1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ተፋላሚ ኃይላት ስምምነት አተገባበርና ፈተናው

ዓርብ፣ ኅዳር 9 2015

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና የትግራይ ኃይሎች በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ እና በኬንያ ናይሮቢ የተፈራረሙት ስምምነት አተገባበር ፈተናዎች ብገጥሙትም ስምምነቱን መሬት ላይ የማውረድ አድሉ ግን ከፍተኛ ነው ተባለ።

https://p.dw.com/p/4Jl1c
Kenia I Friedensabkommen von Pretoria
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

«ስምምነቶቹ የመተግበር እድላቸው ከፍተኛ ነው»

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና የትግራይ ኃይሎች በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ እና በኬንያ ናይሮቢ የተፈራረሙት ስምምነት አተገባበር ፈተናዎች ብገጥሙትም ስምምነቱን መሬት ላይ የማውረድ አድሉ ግን ከፍተኛ ነው ተባለ። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የሕግ ባለሙያዎች መሬት ላይ ያለው እውነታ ስምምነቱን ከመተግበር ሌላ የተሻለ ሰላም የማምጣት አማራጭ አለመኖሩ ተፋላሚዎቹ ወደ አተገባበሩ እንዲገቡ ያስገድዳቸዋል ይላሉ።

ለሁለት ዓመታት አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ እና የንብረት ውድመትን ያስከተለውን የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፤ በቅርቡ ደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶሪያ ላይ ለ10 ቀናት በቆየው ድርድር መቋጨቱ በበርካቶች ዘንድ አዎንታዊ ምላሽን ያሰጠና ተስፋን ያጫረ ነበር፡፡ ይሁንና ስምምነቱ ላይ የደረሱት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና የትግራይ ኃይሎች የተስማሙባቸውን ነጥቦች ገቢራዊ ማድረግ ላይ ቀላል ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ እንደማይታመን በህግ ባለሙያዎች ይገለጻል፡፡

የኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ገቢራዊነቱ

ዶ/ር አደም ካሴ በኔዜርላንድስ አገር አይዲያ የተሰኘ ሰላም ላይ በሚሰራ ተቋም ውስጥ የህገመንግስት እና ሰላም ግንባታ አማካሪ ሆነው ይሰራሉ፡፡ እንደ ዶ/ር አደም ማብራሪያ ተፋላሚ ኃይላቱ በከፍተኛ አለመተማመን ውስጥ እንደ መቆየታቸው የሰምምነት መንገዱን በአንዴ ወደ ተግባር መቀየር ቀላል ሆናል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በተለይም የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት እና በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፎ እንዳላቸው የሚታመነው የኤርትራ ሰራዊትን ወደ ድንበር መመለስ የስምምነቱን አተገባበርና የቅድም ተከተል ጥያቄ ስለሚያስነሳ ሊያወዛግብ እንደሚችል ተጠባቂ ነው ብለዋል፡፡ ይሁንና አንዱን ቀድሞ መተግበር የግድ ስለሚሆን ተፋላሚዎቹ መካከል መተማመን ማስፈን የግዴታ መሆኑንም ተንታኙ ያነሱታል፡፡

Kenia I Friedensabkommen von Pretoria
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ (ግራ) እና የትግራይ ኃይላት ጄኔራል ታደሰ ወረደ (ቀኝ)ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

የፌዴራል መንግስቱ የሁሉም ተፋላሚ ሃይላት አገናኝ እንደመሆኑ የበዛ ኃላፊነት እንዳለበትም ተንታኙ አክለው አብራርተዋል፡፡ የቀድም የተባበሩት መንግስታት ባልደረባ እና የዓለማቀፍ ህግ ባለሙያ አቶ ባይሳ ዋቅዎያም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡

«ትልቁ እና ቀዳሚው ነገር ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ ሲሆን በዚህ ላይ ሁለቱም ተፋላሚ ሃይላት እኩል ሃላፊነት አለባቸው፡፡ በተሌም ደግሞ መንግስት ላይ ኃላፊነት ከፍ ሊል ሚችለው እንደመንግስትነቱ የተሻለ የማድረግ አቅምና ኃፊነት ስለሚኖርበት ነው» ይላሉ አቶ ባይሳ ዋቅዎያ፡፡

ከፕሪቶሪያ መልስ ላቅ ያለው ተስፋ እና ትንሹ ስጋት

ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የስምምነቱ ገቢራዊነት እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ የሚመስሉ አስተያየቶችና መግለጫዎች በተፋላሚ ኃይላት በኩል ተሰምተዋል፡፡ በተለይም በህዋሃት በኩል ስምምነቱን የፈረመ የትግራይ መንግስት እንጂ ህወሓት አይደለም የሚለው ሃሳብ ለሂደቱ እንቅፋት ይሆናል ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የምስራቅ አፍሪካን ፖለቲካ ተንታኝ እና የሕገመንግስትና ሰላም አማካሪ ዶ/ር አደም ካሴ በፍጹም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Pretoria | Waffenstillstandsabkommen für Äthiopien
መንግሥትና ሕወሓት ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላምስል PHILL MAGAKOE/AFP

እንደሳቸው ማብራሪያ ስምምነቱን ማንም ይፈርም ማን፤ ትልቁ ትኩረት ልዩነቶችን የፈጠሩ እና የሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ መሆን አለበት ብለዋል፡፡ ይህም ትጥቅ የመፍታት፣ የኤርትራ ሰራዊትን ከአከባቢው የማስወጣት እና የሰብዓዊ ድጋፎችን ማቀላጠፍ ናቸው የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የዓለማቀፍ ሕግ ባለሞያው አቶ ባይሳ ወቅዎያ በበኩላቸው ከስምምነቱም ማግስት ቢሆን የሚንጸባረቁ የሃሳብ ልዩነቶች ተጠባቂ ናቸው ይላሉ፡፡

ሰሞኑን በኢትዮጵያ መንግስት መከላከያ በኩል ለውጭ ዲፕሎማቶች ወታደራዊ አታሼ በተሰጠው ማብራሪያ የትግራይ ሃይሎችን ትጥቅ ለማስፈታት የሚረዳ ኮሜቴ በናይሮቢ ስምምነት መሰረት በሁለቱም ሃይላት በኩል የማዋቀር ስራ እየተሰራ ነው ተብሎ ነበር፡፡ 

ዩናይትድ ስቴትስም በዚህ ሳምንት በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ በኩል እንዳሳወቀችው ስምምነቱን የሚያደናቅፉ ተፋላሚዎች ላይ ከፍተኛ ማዕቀብ የሚጣል ይሆናል፡፡

የሕገመንግስት እና ሰላም አማካሪው ዶ/ር አደም ካሴ እና የዓለማቀፍ ሕግ ባለሞያው አቶ ባይሳ ዋቅዎያ ግን ማስፈራሪያ ኖረም አልኖረም፤ የፍላጎት ልዩነቶችም በተፋላሚዎች መካከል ተስተዋለ አልተስተዋለ ስምምነቶቹ የመተግበር እድላቸው ከፍተኛ ነው ባይ ናቸው።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ