኝቼ" እና አያሌ የሙዚቃ ግጥሞችን በመድረስ ስሙ ዛሬም ድረስ የሚወሳው አርቲስት አመሃ ተወዳጅ ሌሎችም አያሌ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በእርጅና፣  በጤና ዕክልና በተገቢ የህክምና ክትትል ዕጦት አስታዋሽ ማጣታቸው በሕይወት የተለዩትም እንደነ አሰፋ አባተ፣  ሜሪ አርምዴ፣  ብዙነሽ በቀለና ሽሽግ ቸኮልን የመሳሰሉት ዘመን ተሻግሮ ትውልድ በረቂቅ የጥበብ ትሩፋታቸው የሚዘክራቸው የታሪክና የሀገር ባለውለታዎች መካነ መቃብር በአያያዝ ጉድለት አስታዋሽ አጥቶ ጠፍቶ ማየቱ ለአንዳንዶቹም የሚታወሱበት እንኳ አለመቆሙ እጅግ ስላሳዘነው ወደ ጀርመን ከመመለሱ በፊት ለመላው የኪነጥበብ ባለሙያ የሚጠቅም አንድ በጎ ነገር ከውኖና መሰረት ጥሎ ለመመለስ ለኅሊናው ቃል ገባ::  

ይህን ሰዓልያንን፣  ደራስያንን፣  ቀራጽያንን፣  ሙዚቀኞችን ፣  የመድረክ ከያኒዎችን እና ሌሎችንም የኪነጥበብ ባለሙያዎች በቁም የሚረዳ, ታሪካቸውን ለተተኪው ትውልድ የሚያስተላልፍ እንዲሁም የጤና እክልና የፋይናንስ ችግር ለገጠማቸው የሚረዳ ብሔራዊ የሙያ ማህበር ለመመስረትም በብሔራዊ ቴአትር የሚሰሩ አንጋፋ አርቲስቶችና ሌሎችም የኪነጥበብ ባለሙያዎች የሃሳብ ድጋፍ በማድረግ የመጀመሪያው መስራች ስብሰባ ተደርጎ ማህበሩ ተመሰረተ::በዚህ መልኩ በተፈሪ ሃሳብ አመንጭነትና በሌሎችም የሙያው አጋሮቹ ትብብር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ለመርዳት በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ማህበር ምስረታ ዕውን ከሆነ በኋላም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ድጋፍ ለማስተባበርና ለማጠናከር እንዲረዳ በዶክተር ሉዑል አሳፋ-ወሰን አስራተካሳ የቦርድ የበላይ ጠባቂነት በጀርመንም እንዲሁ ተመሳሳይ  ድጋፍ ሰጪ ማሕበር በማቋቋም ዛሬም ድረስ በአስተባባሪነት የበጎ አድራጎት ግልጋሎት በመስጠት ላይ ይገኛል:: ባለፉት አያሌ ዓመታትም ማህበሩ ከ 39 በላይ ድምጻውያንን እና የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ከኢትዮጵያና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጀርመን ድረስ በመጋበዝ ስራዎቻቸውን እንዲያቀርቡና ከመድረክ የሚገኘውንም ገቢ እንዲጠቀሙ በማድረግ ድጋፍ ሲሰጥ ቆይቷል:: በየዓመቱ በሚያዘጋጀው የአንጋፋና ስመጥር ከያኒያን የምስጋናና የዕቅና መርሃግብርም ሽልማቶችን እንዲሁም ከመድረኩ የሚገኘውን ገቢ ለሙያተኞቹ በማበርከት የሞራልና መጠኛ የፋይናንስ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ለማወቅ ችለናል:: በማህበሩ ዕውቅናና ሽልማት ከተበረከተላቸው ሙያተኞች መካከልም ስመ ጥሩ ፀሃፊ ተውኔትና ገጣሚ ፀጋዬ ገብረ መድህን፣  የክራሯ ንግሥት አስናቀች ወርቁ፣  አርቲስት አመሃ ተወዳጅ፣  ታዋቂዋ ፀሃፊ ተውኔት፣ ገጣሚና ከያኒ አርቲስት ዓለምፀሃይ ወዳጆ፣ ዶክተር ማህሙድ አሕመድና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው:: 

Äthiopien Teferi Fekade
ምስል Teferi Fekade

በፋይናንስ ችግርና በዘመናዊ ሕክም ዕጦት ሲሰቃዩ የነበሩ አያሌ ኢርቲስቶችም ጀርመን ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በመነጋገርና ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በማዘጋጀት የህክምና ወጪያቸውን ሸፍኖ በጀርመንና ሃገር ውስጥ ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ ለሌሎችም ወገኖች አርአያ ሆኖ የሚጠቀስ የበጎ አድራጎት ተግባር እየከወነ ይገኛል:: ከእነዚህም መካከል ታዋቂዋ አርቲስት አስናቀች ወርቁ፣ የመድረክ ፈርጥ የሚባለው ተዋናይ ጀምበሬ በላይ፣ አንጋፋው አርቲስት አመሃ ተወዳጅ፣ አሰለፈች አሽኔ፣ አብርሃም አስመላሽና ባዩሽ ዓለማየሁ  ሌሎችም ከማህበሩ ድጋፍ ያገኙ ሲሆን በቅርቡም  እስከ መቶ ሺህ ዩሮ የሕክምና ወጪን በሚጠይቅ ከባድ ህመም ይሰቃ የነበረ አንድ አርቲስትን ለመርዳት ከ 35ሺህ ዩሮ ክፍያ በተጠየቀበት ወቅት በጀርመን ነዋሪ የሆኑ ዶክተር ስንታየሁና ዶክተር ፀጋዬ የተባሉ ሃገር ወዳዶችን በማስተባበር የሕክምናው ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ በአሁኑ ወቅት ፈውስ አግኝቶ ወደ ሃገር መመለሱን የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ተፈሪ ገልፆልናል::  ባለሙያዎቹ ለሃገር ከሚያበረክቱት የላቀ አስተዋጽዖ አንጻር በቂ ክፍያ እያገኙ አይደሉም የሚለው ተፈሪ ከፍተኛ የጤና ዕክል የገጠማቸውና ከሃገር ውጭ ወጥተው መታከም የማይችሉትም በአንደኛ ማዕረግ ተገቢው ክትትልና ነጻ የሕክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ከጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ጋር ስምምነት መደረጉን ገልፆልናል:: ድምፀ መረዋዋ አስናቀች ወርቁ ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየቷ በፊት ማሕበሩ ላበረከተላት በጎ ድጋፍ ከነበሯት ሶስት ክራሮች አንዷን በስጦታ እንዳበረከተችለት የገለፀልን ተፈሪ እንዲህ ዓይነት የአንጋፋ አርቲስቶች ቅርሶችና ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች በስርዓት ተይዘውና ተመዝግበው ለጥናትና ለምርምር ስራ ለተተኪው ትውልድ የሚተላለፉበት አንድ ማዕከል ወይም ሙዝየም የማቋቋም ውጥን እንዳለው ተናግሯል:: ከሶስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በተካሄደው ለውጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ከዲያስፖራው ጋር ለመምከር ፍራንክፈርት በመጡበት ወቅትም ተፈሪ በግሉ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ዜጎች የተሳተፉበትን የማርሽ ባንድ የሙዚቃ ዝግጅት በማቅረብ ለመርሃግብሩ ልዩ ድምቀትን መስጠቱን ብዙዎች ያስታውሳሉ:: ማህበሩ ከአባላቱ የሚሰበስበው አምስት ዩሮ ወሃዊ መዋጮ የቀየሳቸውን መጠነ ሰፊ ዕቅዶችና የበጎ ስራ እንቅስቃሴዎች ለማሳካት በቂ ባለመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የሙዚቃ መዝናኛ ዝግጅቶችን፣  የፋሽን ሾው ትሪቶችን፣  የቴአትር ፣ የግጥምና የሥነጽሁፍ መርሃግብሮችን በማዘጋጀት ባለሙያዎችን ለመርዳት ጥረት አድርጓል:: በማሕበሩ ድጋፍ በሃገር ውስጥና በጀርመን የሕክምና ድጋፍ ካገኙት መካከል አርቲስት አመሃ ተወዳጅ በአንድ ወቅት ማህበሩን በተመለከተ ተጠይቆ በሰጠው ማብራሪያ "ወድቀን ከተረሳንበት አንስቶ በማሳከም በሕይወት እንድንኖር አድርጎናል" ሲል ምስጋናውን በማቅረብ እንዲህ ዓይነቱ የበጎ ተግባር ስራ እንዲጠናከርም ጠይቋል::አምና ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውና ከ 40 ዓመታት በላይ በመድረክ ሙያ ያገለገለው, ከ 60 በላይ ተውኔቶችን በሃገር ፍቅርና ብሔራዊ ቴአትር ቤቶች እንዲሁም በሌሎችም መድረኮች እንደተወነ የሚነገርለት ከዚህ ሌላ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የራድዮና የቴሌቪዥን ድራማዎችን በመተወን ሙያዊ ክህሎቱን ያስመሰከረው ታዋቂው የመድረክ ከያኒ ጀምበሬ በላይም ከሕልፈተ ሕይወቱ በፊት በጀርመን ሕክምና እንዲከታተሉ ከተደረጉ የጥበብ ሰዎች አንዱ እንደነበር በመግለጽ "ዕድሜውን ሙሉ ሕዝብና ሃገሩን አገልግሎ" በማረፊያ ዕድሜው የሰው እጅ ተመልካች መሆኑ እንዳሳዘነው በወዳጆቹ ፊት በለቅሶ ታጅቦ ያስተላለፈው መልዕክት እንደነ ተፈሪ ያሉ የበጎ አድራጎት ስራዎች እንዲጠናከሩ የመንግሥት , የመገናኛ ብዙኅን እና የማህበረሰቡ ድጋፍና ሚና እጅግ ወሳኝ መሆኑን አመላካች ጥሩ የማንቂያ ደውል ነው::

Deutschland Auszeichnung für Mohamud Ahmed
ምስል basPhotos/Biruk A. Seifegebreal

በጀርመን የኢትዮጵያ የኪነጥበባት ባለሙያዎች ማሕበር ሊቀመንበር ተፈሪ ፈቃደ እንደነ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴን የመሳሰሉ ለኢትዮጵያ ረቂቅ የቅኔ የሥነ ጥበብና ታሪክ ጉልህ ሚና የነበራቸው አንጋፋ ሙያተኞች የሚዘከሩበት ማስታወሻ ለማኖር ያደረገው ጥረት በተደጋጋሚ ከፍተኛ ውጣ ወረድ እና እክል እንደጋጠመው በሃዘን ይገልጻል:: ከበርካታ ዓመታት በፊት የተመሰረተው ማህበራቸው እንደነ ባለሙያዎችን ለመርዳት አመርቂም ባይሆን የአቅሙን ጥረት እያደረገ ቢገኝም አሁንም ድረስ በአዲስ አበባ የራሱን ቢሮ እንኳን ማግኘት አለመቻሉ የእንቅስቃሴውን አድማስ ለማስፋት ሌላው እክል መሆኑንም ለዶይቼ ቨለ ገልጿል:: በቅርቡ አንጋፋዎቹን አርቲስቶች አብራር አብዶና ፋንቱ ማንዶዬ ወደ ጀርመን በመጋበዝ የተለዩ ድጋፍ ሰጪ ዝግጅቶችን ለማቅረብ መሰናዶውን እያጠናቀቀ የሚገኘው ማህበሩ፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መሰረታዊ የቢሮና ተዛማጅ ችግሮቹን በዘለቄታው ለመቅረፍ ጥረት እንደሚያደርግና በአውሮጳ አቀፍ ደርጃ የማህበሩን አድማስ ለማስፋት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ለማወቅ ችለናል::


እንዳልካቸው ፈቃደ

አዜብ ታደሰ