1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ርዳታ ለአማራ ክልል ተፈናቃዮች 

ዓርብ፣ ኅዳር 24 2014

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በአማራ በአፋርና በትግራይ ክልሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተፈናቅለዋል። በአማራ ክልል ጦርነቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ወገኖች አፈናቅሏል። ተፈናቃዮቹም ለከፋ ችግር መዳረጋቸው በተደጋጋሚ ተገልጿል።ህወሓት በተቆጣጠራቸው የአማራ ክልል አካባቢዎችም 6 ሚሊዮን ወገኖች የከፋ ረሀብ ላይ ይገኛሉ፡፡ 

https://p.dw.com/p/43nXX
Äthiopien Bahar Dar
ምስል DW/A. Mekonnen

እርዳታ ለአማራ ክልል ተፈናቃዮች 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በአማራ ክልል በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል እርዳታ ሰጠ። የፌደሬሽኑ ፕረዚደንት አትሌት ደራርቱ ቱሉ እርዳታውን ባሕር ዳር በመገኘት እ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ለአማራ ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን አበርክታለች።
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በዘመድና በየመጠለያ ጣቢያዎች ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠው ይገኛሉ፣ በተለይ በአማራ ክልል ጦርነቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ወገኖች አፈናቅሏል። ተፈናቃዮቹም ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን የአማራ ክልል መንግስት በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ ህወሓት በተቆጣጠራቸው የአማራ ክልል አካባቢዎችም 6 ሚሊዮን የ ወገኖች በከፋ የረሀብ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም አሳውቋል፡፡ 
የተለያዩ አካላት በተለይ ተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ጥረቶችን እያደረጉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ትናንት በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚያገለግል 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ፍራሾችንና ለምግብነት የሚያያገለግሉ እርዳታዎችን አድርጓል፡፡ 
ባሕር ዳር ከተማ በመገኘት እርዳታውን ያበረከተችው አትሌት ደራርቱ ቱሉ እንዳለችው፣ ችግሩ የአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን የሁሉም በመሆኑ እርዳታውን መለገሳቸውን ተናግራለች፡፡ 
እገዛውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገረችው አትሌት ደራርቱ፣ ችግሩ እስኪወገድ በስነልቦና መጠንከር ያስፈልጋል ብላለች፡፡ 
የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ እርዳታው ፍራሾችንና ሌሎችንም ምግብ ነክ ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ 
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ማህበራዊ ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን በአማራ ክልል ከ2 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃይና 6 ሚሊዮን የሚጠጋ በጦርነት ቀጠና ውስጥ በችግር ያሉ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰው፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ያደረገው እርደታ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል፡፡ 
ችግሩ የሰፋ በመሆኑ በቀጣይም ሌሎች አካላትም ድጋፎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ ስዩም ጥሪ አቅርበዋል። 
ዓለምነው መኮንን 
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ