1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዳሰሳ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 11 2014

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ቀውስ በአፋርና አማራ ክልሎች 7 ዞኖች መደበኛና ጥራት ያለው የመንግሥት አገልግሎት ለመስጠት አዳጋች ማድረጉን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ተናገረ። በሁለቱ ክልሎች ውስጥ በጦርነቱ በርካቶች ለሞት፣ ለመፈናቀል፣ ለጾታዊ ጥቃት ከመጋለጣቸው ባሻገር ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱን ተቋሙ ገልጧል።

https://p.dw.com/p/4A6mt
Äthiopien | Seblework Tariku und Adane Belay
ምስል Solomon Muchie/DW

በርካቶች ለሞት፣ ለመፈናቀል፣ ለጾታዊ ጥቃት ተጋልጠዋል

በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት ያስከተለው ቀውስ  በአፋር እና በአማራ ክልሎች ውስጥ ባሉ ሰባት ዞኖች መደበኛ እና ጥራት ያለው የመንግሥት አገልግሎት ለመስጠት አዳጋች ማድረጉን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ተናገረ። ተቋሙ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ለ18 ቀናት አደረግሁት ባለው ዳሰሳዊ ቁጥጥር በጦርነቱ በርካቶች ለሞት፣ ለመፈናቀል፣ ለጾታዊ ጥቃት ከመጋለጣቸው ባሻገር ከፍተኛ የንብረት ውድመት ደርሷል ብሏል። ጥናት በተደረገባቸው አምስት ዞኖች ብቻ ከአንድ ሺህ በላይ የጾታ ጥቃት መመዝገቡ ተገልጧል። ይህም በመሆኑ አፋጣኝ መፍትኄ ካልተበጀለት ቀውሱ ወደ ከፋ ደረጃ ተሸጋግሮ የፀጥታ ችግር ሊያስከትል ይችላልም ብሏል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ይህንን ሥራውን ትግራይ ክልል ውስጥ ኼዶ ማከናወን አለመቻሉን ገልጿል። ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ችግሩ ከፍተኛ ጫና እና ተጽእኖ ባሳደረባቸው አካባቢዎች መሰረታዊ የመንግሥት አገልግሎቶች እንዲሰጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግሥት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እንዲያደርግም ጠይቋል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ