1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መንግሥት የመልሶ ግንባታ ዝግጅት  

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 20 2014

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገው ጦርነት ጋብ የማለት አዝማሚያ ሲያሳይ የፌድራል መንግሥት ለመልሶ ግንባታ እየተዘጋጀ ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስተላለፈው የተጨማሪ በጀት ጥያቄ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች የሚያገግሙበት እና የወደመው መልሶ የሚገነባበትን "መነሻ በጀት" እንደሚያካትት የገንዘብ ምኒስትሩ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/44xjh
Äthiopien North Wollo | Tigray Konflikt zerstörte Fahrzeuge
ምስል Seyoum Getu/DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የኢትዮጵያ መንግሥት የመልሶ ግንባታ ዝግጅት  

የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት "የተጨማሪ በጀት ጥያቄ እና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ" ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ውሳኔ አሳልፏል። መንግሥት ተጨማሪ በጀት ከሚጠይቅባቸው ምክንያቶች መካከል "በአገሪቱ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ተጨማሪ ወጪ በማስፈለጉ" የሚለው ይገኝበታል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ረቡዕ ታኅሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ካደረገው ውይይት በኋላ ባወጣው መግለጫ "ከኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አኳያ የሚሰበሰበው ገቢ አሁን ያለውን የክፍያ ጥያቄ ለማስተናገድ አስቸጋሪ ሁኔታ በመፍጠሩ" መንግሥት ተጨማሪ በጀት እንዲጠይቅ ካስገደዱ ምክንያቶች መካከል እንደሚገኝበት ይፋ አድርጓል። በመግለጫው መሠረት "ወቅቱ የፈጠረውን የተጨማሪ ወጪ ፍላጎት በበጀት ሽግሽግ ለማስተናገድ" አልተቻለም።

በዚህም ምክንያት በገንዘብ ሚኒስቴር የተዘጋጀው የተጨማሪ በጀት ጥያቄ ዛሬ ረቡዕ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውይይት ከተደረገበት በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት "በጦርነትና በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ" የተጠየቀው ተጨማሪ በጀት አምስት ቢሊዮን ብር ነው። 

የኢትዮጵያ የገንዘብ ምኒስትር አሕመድ ሽዴ "የጸጥታ ኃይሎችን ማደራጀት" እና "የማብቃት ሥራ" ከፍተኛ ወጪ መጠየቁን ባለፈው ሣምንት ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባዘጋጀው እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተሳተፉበት ውይይት ላይ በጦርነቱ ወጪ ምክንያት አገሪቱ "ያልተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ሽግሽግ" ለማድረግ እና ለማዘግየት መገደዷን የገለጹት አቶ አሕመድ የፈጠረውን ኤኮኖሚያዊ ጫና ዘርዘር አድርገው አስረድተዋል። አቶ አሕመድ "የዕድገት አቅማችንን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከፍተኛ ጫና ውስጥ የከተተ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለንው" ሲሉ ተደምጠዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ተወያይቶበት ወደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የላከው የተጨማሪ በጀት እና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ረቂቅ አዋጅ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች የሚያገግሙበት እና የወደመው መልሶ የሚገነባበትን "መነሻ" ያካተተ ጭምር ነው። አቶ አሕመድ "ከልማት አጋሮች ጋር ባለን ትብብር መሠረት በተለይ ከዓለም ባንክ 400 ሚሊዮን ዶላር የማገገሚያ እና መልሶ መገንቢያ መርሐ-ግብር የመቅረጽ ሒደቱ ተፋጥኖ ነው ያለው። የአደጋ ሥጋት አስተዳደር (disaster risk management) 350 ሚሊዮን ዶላር መርሐ-ግብር እየተቀረጸ ነው" ብለዋል።

"የህብረተሰቡ ጥሪት መልሶ እንዲገነባ የገቢ ምንጫቸው ወደ ነበረበት እንዲመለስ የሥራ ዕድል ፈጠራም እንዲኖር መልሶ መገንባት እና ማሻሻል የሚለውን መርኅ በመከተል አቅማችን በፈቀደ ልክ በመንግሥት በስፋት ይሰራል" ያሉት አቶ አሕመድ ሥራው "በመንግሥት መሪነት እና አስተባባሪነት መካሔድ ይኖርበታል" ሲሉ ተደምጠዋል። "ግልጽነት፣ ተጠያቂነት እና ፍትኃዊነትን ያገናዘበ" ይሆናል ያሉት የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቀርጸው መልሶ የመገንባት እና ማሻሻል መርሐ-ግብር ቀጥታ ጦርነት ከተካሔደባቸው ቦታዎች በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ክልሎች ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች የሚያካትት ነው።

በጦርነቱ የወደመውን መልሶ የመገንባቱ መርሐ-ግብር አመታት ሊወስድ እንደሚችል የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። "የተፈጠረው ጉዳት እና የተናጋው የህይወት መሠረት እጅግ ከፍተኛ" መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሕመድ መርሐ-ግብሩ ከሶስት እስከ አምስት አመታት ሊወስድ እንደሚችል አስረድተዋል።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በተቀሰቀሰው ውጊያ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ለአንድ አመት የዘለቀው እና ጋብ የማለት አዝማሚያ ያሳየው ውጊያ ክፋት ግን የፈጠረሰው ሰብዓዊ ቀውስ ብቻ አይደለም። ጦርነቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች ከመኖሪያ ቤት እስከ ሆስፒታል፤ ከትምህርት ተቋማት እስከ አውሮፕላን ማረፊያዎች አገሪቱ የነበሯት ጥሪቶች ወድመዋል፤ አሊያም ተዘርፈዋል። ባለፈው ሣምንት ቅዳሜ የኢትዮጵያ መንግሥት የኮምዩንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ከሳ በሰጡት መግለጫ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በትግራይ ኃይሎች ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች ከ35 በላይ ሆስፒታሎች፣ 418 የጤና ጣቢያዎች፣ 1 ሺህ 700 ገደማ ጤና ኬላዎች መዘረፋቸውን እና መውደማቸውን ገልጸዋል።

ሶስት ክልሎችን ያመሰው ጦርነት በተቀሰቀሰበት በትግራይ አሁንም በቂ ሰብዓዊ ዕርዳታ እየቀረበ አለመሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል። በድርጅቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የዛሬ ሣምንት ታኅሳስ 14 ቀን 2014 ባወጣው መግለጫ ከምዕራባዊ ትግራይ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ሰሜን ምዕራብ ዞን እየደረሱ መሆኑን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቃል አቀባይ ፋርሐን ሐቅ ባለፈው ሣምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰሜናዊ ኢትዮጵያ "ያለው ሁኔታ ተለዋዋጭ እና ሊገመት የማይችል" ሲሉ ገልጸውታል። "በሰሜን ኢትዮጵያ በቂ አቅርቦት፣ ነዳጅ እና ጥሬ ገንዘብ ለትግራይ ማቅረብ አለመቻልን ጨምሮ የዕርዳታ አቅርቦት ሥራው አሁንም በርካታ ተግዳሮቶች እየገጠሙት ነው" ያሉት ፋርሐን ሐቅ "በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች ነጻ፣ ዘላቂ እና ደሕንነቱ የተጠበቀ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች እንቅስቃሴ እና የዕርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች" መኖሩን እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ጦርነቱ በተካሔደባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥሪታቸውን እንዳጡ እና "የማምረት አቅማቸው በከፍተኛ ደረጃ" እንደተናጋ በአዲስ አበባ በተካሔደው ውይይት ላይ አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የጦርነቱን ዳፋ "ተቋቁሞ የማለፍ አቅሙ በተሻለ ደረጃ ላይ" እንደሚገኝ ይግለጹ እንጂ የመንግሥት "ገቢ የተወሰነ መቀዛቀዝ" እንደሚገጥመው አልሸሸጉም።

"ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ሰፊ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም" ያሉት አቶ አሕመድ ባለፉት ወራት የነበረው ሁኔታ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ "ከፍተኛ ጫና ውስጥ" የሚከት እንደሆነ አስረድተዋል። አቶ አሕመድ እንዳሉት መንግሥታቸው በመጪዎቹ ጊዜያት በጦርነቱ የከፋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የዕለት ደራሽ እርዳታ ማቅረብ ላይ ትኩረት ያደርጋል። የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ሥራ መመለስም ሌላው ተግባር ነው።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ