1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ውሃ ጉዳዮች መማክርት አስተያየት በዓባይ ግድብ

ዓርብ፣ ሐምሌ 29 2014

የኢትዮጵያ ውሃ ጉዳዮች መማክርት ፕሬዚዳንት ዶክተር አክሎግ ቢራራ በተለይ ለዶይቸ ቨለ እንደገለጹት፣የአውሮፖ ህብረትና የሱማሊያ መንግስት በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ አሳሪ ስምምነት ይኑር የሚለውን የግብጽ አቋም እንደሚደግፉ በቅርቡ መግለጻቸው በፍጹም ተቀባይነት ሊኖረው የማይችል ነው።

https://p.dw.com/p/4FBCV
Äthiopien Guba | Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre
ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

የአውሮፖ ህብረትና ሶማሊያ በአባይ ግድብ ላይ ለግብጽ መወገናቸውን የኢትዮጵያ ውሃ ጉዳዮች መማክርት ተቃወመ።

የመማክርቱ ፕሬዚዳንት ዶክተር አክሎግ ቢራራ በተለይ ለዶይቸ ቨለ እንደገለጹት፣የአውሮፖ ህብረትና የሱማሊያ መንግስት በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ አሳሪ ስምምነት ይኑር የሚለውን የግብጽ አቋም እንደሚደግፉ በቅርቡ መግለጻቸው በፍጹም ተቀባይነት ሊኖረው የማይችል ነው። የመማክርቱ መስራችና የቀድሞ የኢትዮጵያ መንግስት የኘላንና ልማት ሚኒስትር አቶ መርስዔ እጅጉ በበኩላቸው፣የዓባይ ወንዝ አጠቃቀምና አጠባበቅ በተመለከተ የዓለም ታላላቅ ወንዞች ጋር ተመሣሣይነት ባለው ሁኔታ መራመድ እንዳለበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌት መካሄዱ እየተነገረ ነው፤በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ስለጉዳዩ እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም።

ይህን ተከትሎ ግብጽ፣በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሳሜህ ሹክሪ በኩል ለመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ ማስገባቷ ተዘግቧል። በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ምክንያት፣ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገበው ግብፅ፣ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥረት ስታደርግ ሰንብታለች። ካይሮ፣በውኃ አጠቃቀሙ ላይ ሕጋዊ እና አሳሪ ሥምምነት ከኢትዮጵያ ጋር እንዲደረስ ትሻለች።

የግብፅ ኘሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲና የሱማሊያው አቻቸው ሐሰን ሼህ መሐመድ ካይሮ ውስጥ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ሳይውል ሳያድር በግድቡ አሞላልና አጠቃቀም የአስገዳጅ ሥምምነት አስፈላጊነትን አስምረውበት አልፈዋል፤ሱማሊያ ግን የተባለውን ታስተባብላለች።

Äthiopien, Simegnew Bekele, Projektleiter des Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD)
ምስል DW/T.Waldyes

የአውሮፓ ህብረትም፣በግድቡ ሙሌትና አሠራር ላይ በሁሉም ተቀባይነት ያለው አስገዳጅ ስምምነት ጉዳይ ከግብፅ ጋር ወግኖ አቋሙን አስተጋብቷል።

የአውሮፖ ምክር ቤት ማኀበርና ግብፅ ዘጠነኛውን የጋራ ስብሰባ፣ሉክዘምበርግ ውስጥ ባደረጉበት ወቅት ነው አቋማቸውን የገለጹት።

ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው ተቀማጭነቱን አሜሪካ ያደረገው የኢትዮጵያ የውኃ ጉዳዮች ምክር ቤት ኘሬዚዳንት ዶክተር አክሎግ ቢራራ፣ድርጅታቸው ውሳኔውን በጽኑ የሚቃወመው እንደሆነ ገልጸዋል።

"ጠንካራ የሆነ ሬዞልሽን፤በኢትዮጵያ የውኃ ጉዳዮች መማክርት ካውንስል ቦርድ እንዲጽፍ ተስማምተናል።ምክንያቱም የአውሮፖ የጋራ ማኀበር ግብጽን ደግፎ ያወጣው አቋም አንቀበለውም የሚል ነው ዋናው።የሱማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ ከግብፅ ፕሬዚዳንት ሲሲ ጋር ሆኖ ባይንዲግ/አሳሪ/ሥምምነት የሚለውን ኢትዮጵያ መፈረም አለባት ነው ያለው፤እሱን አንቀበልም እኛ።"

ከኅዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ፣የሚደረግ አሳሪ ስምምነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መብት የሚጥስ ነው ብለውታል ዶክተር አክሎግ።

አሳሪ ሕጋዊ ሥምምነት፣ኢትዮጵያ ወደፊት ግድቦች ለመስራት አያስችላትም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣እንዲህ ዓይነቱን ከመንግስታትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት የሚመጣ ግፊት መቀበል እንደሌለባት አስገንዝበዋል።

BG Staudämme und Folgen | Grand Ethiopian Renaissance Dam
ምስል Gioia Forster/dpa/picture alliance

"ምክንያቱም አሳሪ ስምምነት የሚለው፣የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መብት የሚጥስ ነው፤ስለዚህ ኢትዮጵያ ግድቦች ለመስራት አትችልም የሚል ነው።ይህንን የሚያደርጉት መንግስታትም ይሁኑ ተቋማት እንደ አውሮፓ የጋራ ማኀበር ያሉ እኛ በምንም ዓይነት አንቀበልም፣ኢትዮጵያም መቀበል የለባትም የሚል አቋም ነው ያለን።"

አቶ መርስዔ እጅጉ፣የኢትዮጵያ የውኃ ጉዳዮች መማክርት ምክር ቤት መሥራች እንዲሁም  የቀድሞ የኢትዮጵያ መንግስት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ናቸው፤እርሳቸውም የዶክተር አክሎግን አስተያየት ያጠናክራሉ።

"የግብፅና የአውሮፓ ህብረት ዓመታዊ የጋራ ስብሰባ፣እና ያወጡት የጋራ መግለጫ ግድቡን በሚመለከት አሁንም ደግሞ የሱማሊያ ፕሬዚዳንት ግብፅ ሄዶ ያንን በሚያስተጋባ መልክ ነው እንግዲህ መግለጫ የወጣው። እና ይሄ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ወይም የኅዳሴን ግድብ በሚመለከት ገዢ የሆነ ስምምነት እንዲኖር ያስፈልጋል የሚለው ግብፅ የምታራምደው ዐሳብ፣ችግሩን ሊቀርፍ የሚችል አይደለም።በአጠቃላይ የውኃውን አጠቃቀም የዓባይ ውኃ ያለበትን ሁኔታ በዐባይ ውኃ ላይ ያለውን ተጽእኖ ያገናዘበ አይደለም።"

እንደ አቶ መርስዔ ገለጻ፣አሁን የሚያስፈልገው የዐባይን ወንዝ ሁኔታ የተገነዘበ የውኃውን አጠቃቀም ደግሞ በአኩልነትና በዘላቂነት ሊመራ የሚችል ዐሳብ ላይ ማተኮር ነው።

የወንዙን ሁኔታ በተመለከተ፣አጠባበቅና አጠቃቀሙ ደግሞ የዓለም ታላላቅ ወንዞች ጋር ተመሣሣይነት ባለው ሁኔታ መራመድ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

"ግብፅ የዓባይ ውኃ ሙሉ በሙሉ የእኔ ነው፣የእኔ ብቻ ነው ከዚህ ቀደምም ደግሞ የ1959 ስምምነት የሚባል አለ።ሁለቱ ሃገሮች ግብፅና ሱዳን የተፈራረሙት የዓባይ ውኃ መቶ በመቶ የእኛ ነው ብለው ነው የተስማሙት፤ ይሄ ትክክል አይደለም።"

ፍትሃዊና ቀጣይነት ያለው የውኃ አጠቃቀም ደንብ ዓለም አቀፋዊ ምርጥ ተሞክሮ ነው ያሉት አቶ መርስዔ፣ከትብብር የምናገኘው ብዙ ነገር አለ በማለት አስገንዝበዋል።

 ታሪኩ ኃይሉ 

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ኂሩት መለሰ