1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ጉዞ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 3 2014

በ500 ሺሕ ብር መነሻ ካፒታል በአራት ቅርንጫፎች የተቋቋመው ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የባንኮች ገበያን ሊቀላቀል እየተንደረደረ ነው። ኦሞ ባንክ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ለማቅረብ ተቋቁመው ወደ ባንክ ከሚሸጋገሩ አንዱ ነው። ወደ ባንክ የሚያድጉት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት 70 በመቶ ድርሻ በክልል መንግሥታት ሲሆን ጥምር ግልጋሎት ሊሰጡ አቅደዋል

https://p.dw.com/p/41dUs
Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ከኤኮኖሚው ዓለም፣ የኢትዮጵያ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ጉዞ

መቀመጫውን በሐዋሳ ከተማ ያደረገው ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ከተመሠረተ 25 አመታት ሊሞሉት በጣት የሚቆጠሩ ወራት ቀርተውታል። ተቋሙ ሥራውን አንድ ብሎ የጀመረው በ500 ሺሕ ብር መነሻ ካፒታል እና በጉራጌ ፣ ከምባታ እና በወላይታ በተከፈቱ አራት ቅርንጫፎች ብቻ ነበር።

የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ገዛኸኝ ሜጎ ለዶይቼ ቬለ "በአራት ቅርንጫፎች የተጀመረው ሥራ በአሁኑ ጊዜ ወደ 232 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች" ማደጉን ተናግረዋል። ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው "በ500 ሺሕ ብር የተጀመረው ካፒታላችን ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር አካባቢ ደርሷል። ጠቅላላ ሐብቱ ወደ 10.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ወደ 5.4 ሚሊዮን ቆጣቢዎች አሉ። 1.6 ሚሊዮን ተበዳሪዎች አሉ። በድምሩ ወደ 7 ሚሊዮን ደንበኞችን ተደራሽ ማድረግ የቻለ ተቋም ነው" ሲሉ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አሁን ያለበትን ደረጃ አብራርተዋል።

ኦሞ ባንክ እየመጣ ነው

ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማሕበር ተብሎ ይጠራ የነበረው ተቋም ባለፉት አመታት የደንበኞቹ እና የቅርንጫፎቹ ቁጥር እንዲሁም የሐብቱ መጠን ብቻ ሳይሆን ሕልሙም ከፍ ብሏል። በደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች ግልጋሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ይኸው ተቋም ባለ አክሲዮኖች ባለፈው መስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም ያካሔዱት ጠቅላላ ጉባኤ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማሕበር ወደ ኦሞ ባንክ እንዲሸጋገር ውሳኔ አሳልፏል።

"በተለይ ባንክ የሚሰጣቸውን ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት ስለማንችል ሁሉ ነገር እዚያው ቁጥ ቁጥ በመሆኑ ገበያ ላይ ተወዳዳሪነትን በተለያየ መልኩ እየገታው መጥቷል። ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል አቅም ከመፍጠር አኳያ ዕድገቱ ዘገምተኛ ሆኗል" የሚሉት አቶ ገዛኸኝ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ በተወሰኑ አገልግሎቶች ተገድቦ መቆየቱ ያሳደረውን ተጽዕኖ ይተቻሉ።

ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ወደ ባንክነት ሲሸጋገር እስካሁን የሚወቅባቸውን የአነስተኛ ብድር እና ቁጠባ አገልግሎቶች ከባንክ ሥራ ጋር በማጣመር ሊያከናውን አቅዷል።  "ይኸ እኛ ስለፈለግን ብቻ ሳይሆን የሕብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታም ስለሚያስገድድ፤ ትልልቅ ብድሮችን መውሰድ የማይችሉ፤ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላሉትም በአግባቡ አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ እና እንዳይቋረጥ ትኩረት እናደረጋለን። እስከዚህ ደረጃ ያደረሱን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ የሕብረተሰብ ክሎች በመሆናቸው እነዚህ ላይ የምንሰራውን ሥራ የበለጠ የምናጠናክርበት ይሆናል" ሲሉ አቶ ገዛኸኝ ተቋማቸው የታወቀባቸውን አገልግሎቶች ችላ እንደማይል ማስተማመኛ ሰጥተዋል።  

ወደ ባንክ ሽግግር ላይ የሚገኙት ተቋማት እነማን ናቸው?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማሕበር ያሉ ተቋማት ወደ ባንክ መሸጋገር የሚችሉበትን ዕድል የከፈተ መመሪያ ይፋ ያደረገው በነሐሴ 2012 ነበር። "በገጠር እና በከተማ በግብርና እና በሌሎች ሥራዎች እንዲሁም በገጠር እና በከተማ በጥቃቅን እና አነስተኛ የሥራ መስኮች ለተሰማሩ ሰዎች ብድር መስጠት" ዋና ዓላማቸው ሆኖ ከተቋቋሙ የኢትዮጵያ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት በ24 ወራት ውስጥ ወደ ባንክ እንዲሸጋገሩ ይኸው መመሪያ ይፈቅዳል። በመመሪያው ከተቀመጡ ቅድመ-ሁኔታዎች አንዱ "እየሰጡ የሚገኘውን የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቶች የበለጠ መስጠት የሚችሉበት ሁኔታ መኖር አለበት" የሚለው ነው።

መመሪያው ይፋ ከሆነ በኋላ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከተመዘገቡ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት መካከል የባንክ ገበያውን ያማትር የያዘው የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ብቻ አይደለም። ከ25 አመታት ገደማ በፊት በ517 ሺሕ ብር የተከፈለ፤ በ1.7 ሚሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል በአምስት ባለ አክሲዮኖች የተቋቋመው አዲስ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ተመሳሳይ ሽግግር ጀምሯል። ባለፈው ሣምንት መገባደጃ የአዲስ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ወደ ባንክ ኦፍ አዲስ ወይም የአዲስ አበባ ባንክ እንዲሸጋገር መወሰኑን ይፋ አድርጓል።  ባለፈው አመት መጋቢት ወር የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ጸደይ በሚል ስያሜ የባንክ ገበያውን ለመቀላቀል ሒደት ጀምሯል። በግንቦት ወር የኦሮሚያ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ሲንቄ በሚል ስያሜ ወደ ባንክነት ሽግግር መጀሩን ይፋ አድርጓል።

የአዳዲሶቹ ባንኮች ዕድል 

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት 42 አነስተኛ ብድር እና ቁጠባ ተቋማት ይገኛሉ። በኢስታንቡል ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ጥናት ባለሙያው ዶክተር አብዱ ሰዒድ እንደሚሉት የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም፣ የኦሮሚያ ብድር እና ቁጠባ ተቋም፣ ደደቢት ብድር እና ቁጠባ ተቋም፣  አዲስ ብድር እና ቁጠባ ተቋም እና ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ዘርፉ በአጠቃላይ ከሚያቀርበው ብድር 85 በመቶውን፤ ከቁጠባ 90 በመቶውን ይሸፍናሉ።

እነዚህ ተቋማት የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት፣ ለድህነት ቅነሳ፣ ለሥራ ፈጠራ እና ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማትን ለመደገፍ ከፍ ያለ ኃላፊነት እንተጣለባቸው የሚያስታውሱት ዶክተር አብዱ ባንክ ለመሆን የሚያደርጉት ሽግግር በርከት ያሉት ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

Äthiopien | Traditioneller Markt in Debre Markos
"በገጠር እና በከተማ በግብርና እና በሌሎች ሥራዎች እንዲሁም በገጠር እና በከተማ በጥቃቅን እና አነስተኛ የሥራ መስኮች ለተሰማሩ ሰዎች ብድር መስጠት" ዋና ዓላማቸው ሆኖ ከተቋቋሙ የኢትዮጵያ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት በ24 ወራት ውስጥ ወደ ባንክ እንዲሸጋገሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ይፈቅዳል። ምስል DW/E. Bekele

ዶክተር አብዱ "በብዛት ያሉት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በመንግሥት በተለይ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች ሥር የሚገኙ ስለሆኑ አጠቃላይ የገንዘብ አቅማቸው ደከም ያለ ሊሆን ይችላል። ይኸንን ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ ወደ ባንክነት በሚቀየሩበት ጊዜ የተሻለ ዕድል ይኖራቸዋል" ሲሉ ፋይዳውን ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ ባደረገው መመሪያ "አሁን ወደ ባንክ በሚያድጉት ተቋማት ላይ የመንግሥት ድርሻ ወይም የክልል እና የከተማ አስተዳደር ድርሻ ከ70 በመቶ መብለጥ የለበትም የሚል ነገር አለ። 30 በመቶውን ደግሞ ለግል ባለሐብቶች ክፍት እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል። ይኸ ደግሞ የግል ካፒታልን በማመንጨት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታል" የሚሉት ዶክተር አብዱ በአስተዳደር፣ ግልጽነትን በማስፈን፣ የተሻለ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም እና አሰራራቸውን ለማዘመን ይጠቅማቸዋል ብለዋል። ከአነስተኛ ብድር እና ቁጠባ አቅራቢነት ወደ ተሟላ ባንክነት የሚያደርጉት ሽግግር የፋይናንስ ጥናት ባለሙያው እንደሚሉት "ዘላቂ ትርፋማነት እና የተሻለ የሥራ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ያገለግላል።"

ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስም ሆነ አዲስ ብድር እና ቁጠባ ተቋም እስካሁን የሚታወቁበትን አነስተኛ ብድር እና ቁጠባ እንዲሁም የባንክ አገልግሎቶችን በምጥረት ለማቅረብ አቅደዋል። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ረዳት ፕሮፌሰር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ዶክተር ጥላሁን አዕምሮ ይኸ ሁለቱን አገልግሎቶች ማጣመር ዶክተር አብዱ የጠቀሱትን "ዘላቂ ትርፋማነት" ለማሳካት ኹነኛ መንገድ እንደሆነ ይናገራሉ።

ዶክተር ጥላሁን "የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሚደግፉት ደሐውን የሕብረተሰብ ክፍል ስለሆነ ብዙም ትርፋማ ላይሆኑ ይችላሉ። የንግድ [ባንክ] ክንፉ ግን በጣም አትራፊ ስለሆነ ትርፋማነቱን ሚዛን በማስጠበቅ ዘላቂ የፋይናንስ ጤንነታቸውን ማረጋገጥ ያስችላል። ምክንያቱም የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እና ባንኮች ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ከሌላቸው ቀጣይነት አይኖራቸውም። ያ ማለት ደሐውን ማሕበረሰብም ሆነ ሌላውን ለመርዳት አይኖሩም ማለት ነው። ስለዚህ የትርፋማነት ሚዛንን ከማስጠበቅ አንጻር ወደ ንግድ ባንክ መቀየራቸው ጥሩ ነው እንጂ መጥፎ የሚባል ነገር አይደለም" ሲሉ ጠቀሜታውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የአዳዲሶቹ ባንኮች ፈተና

እነዚህ ተቋማት የሚያደርጉት ሽግግር ግን ሙሉ በሙሉ አልጋ በአልጋ ሊሆን እንደማይችል ዘርፉን ቀረብ ብለው ያጠኑት ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ። "የአገራችን 80 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሆነው ሕዝብ በገጠር የሚኖር ስለሆነ ያን በገጠር የሚኖርን ሕዝብ ባማከለ ደረጃ ለመስራት ወደ ባንክ ማደጋቸው ቀላል የሆነ ተግዳሮት ላይሆን ይችላል። ከዚህ አንጻር ዓላማቸውን ሊስቱ ይችላሉ በሚል ብዙዎች ሥጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። ሁለተኛው ደግሞ ከአሰራር ጋር በተያያዘ ምንአልባት እነዚህ ባንክ የሚሆኑ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሁለቱንም አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው። ይኸ አሰራር በሰፋ ቁጥር ለመቆጣጠር እና ለማስተዳደር ሊያስቸግር የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል። ሌላው እና ዋናው ከመመሪያ ጋር፤ ከደንብ ጋር፤ ከቁጥጥር ጋር በሚያያዝ ሁኔታ ወደ ባንክ በሚያድጉበት ጊዜ ብሔራዊ ባንክ በከፍተኛ ሁኔታ የአገሪቱን ባንኮች እንደሚቆጣጠረው ሁሉ እነሱንም ይቆጣጠራቸዋል። ከዚህ አንጻር አሉታዊ ጎኖች ሊኖሩት ይችላሉ የሚል ሥጋት አለ።" ሲሉ ዶክተር አብዱ ሰዒድ ሊገጥማቸው ከሚችሉ ተግዳሮቶች ጥቂቱን ዘርዝረዋል።

Äthiopien Währung Birr
የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም፣ የኦሮሚያ ብድር እና ቁጠባ ተቋም፣ ደደቢት ብድር እና ቁጠባ ተቋም፣  አዲስ ብድር እና ቁጠባ ተቋም እና ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ዘርፉ በአጠቃላይ ከሚያቀርበው ብድር 85 በመቶውን፤ ከቁጠባ 90 በመቶውን ይሸፍናሉ።ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲው መምህር ዶክተር ጥላሁን እነዚህ ተቋማት የባንክ ሥራቸውን ሲጀምሩ የአነስተኛ ብድር እና ቁጠባ ግልጋሎት ዘርፉን ችላ ካሉ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ሥጋት አላቸው። የአነስተኛ ብር እና ቁጠባን ቸል ማለት በተለይ በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖረውን የሕብረተሰብ ክፍል ከፋይናንስ አገልግሎት ማራቅ እንደሚሆን የሚናገሩት ዶክተር ጥላሁን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት እንቅፋት እንደሚሆን ያስጠነቅቃሉ።

የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት "ወደ ባንክ ሲቀየሩ የአነስተኛ ብድር እና ቁጠባ ግልጋሎት ዘርፉ ምን ይሆናል? ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አኳያ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት እንዴት ነው የሚቆጣጠሩት የሚለው ዋንኛ አጀንዳ መሆን አለበት። ይኸንን ብሔራዊ ባንክ ትኩረት መስጠት አለበት። ምክንያቱም አካታች የፋይናንስ አገልግሎት የሌለው 78 በመቶው የገጠር ሕዝብ ነው" የሚሉት ዶክተር ጥላሁን የአነስተኛ ብድር እና ቁጠባ ግልጋሎትን ቸል ካሉ  ድሕነትን ለመቀነስ፣ የፆታ እኩልነትን እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዙ ውጥኖች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተናግረዋል።

ዶክተር ጥላሁን እነዚህ ተቋማት ሽግግር ሲያደርጉ የባንክ እንዲሁም የአነስተኛ ብድር እና ቁጠባ ግልጋሎት ስለሚሰጡ "አዲስ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ገበያ 19 ባንኮች በሥራ ላይ ይገኛሉ። ተጨማሪ 20 ባንኮች ዘርፉን ለመቀላቀል መንገድ ላይ ናቸው። ዶክተር አብዱ "እነዚህ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ባንኮች በሚሆኑበት ጊዜ ከግብርና ጋር በተያያዘ የሚያስፈልጉንን የፋይናንስ ሥራዎችን የሚደግፍ መሆን እንዳለባቸው" ጥቆማ ሰጥተዋል።  "እነዚህ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ ማደጋቸው ብቻ የተለየ አስተዋጽዖ ያበረክታል ብዬ አልገምትም። እንዲያውም ሥጋቱ ያለው የተቋቋሙበትን ዓላማ ማህበራዊ ግዴታቸውን እንዳይወጡ ሊያደርጋቸው ይችላል" ሲሉ ዶክተር አብዱ አክለዋል።

ዶክተር ጥላሁን በባንክ አገልግሎት የሚደረገው ፉክክር እስካሁን በገበያው የቆዩትም ጭምር ፊታቸውን አነስተኛ ብድር እና ቁጠባ ወደ ማቅረብ ሊገፋቸው እንደሚችል ተስፋ አላቸው። ከዚህ ባሻገር አሁን በጥቂት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የተጀመረው ወደ ባንክ የሚደረግ ሽግግር ሌሎች በዘርፉ የሚገኙ ሊከተሉት የሚችሉ እንደሆነም ጥቆማ ሰጥተዋል።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ