1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ "በጣም የከፋ" ደረጃ ላይ ነዉ መባሉ

ማክሰኞ፣ ጥር 23 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሁኔታ "በጣም የከፋ" ደረጃ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል አስታወቀ። ተቋሙ የመብት ጥበቃ ተቆርቃሪዎች ለእሥር እየተዳረጉ ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ቢሆንም ይህንን ለማስቀረት ጥረት እያደረግሁ ነው ሲልም አስታውቃል።

https://p.dw.com/p/4MvAa
Äthiopien Zentrum für Menschenrechtsverteidiger EHRDC
ምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል

ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ያለው የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሁኔታ "በጣም የከፋ" ደረጃ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል አስታወቀ። በዋናነት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችን መብት ለመጠበቅ ከሁለት ዓመታት በፊት የተቋቋመው ይህ ተቋም የመብት ጥበቃ ተቆርቃሪዎች ለእሥር እየተዳረጉ ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ቢሆንም ይህንን ለማስቀረት ጥረት እያደረግሁ ነው ሲል አስታውቃል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ብዙውን ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ይሰራሉ ያሉት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አዎር "ብዙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሥራቸው ምክንያት ብቻ ይታሰራሉ፣ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይደርስባቸዋል" ብለዋል። ከተመሠረተ ሁለተኛ ዓመቱን ያከበረው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና እንዲጠበቁ ከውትወታ ሥራው ወደኋላ እንደማይልም ገልጿል። 
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሥራቸውን በመሥራታቸው ብቻ ለእሥር እንደሚጋለጡ ፣ ትንኮሳ እና ዛቻዎች እንደሚደርስባቸው ገልፀው ፣ የታሠሩት እንዲለቀቁ በመጠየቅ ፣ ጠበቃ በማቆም፣ ለቤተሰቦቻቸው የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እና ለችግር ሲጋለጡ ቤተሰቦቻቸውን በገንዘብ በመደገፍ እያገዙ መሆናቸውን አስታውቀዋል። "ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ አሁን የከፋ ሁኔታ ነው ያለው። ምንም እንኳን ጦርነቱ ቢያበቃም እንደ ኦሮሚያ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በየቀኑ የሰብዓዊ መብት በገፍ ይጣሳል"የማዕከሉ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ዳን ይርጋ በመብት ጥበቃ ዙሪያ "መሻሻሎች የነበሩ ቢሆንም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መስተዋል ጀምረዋል" ብለዋል። አክለውም ኢትዮጵያ ውስጥ ከሕግ አሠራር ውጪ ከፍተኛ እና አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መኖራቸውን በማሳያ በመጥቀስ ይህ እንዳይደርስ የሚሟገቱት ሊጠበቁ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ባለፉት ዓመታት በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መካከል ጠንካራ ጥምረት በመመስረት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን እና የሌሎችንም አቅም በማጠናከር ደህንነቱ የተጠበቀ የሥራ አካባቢ በመፍጠር ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ደህንነት እና መብቶች መከበር ሲወተውት መቆየቱን ገልጿል።
በቀጣይ ምን ለማድረግ እንዳሰቡም አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ገልፀዋል።

Symbolfoto Justitia
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሕግ አሠራር ውጪ ከፍተኛ እና አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይታያልምስል picture alliance


በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎች ላይ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደርግ አምባሳደር ስቴፈን አዎር ተናግረዋል። "የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን መጠበቅ ጀርመን ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ ነው። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ለመጠበቅ በዓለም አቀፍ ደረጃም ይሁን በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችንና እርምጃዎችን አድርገናል። የሰብዓዊ መብት ላይ ለሚሰሩ ድርጅቶች በቀጥታ በገንዘብ በመደገፍ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ የሚያስችላቸውን ሥራ እንዲያከናውኑ አድርገናል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ብዙውን ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ነው የሚሠሩት።
እንደሰማነው ብዙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሥራቸው ምክንያት ብቻ ይታሰራሉ፣ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይደርስባቸዋል።
ስለዚህም እንደ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ያሉ ጥምረቶችን በማሳደግ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥበቃ ማግኘታቸው እና ድምፃቸው መሰማቱን ማረግልገጥ ያስፈልጋል"


ሰለሞን ሙጬ 


አዜብ ታደሰ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ