1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የብር ኖቶች መቀየር፣ የኦነግ ውዝግብና በቤኒሻንጉል ዘር ተኮር ጥቃት  

ዓርብ፣ መስከረም 8 2013

ሰሞኑን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ታዳሚዎችን ካጨናናነቁ ሁነቶች መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት በድንገት የወሰደው አዲስ የብር ለውጥ እርምጃ ቀዳሚው ነው:: በዚህ ውሳኔ የተደሰቱና ጮቤ የረገጡ የመኖራቸውን ያህል በውሳኔው ዱብ ዕዳነት የተደናገጡና የበሸቁትም ቁጥር ቀላል አለመሆኑን የተሰጡ አስተያየቶች ያሳያሉ::

https://p.dw.com/p/3ih8v
Instagram
ምስል picture-alliance/empics/Y. Mok

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሰሞኑን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ታዳሚዎችን ካጨናናነቁ ሁነቶች መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት በድንገት የወሰደው አዲስ የብር ለውጥ እርምጃ ቀዳሚው ነው:: በዚህ ውሳኔ የተደሰቱና ጮቤ የረገጡ የመኖራቸውን ያህል በውሳኔው ዱብ ዕዳነት የተደናገጡና የበሸቁትም ቁጥር ቀላል አለመሆኑን የተሰጡ አስተያየቶች ያሳያሉ:: እኛም ነቅተናል ጉድጓድ ምሰናል የሚለውን ሃገርኛ ብሂል ያስታወሰን የሕወሃት ደጋፊ አክቲቪስት ነው የሚባለው ዳንኤል ብርሃኔ "ይህ የብር ልውጥ መረጃ አስቀድሞ ስላፈተለከ ብዙ ብር ያላቸው የተለያየ አማራጭ ተጠቅመዋል:: ወደ ወርቅ ወደ ዶላርና ወደ ቋሚ ንብረት በመቀየር" ሲል አጠር ያለ መልዕክቱን በፌስ ቡክ ገፁ ላይ አስፍሯል::

Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

"በጨረቃው ምርጫ ማግስት አብቹ ከባድ ቡጢ በሕወሃት ላይ አሳርፏል:: አሁን ትህነግ የዓለም ከባድ ሚዛን ቦክሰኛው ማይክ ታይሰን በሻምፒዮና ውድድር ወቅት የኤቫንደር ሆሊፊድ ቡጢ ሲበዛበት በጥርሱ ወደ ጆሮ ዝንጠላ እንደተሸጋገረበት አስደንጋጭ ትዕይንት በድንገተኛ ብር ለውጡ አቅሏን የሳተችው ወያኔም ባለ በሌለ ጉልበቷ የጥፋት አቧራ ለማስነሳት የሞት ሽረት ትግል ላይ ያለች አስመስሏታል:: በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ´ከምርጫው በኋላ ከፌደራል መንግስቱ ጋር የሚኖረን ግንኙነት ልክ እንደ ጎረቤት ሶማሊያ የጦር አበጋዞች ይሆናል´ ሲሉ በኢትዮጵያዊነቱ ከሚኮራው የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት ውጪ ህገወጥ ሀገረ-መንግሥት እንመሰርታለን በሚል ባዶ ፉከራ የማዕከላዊ መንግስትን እጅ ጠምዝዘው ዳግም የስልጣን ኮርቻ ላይ ለመፈናጠጥ የፖለቲካ ሴራ ሲሸርቡ የከረሙት የሕወሃት አመራሮች ለ 27 ዓመታት በህገወጥ መንገድ ዘርፈው ሃገር የሚያምሱበትን በቢልዮን ምናልባትም በትሪልዮን የሚቆጠር ሕገወጥ ብር ህጋዊ ለማድረግ ሩጫ ላይ ናቸው:: ወዳጆቻችን እነ ኢትዮ-ዊኪሊክስና እነ ኢትዮ-ፓፓራዚ ሹክ እንዳሉን እዚህ በለንደን ጎዳናዎች ሳይቀር አዲሱን ብር በዩሮ በዶላርና በፓውንድ ለማምከን አንድ ፓውንድ እስከ ሰባ ብር የሚመነዝሩ ህገወጥ ሰዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል:: አጃኢብ ነው! ወይ ያልታደለች ሀገር! ልብ በሉልኝ ! መንግሥት ሙስናን ህገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድንና የገንዘብ ዝውውርን በተጨማሪም ሀገራዊ ሽብርተኝነት ለመቀልበስ ይረዳል ብሎ የወሰደው የብር ለውጥ እርምጃ በእጅጉ የሚደገፍ ቢሆንም በሕወሃት ውስጥ የመሸጉ በወንጀል ተጠርጣሪዎች ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በዘረፋ አከማችተውታል የሚባለውን የፋይናንስ አቅም ለማምከን ቆርጦ እንደተነሳው ሁሉ ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ እንዲሉ በኦሮምያም ክልል እንዲሁ ከሃያ ያላነሱ ባንኮችን ተደራጅተው በጠራራ ፀሃይ የዘረፉትን ህገወጦች እና የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን በተጨማሪም ከትህነግ ዘረፋ በባሰ መልኩ ሽርክና ፈጥረው በአዲስ አበባና በአጎራባች አካባቢዎች በኮንዶምኒየም የመኖሪያ ቤቶች ህገወጥ እደላና በመሬት ስርቆት ላይ የተሰማሩ የመንግሥት አመራሮችን ቢሮክራቶችን እና ቴክኖክራቶችንም ለፍርድ ያቀርብልናል ብለን እንጠብቃለን" ሲሉ ትዝብት አዘል አስተያየታቸውን ጀባ ብለዋል:: የገበያው ታምር ምጥን መልዕክት ግን ገዢው ፓርቲ ላይ በቀጥታ ያነጣጠረ ሲሆን "በህወሃት ስም የሚነግደው ራሱ የለውጥ ኃይል ነኝ ባይ ተረኛው መንግስት ነው" የሚል አንድምታ አለው::

አቤም ጌቱ የተባሉ ግለሰብ በበኩላቸው ከዚሁ ከገንዘብ ለውጥ ጋር በተያያዘ አጠር ያለ የጥንቃቄ ምክራቸውን እንዲህ ለግሰዋል:: "ስሜት ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ጥንቃቄም ያስፈልጋል:: ለምሳሌ አሮጌው የብር ኖት ቢያንስ ለዘጠና ቀናት ጎን ለጎን አገልግሎቱ ይቀጥላል:: ስለሆነም አርብቶ አደሩና በተለይም ቡና አብቃይ ገበሬው አካባቢ ምርቱን በጥሬ ብር ባይገበያይ መልካም ነው:: ይህን ችግር ለመቅረፍ በልማት ሰራተኞች በኩል ከወዲሁ ማንቃት ቢቻል እና የምርት ሽያጩም በገንዘብ ሳይሆን በሰዎች መካከል ሊዘዋወርም ሆነ ሊተላለፍ በማይችለው በቫውቸው ገንዘቡን ተክቶ የሚሰራበትን መላ መዘየድ ያስፈልጋል:: ለማህበራትም ከወዲሁ በበቂ ሁኔታ ቫውቸር ታትሞ መቅረብ ይኖርበታል:: አለበለዚያ ግን ኮንቴይነር ውስጥ የሻገተ ብር የመበተን ዕድሉ ከፍተኛ ሲሆን አዲሱንም ብር በቀላሉ ህገወጦች ከገበያ ሊሰበስቡት ይችላሉ" በማለት ምክራቸውንም ስጋታቸውንም ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ይድረስ ብለዋል::

ይህን አስተያየት ያነበቡትና ውስጥ አዋቂ የሚመስሉት ሳራ ግርማ በአፀፋቸው "ብልፅግናዎች ብር መቀየር የፈለጉበት ዋናው ዓላማ ህወሃቶች እጅ ያለውን ብር ዋጋ እንዲያጣ ለማድረግ ነው:: ችግሩ በህወሃቶች እጅ በአሁኑ ሰዓት በብዛት ያለው ብር ሳይሆን ዶላር እና ዩሮ ብቻ ነው::" ሲሉ በምፀት ሃሳባቸውን አጋርተዋል:: ተክሊት አብርሃም ግን የብር ኖቱን ለውጥ ከሚቃወሙት ወገን ናቸው:: ዘሃበሻ ፌስቡክ ላይ ባሰፈሩት አስተያየት " ሲጀምር ለስም ግንባታ ለፖለቲካ ትርፍ እና ታሪክ ለማትፋት ካልሆነ በስተቀር የብር ለውጡ ለኢኮኖሚው እድገት አንዳችም ፋይዳ የለውም:: በኤሌክትሮኒክስና ሞባይል የመረጃ መረብ /ኢንተርኔት/ ኦንላይን ባንኪንግ የረቀቀ ዘመን በወረቀት ብር መጠቀም ከዚህ በተጨማሪ 200 አዲስ የወረቀት ኖት ማሳተም እንደ ኢትዮጵያ ላለ ደሃ ሀገር ህገ-ወጥ ፎርጅድ ብርን ከማስፋፋት እንዲሁም ለህትመት ከሚወጣ የውጭ ምንዛሪ በስተቀር ምንም ጥቅም የለውም:: ምናልባት አንዳንድ አራጣ አበዳሪዎች፣ ግብር የሚሰውሩ አስመጪዎች፣ ሃዋላ የሚሰሩ ህገወጦችና እንደ አሮጌ መኪና ያሉትን መገልገያዎች አስመጪዎች ከዕቃው ሽያጭ ዋጋ ተመን በታች (under invoice) ደረሰኞችን ስለሚያሰሩ እንዲሁም በራስ የውጭ ምንዛሪ የሚሰሩ ነጋዴዎችን በተወሰነ ደረጃ ሊጎዳ ይችል እንደሆነ እንጂ በጠራራ ፀሃይ ባንክ እየተዘረፈና ህጋዊ ያልሆነ የባንክ ብድር እደላ አስካልቆመ ብርን መለወጥ ብቻውን አንዳችም ትርጉም የለውም" ነው ያሉት ተክሊት በማህበራዊ ሚድያ ባጋሩት መልዕክታቸው::

በሰሞኑ የኦነግ አመራሮች ውዝግብ ዙሪያም ማህበራዊ መገናኛ ዜደዎች የሕዝቡን አስተያየት በስፋት እያስተናገዱ ነው:: ማሪዮ ስትራምፎ የተባሉ ግለሰብ በአፈትላኪ ዜናዎች ፌስቡክ ላይ "ቃል በተግባር ሲፈተን" በሚል ርዕስ እንዲህ የግል ሃሳባቸውን አጋርተዋል:: "ጠቅላያችን የለውጡን አመራር ሲረከቡ ባደረጉት ንግግር "ከእንግዲህ ከሕዝብ የተደበቀ አንዳችም ስራ አንሰራም" ሲሉ ቃል ገብተው ነበር:: ቃሉን አምነናቸው ስናበቃ በዛው ሰሞን የለውጡ ሞተር የበሩት ለማ መገርሳ አስመራ ተሻግረው ከኦነግ ጋር ያደረጉት ምስጢራዊ ድርድር ግን ዛሬም እንቆቅልሽ እንደሆነብን አለ:: ከ 25 ዓመታት በላይ በአስመራ በረሃዎች ትጥቅ ሳይሆን ሞፈር ጨብጦ ሲንከላወስ የኖረው ኦነግ ሸኔ በሰላምና በለውጥ ስም ከሕዝብ በተደበቀ ስምምነት ወደ ሃገር ሃገር ከገባ በኋላ ከሌሎች ታጣቂ ኃይላት በተለየ ሁኔታ ጫካ መሽጎ በመሳሪያ እንዲደራጅና ጉልበቱን እንዲፈረጥም መንግስት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ልዩ ድጋፍ ሰጥቶታል:: ዛሬ አያሌ ተማሪዎች በታጣቂው ሃይላት ታግተው የውሃ ሽታ ሆነው እንደቀሩ እየተነገረ ነው:: በኦሮምያ በአማራ ክልል እና በቤኒሻንጉልም ሰላማዊ ዜጎች ዛሬም ድረስ በግፍ እንዲያልቁና ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ዋናው ምክንያት መሆኑም ይጠቀሳል:: በቅርቡ ድርጅቱ ለሁለት ሲከፈል አንዳንድ ዋና አመራሩ መቀሌ ከመሸገው ቡድን ጋር ግንኙነት ፈጥሮ ሰላማዊውንም የትጥቅ ትግሉንም ጎን ለጎን ሲያራምድ መቆየቱን ሰምተናል:: ለመሆኑ የመንግስትን ስልጣን የሚጨብጠው ቡድን እስከመቼ ይሆን በደሃው ደም መቆመር የሚቀጥለው? እስኪ እናንተም ሃሳብ ሰንዝሩበት" ነው ያሉት ማርዮ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ::

 Logo Oromo Liberation Front

ያየኽ መኩሪያው የተባሉ ግለሰብም በኦነግ አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ላይ በዘሃበሻ ፌስቡክ ታዳሚው የሚያደርገውን ውይይት ታዝበው "አሁን ደግሞ ሌላ ዕልቂት ሊመጣ ነው:: እኔ የምለው ፖለቲከኞች በቁማር በተኳረፉ ቁጥር እስከመቼ ነው የንፁሃን ደም የሚፈሰው? መንግሥት ተብዬው እንደሆነ የዜጎቹን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን ዘንግቶታል:: ባለፈው እንኳ ኦነግ ሸኔ ትጥቅ ይፍታ በሚባልበት ወቅት ´ማነው ፈቺ ማነው አስፈቺ´ ማለታቸውን እናስታውሳለን:: ይህ አባባል የሚነግረን አንድም መንግሥት አቅመ ቢስ መሆኑን አልያም ደግሞ ኦነግ በምሥጢር በመንግሥት እንደሚደገፍ የሚያሳይ ነው" ሲሉ ስሜታቸውን አንፀባርቀዋል:: ከዚህ በተለየ እጥር ምጥን ያለ አስተያየቱን ያቀረበው አማኒ ሶሪ "ዳውድ ለ 21ኛው ክፍለዘመን የሚመጥን የፖለቲካ አስተሳሰብ የለውም:: ጦርነት እና መገንጠል ብቻ!" ሲል ምፀታዊ አስተያየቱን አጋርቷል:: ሂሩት ቦጋለም ቀበል አድርጋ "እናንተን ወደ ስልጣን ለማውጣት ስንቱ የኦሮሞ ወጣት እንደወጣ መቅረቱ ያሳዝናል:: አሁንም ወጣቱ ልብ መግዛት አለበት" ስትል መልስ ሰጥታለች::

ሙግቱ ብሽሽቁና እሰጥ አገባው እንዲህ ሞቅ ከረር ባለበት የማህበራዊው የመገናኛ ዘዴዎች የውይይት መድረክ መለስ ቲ. አለሙ በተቃራኒው "ይህቺ የወያኔ ኮፒ ናት:: በቅድሚያ የፖለቲካቸው ስጋት የሆኑ ፓርቲዎችን መከፋፈል፤ ከዛም አሃዳውያኑ በሚያስቀምጧቸው ቡችሎች የኦሮሞን ሕዝብ እንደፈለገው መዘወር ነው ሥልቱ:: የኦሮሞ ሕዝብ አንድነቱን ካልጠበቀ መውደቂያው ከዚሁ ነው የሚጀምረው:: የኦሮሞ ተቆርቋሪ ግለሰቦችን አስሮ፤ የኦሮሞ ታጋይ ፓርቲዎችን አክስሞ የኦሮሞን ሕዝብ ማስተዳደር አይቻልም" የሚል ጠንከር ያለ መልስ ሰጥተዋል:: በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት ኢትዮጵያ ፈርስት በሚል የብዕር ስም የታደሙ ግለሰብ"ወደድንም ጠላንም ኦነግና የኦሮሞ ሕዝብ አንድ ነው:: ሕዝብ ያለውን ድርጅት ደግሞ በድራማ መበተን ቀልድ ነው:: ይልቅስ አሁንም ባለችን ሽርፍራፊ ሰዓት ሁሉን አሳታፊ የፖለቲካ ውይይት ይደረግ" በማለት የሃሳብ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል:: የኦነግ ደጋፊ ባልሆንም አቶ ዳውድ ኢብሳን ያገደው የአብይ ኃይል ነው የሚል ጥርጣሬ ያላቸው ቢሊሴ ጣፋ ሲዳ የተባሉ ብዕረኛም በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን የሚተላለፈው መግለጫ ከድርጅቱ ያገዳቸው ቡድን ብቻ መሆኑ ለዚህ አባባላቸው አንዱ ማረጋገጫ መሆኑን አመልክተዋል::

በዚህ ሃሳብ የማይስማሙት ጪሮ እርጎ ዘርይሁን በዛው በዘ-ሃበሻ ፌስቡክ በጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ፈጠን ብለው ሰጥተዋል:: "የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የኦሮሞ ሕዝብ እንጂ የዳውድ ኢብሳ ወይም ፍሬው ኢብሳ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው እንዴ? አባላቱን የሚሾማቸውም ሆነ የሚያወርዳቸው እኮ ጠቅላላው ጉባኤ ነው:: አሁን ማረፍ አለባቸው ብሎ ከስልጣን ሲያወርዳቸው ደግሞ ውሳኔውን መቀበል አለባቸው:: በመሰረቱ የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ላይ አቶ ዳውድ ኢብሳ ለዘለዓለም መምራት አለባቸው ተፅፎ ከሆነ በእርግጥ ያ ህግን መጣስ ነው:: ካልሆነ ግን ግለሰቦችን ማውረድም ሆነ መሾም ስልጣኑ የጠቅላላው ጉባኤ ስለሆነ አቶ ዳውድም ሆኑ አቶ ፍሬው ባወጡት ህግ ነውና የተዳኙት ለጉባኤው የህግ ውሳኔ ተገዢ መሆን አለባቸው::" ይህ ከሞቀው የሰሞኑ የማህበራዊ ሚድያ የኦነግ አመራሮች ውዝግብ ውይይት ላይ በጥቂቱ የቀነጨብነው ነበር::

"ኢትዮጵያ የአማራ የግፍ መቃብር መሆኗ መቼ ያበቃል?" በሚል ርዕስ ሊክድ አማርኛ ማህበራዊ የፌስቡክ አምድ ረዘም ያለ አስተያየት ለንባብና ለውይይት አቅርቦ ነበር:: በአካባቢው ጥቃት ከመፈፀሙ አስቀድሞ መዋቅራዊ ወይም ( ህገ-መንግስታዊ) በሆነ መንገድ " እኛ" እና " እነሱ" የሚል አደረጃጀት መፈጠሩን ነው መልዕክቱ የሚያብራራው። ለምሳሌ በክልሉ ህገ- መንግስት መሰረት የክልሉ ባለቤቶች በርታ፣ ጉምዝ፣ ሽናሻ፣ ማኦና ኮሞ ናቸው ይላል። እጅግ አስገራሚው ነገር የህዝብ ብዛት ስብጥሩ ግን 31% አማራና አገው፤ 22% በርታ፤ 13% ኦሮሞ፤ 8% ሺናሻ ሲሆኑ የተቀሩት ከሺናሻ ቁጥር በታች መሆናቸው ነው። በጥቃቱም የሚገደሉ ሰዎች አስቀድሞ ስም ዝርዝራቸው ተለይቷል። የውስጥና የውጪ ሃይሎች በተሳተፉበት አሰቃቂው ጥቃት እንዲገደሉና ንብረታቸው እንዲዘረፍ ታርጌት የተደረጉት በተለይ አማራና አገው ሲሆኑ ከአንድ ቤተሰብ እስከ 5 ሰዎች አሰቃቂ በሆነ መንገድ ተገድለዋል። መንግሥትና የሚዲያ ተቋማቱ ነገሩን የማደባበስና የመካድ ስራ ሰርተዋል። ግድያው ከመፈፀሙ በፊት የጥቃቱ ሰለባዎች ስጋት እንዳለባቸው ለአካባቢው መንግስት ቢያሳውቁም መንግስት በቸልተኝነት የሰዎች ህይወት እንዲጠፋ አድርጓል ነው ያለው ዘገባው። ይህን የውይይት ሃሳብ መነሻ አድርጎም በርካቶች ቁጣቸውን፣ ሃሳብና አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:: አብዩ አይናለም የተባሉ ሴት "በጥባጭ ገዳዮች የት እንደመሸጉ አዴፓ ያውቃል:: እናም መጠየቅ ያለበት እሱ ነው ካባ አልባሹ" ሲሉ ተችተዋል:: አቶ ነጋ ታሪኩም "ሕወሐት በምርጫ ተወጥራ በነበረበት ባለፉት ሳምንታት አገራችን ሰላም ሆና ነበር። እነሆ የጨረቃ ምርጫው ባበቃ በነጋታው ሰዎች መገደል ጀመሩ። ሕወሓት ወደ አገር ማበጣበጥ ስራዋ ተመልሳለች ማለት ነው" ብለዋል:: መሀመድ ሀሰን አደም ግን ይህን ወቀሳ ጅምላ ፍረጃ ሲሉ ተቃውመውታል:: እጥር ምጥን ባለ መልዕክታቸውም"ህወሃት አርዕስት ከመሆን አርፋ ነበር:: ሀገር መምራት ያቃተው ሁሉ ህወሀትን እና ኮረናን የእድሜ ማራዘሚያ ማድረጉ ደሞ ሊጀመር ነው" ሲሉ ወርፈዋል:: ዮሃንስ እንሰርሙም "እኔ የህወሃት ደጋፊ አይደለሁም:: ግን ካለፉት 27 ዓመታት የከፋ ወንጀል በዚህ ሁለት ዓመታ ውስጥ ተፈፅሟል:: ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ደግሞ በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ነው" በማለት ነበር ትዝብታቸውን ያጋሩት:: ማይንድ ስቴት በተሰኘ ብዕር ስም በውይይቱ የተሳተፉ ግለሰብም "ህወሃት መቀሌ ሆና ያሻትን ማድረግ ከቻለች መወቀስ ያለበት የደካሞች ስብስብ የሆነው ብልፅግና የሚባል ፓርቲ ብቻ ነው" የሚል ትችት ሰንዝረዋል:: አንድ የአፈትላኪ ኒውስ አምደኛም የሰሞኑን የዜጎች ጥቃትና በማህበራዊ ሚድያ አነጋጋሪ የነበረውን የአዴፓ የምስጋና ሽልማት ሥነሥርዓት እንዲህ በሁለት ስንኝ ተችቶታል :- "አባይን ተሻግሮ ቁማር ለበላቸው፣  ካባ ደረቡለት ጆከሩ መስሏቸው" ´እርግጥ ነው የኦዴፓን ድብቅ ሴራ ገሀድ ላወጣው ሽመልስ አብዲሳ ይህ ካባ ያንስበታል´ ብሏል ታዛቢው በመልዕክቱ ማጠቃለያ:: የአብን የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለም በፌስ ቡክ ገፃቸው "ግራችንንም ቀኛችንንም ሰጥተን ጨርሰን ለብኅውትና የሚሆን ትርፍ ገላ የለንም!" በሚል ርዕስ ካሰተላለፉት ጠንካር ያለ መልዕክት ተከታዩን ቀንጭበናል:: "መንግሥት ሕዝባዊ ጥያቄዎች በተነሱበት ቁጥር በተለያዩ የአስተዳደር ክልሎች ላይ በሚገኙ አማሮች ላይ ማፈናቀል፣ እስር አፈናና ጅምላ ጭፍጨፋዎች ይፈጠራሉ:: በአማራ ስም ሥልጣን የያዙ አካላት በስሙ ወንበር የተቀመጡበት ሕዝብ ሲሳደድ፣ ሲታፈንና የዘር ማጥፋት ሲፈፀምበት ሕዝባቸውን አስተባብረውና ሥልጣናቸውንም ተጠቅመው ወንጀለኞችን ከመቅጣትና ዘላቂ መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ በወገኖቻችን እየደረሰ ያለውን ጭፍጨፋ ለምን ተናገራችሁ በሚል እኛኑ ሲያሳድዱ ይውላሉ:: በነገሬ ላይ የመከላከያ ኤታማዦር ሹሙም ሆኑ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ በመተከል እየተፈፀመ ያለውን የዘር ፍጅት የማስቆም ኦፕሬሽኖችን በመምራት ፋንታ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባዘጋጀው ድግስ እስክስታ መታደምን መርጠው በቦታው ነበሩ:: በአማራ ስም በተፈጠሩ ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች የተሰገሰጉ አማራነትን ለግል ፍላጎትና ጥቅማቸው መፈናጠሪያ መሳሪያዊ ማንነት ያደረጉ ተምቾች በመተከል በአማሮች ላይ እየተፈፀመ ያለው የዘር ፍጅት ትኩረት እንዳያገኝና የወገናቸው ጥቃት ያሳሰባቸው ሁሉ ሙሉ ትኩረታቸውን በዚሁ ላይ እንዳያደርጉ መናኛ አጀንዳዎችን እየወረወሩ ከጨፍጫፊዎች እኩል በሕዝባችን ላይ ስርየት የለሽ ነውር መፈፀማቸውን ቀጥለዋል:: የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታ ያለበት መንግሥት እንዳንሞት ከመከላከል ይልቅ ´የገደላችሁ እገሌ ነው´ በማለት ተጠምዷል:: እኛ ምን አገባን? ገዳዮችን አደብ የማስገዛት ግዴታ ያለብህ እኮ አንተ ነህ:: ገዳያችን ህወሃት ሆነ ጣሊያን ሆነ ያገባናል ወይ? ደግሞስ ህወሃት በአሸባሪነት ተፈርጆ ከፓርቲነት በህግ ይታገድ ፣ ኃብቱም ይወረስ ስንል በዝምታ ይሁንታውን የሰጠው ራሱ መንግሥት አይደለም ወይ? ምን ቀረ? አማራ ሆይ! ´ግራህን ሲመቱህ ቀኝህን ጨምርላቸው የሚለውን ለመኖር እንኳ አይታደልህም:: እኛ እኮ ለብኅውትና እንኳን የሚሆን ትርፍ ገላ የለንም:: ሁሉንም ሰጥተን ጨርሰናል:: ይልቅ ልንገርህ:: መሞትህ ካልቀረ አሟሟትህን አሳምር!´ " ነው ያሉት አቶ ክርስቲያን ታደለ ሃሳባቸውን ሲያጠቃልሉ::

Äthiopien Assosa | Polizei, Region Police | Commission gate
ምስል DW/N. Dessalegn

 

እንዳልካቸው ፈቃደ

አዜብ ታደሰ