1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 14 2014

በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመደገፍ እና የወደሙ የሃይማኖት እና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲረባረብ ተጠየቀ። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በጦርነቱ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች ጊዜያዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/44lqi
Äthiopien | Mufti Haji Umer Idris
ምስል Solomon Muchie/DW

በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን ለመገንባት ጥሪ አቀረበ

በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመደገፍ እና የወደሙ የሃይማኖት እና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲረባረብ ተጠየቀ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በጦርነቱ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች ጊዜያዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል።
ሆኖም አሁን ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ የሚጠብቃቸው ሽሮ እና በርበሬ እንካን የሌለበት ባዶ ቤት በመሆኑ መቋቋሚያ ስለሚያስፈልጋቸው መረዳዳትና መተጋገዝ ያስፈልጋል ሲል ምክር ቤቱ ተናግሯል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቱ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ኢትዮጵያ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ፣ በወለጋ እና በመተከል በችግር ተወጥራ ቆይታለች።
የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች አስቀድመን ችግሩን ለመቅረፍ ብዙ ጥረት አድርገን የነበረ ቢሆንም ልፋታች አልተሳካም ፣ ውጤትም አላመጣም ሲሉም ተናግረዋል።
ችግሩ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይለይ ሁሉንም የጎዳ መሆኑን የገለፁት ተቀዳሚ ሙፍቲ መስጊዶችም አብያተ ክርስትያናትም ፈርሰዋል፣ የጤና እና የትምህርት ተቋማትም ወድመዋል ብለዋል።
በተለይ ገበሬው ተፈናቆሎ፣ ሞቶ፣ ቆስሎ የማረሻ ሞፈሩና ቀምበሩ ተፈልጦ ተማግዶበታል ሲሉ ገልፀዋል።
የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ኮሚቴ እናቋቁማለን ያሉት ሙፍቲ በወለጋ በኩል ያለው ችግር አሁንም እንዳልበረደና ብዙ ሕዝብ ፣ መስጊዶችና አብያተ ክርስትያናት ውድመት እንደደረሰባቸውና ይህም መፍትሔ ያገኛል ብለው እንደሚያምኑ ጠቅሰዋል።
የሰው ልጅ ደም፣ የንፁሃን ደም እንዲፈስ አንፈልግም። ሕዝብም እንዲለያይ አንፈልግም። ስለሆነም የሃገር ሽማግሌዎች የሰላም መንገድ እንዲቀይሱ ይቀራረቡ በሚልም ጥሪ አቅርበዋል።
መሻሂኮችና ዑለማዎች ፣ሌሎችም የሃይማኖት መሪዎች ከተለያየ ቦታ ተፈናቅለዋል፣ 60 የሚሆኑ የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች አሁን ድረስ በጠቅላይ ምክር ቤቱ ግቢ ውስጥ እንደተጠለሉ ይገኛሉም ተብሏል።
መጅሊስ የኢትዮጵያን ሕዝቡ አስተባብሮ ሀብት በመሰብሰብ መስጊዶች እና አብያተ ክርስትያናት እንዲሁም የማህበራዊ ተቋማት እንዲሰሩ እናደርጋለን በማለት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ቃል ገብተዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ