1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የአማራ ክልል መንግሥትን ሊከስ ነው

ሰኞ፣ ጥር 18 2012

በሞጣ እና ሌሎች ከተሞች «ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች፤ ለደረሰ የገንዘብ፣ የንብረት እና የሥነ-ልቦና ቀውስ» የአማራ ክልል መንግሥትን ለመክሰስ መዘጋጀቱን አስታወቀ። "የፌደራል መንግሥት ገለልተኛ የምርመራ ቡድን በመላክ የደረሰውን የሽብር ጥቃት እንዲያጣራ እንዲሁም በወንጀለኞች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ» ጠቅላይ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

https://p.dw.com/p/3Wocx
Äthiopien EIASC Gericht für islamische Angelegenheiten
ምስል EIASC

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሞጣ ከተማ በመስጂዶች እና የእስልምና እምነት ተከታዮች ንብረት ላይ ለተፈጸመው ጥቃት «አጥጋቢ እርምጃ» አልወሰደም ያለውን የአማራ ክልል ሊከስ መዘጋጀቱን አስታወቀ።

በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ በሞጣ እና ሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች «ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች፤ ለደረሰ የገንዘብ፣ የንብረት እና የሥነ-ልቦና ቀውስ በሕግ ለመጠየቅ » ለጠቅላይ ምክር ቤቱ የሕግ ክፍል ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውቋል። ምክር ቤቱ በመግለጫው የሞጣውን ድርጊት «የሽብር ጥቃት» ሲል ገልጾታል። 

በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ ባለፈው ታኅሳስ መስጊዶች ከተቃጠሉ በኋላ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሔዱ ነበር። ድርጊቱ "ስርዓት አልበኛ የሆኑ ቡድኖች" እንደፈጸሙት ያስታወቀው የክልሉ መንግስት ተጠጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል። አምስት ጥያቄዎች ለክልሉ መንግሥት ያቀረበው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እስካሁን ይፋ መልስ አለማግኘቱን አስታውቋል።

የሞጣን ቃጠሎ የባሕርዳር ነዋሪዎችና የሃይማኖት አባቶች አወገዙ

ምክር ቤቱ የአማራ ክልል ይቅርታ እንዲጠይቅ፤ ለተጎዱ ዜጎች ካሳ እንዲከፍል፤ ለዜጎች ደኅንነት ዋስትና እንዲሰጥ ጥያቄ ማቅረቡን በዛሬው መግለጫው አረጋግጧል። በሞጣው ድርጊት ንብረቶቻቸው የወደመባቸውን ዜጎች ለማገዝ እርዳታ ማሳሰሰብ መጀመሩን በደብዳቤ አሳውቋል። 

ምክር ቤቱ «በሞጣ ለደረሰው የሽብር ጥቃት የከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም የክልሉ መንግሥት ገለልተኛ የአጣሪ ኮሚቴ ያላዋቀረ ሲሆን እየተወሰደ ያለው የህግ እርምጃም አጥጋቢ አይደለም» ሲል ነቅፏል። 

 የሞጣ ፀጥታ አሰከባሪ ኃላፊዎች ታሰሩ

«የፌደራል መንግሥት ገለልተኛ የምርመራ ቡድን በመላክ የደረሰውን የሽብር ጥቃት እንዲያጣራ እንዲሁም በወንጀለኞች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ» ጠቅላይ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል። በሀረር፣ ድሬዳዋ እና ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ላይ እየደረሰ ነው ያለው «ትንኮሳ»  እንዲቆም ጠይቋል። 
እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ