1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሻሻል ላይ ምክክር ለማድረግ የሚያስችል መድረክ ማዘጋጀቱን

ቅዳሜ፣ ጥር 20 2015

ኤፓክ፣መድረኩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ፣ዋናው እና በአንደኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚገባዉ የኢትዮጵያ ችግር፣አሁን በሀገሪቱ ያለው ህገ መንግስት ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4Mp7T
Äthiopien Ausgabe der Verfassung, Buchcover
ምስል Solomon Muche/DW

ሕገ መንግስቱን ስለማሻሻል

የኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሻሻል ላይ ምክክር ለማድረግ የሚያስችል መድረክ ማዘጋጀቱን የአሜሪካ ኢትዮጵያ የህዝብ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ-ኤፓክ አስታወቀ።

 የኤፓክ ሊቀመንበር፣አቶ መስፍን ተገኑ በተለይ ለዶይቸ ቨለ እንደገለፁት፣የውይይት መድረኩ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ህገ መንግሥቱ እንዴት ይሻሻል በሚለው ዐሳብ ላይ ድምጽ እንዲኖራቸው ያስችላል።

አቶ መስፍን እንደሚሉት፣ የሚካሄደው ውይይት መድረክ፣በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ሊካሄድ በታቀደው ብሄራዊ ምክክር የመካፈል ዕድል እንዲያገኙ በሚል የተዘጋጀ ነው።
 "የዲያስፖራው ሚና ምድነው? ኢትዮጵያ አሜሪካውያን እንዲሁም፣በዓለም ላይ ያለው ጠቅላላው ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ምንድነው ማበርከት ያለበት የሚለውን እና ያንንስ እንዴት ነዉ የሚያደርገዉ? የሚለው ነገር ካሰብንበት በኋላ፣ገንቢ በሆነ መንገድ ለምክክር ኮሚሽኑ የሚረዳ ስራ መስራት ይቻላል በሚል፣ያንንም በዚህ አጋጣሚ ዲያስፖራው በዓለም ላይ ያለውን ሐሳብ ያካተተ ጠቀም ያለ ሥራ ሰርቶ፣ ለምክክር ኮሚሽኑ በመላክ  ለሚያደርጉት ሥራ አስተዋጽኦ ይሰጣል በሚል እምነት የተጀመረ ነው።"

 ኤፓክ፣ለእዚህ ፕሮጀክት አማካሪና አደራጅ ኮሚቴዎች በቅርቡ እንደሚያቋቋም አቶ መስፍን ጠቁመዋል።

"ህግ የኮንስቲትውሽን እና እንደዚሁም ህግ አወጣጥን ልምድ ያላቸው የሶሻል ሳይንስ እንደዚሁም ይህን የመሳሰሉ ህገ መንግስት ማውጣት ላይ ሊረዱ የሚችሉ ኤክስፐርቲዝ ያላቸው ሰዎች የሚያካትት ኮሚቴ ይሆናል።እንግዲህ ይህም ኮሚቴ የሚቋቋመው በሰዎች ጥቆማ ነው።ሰዎች ራሳቸውን መጠቆም ይችላሉ ወይም ለዚህ ሥራ ቢያገለግል ይጠቅማል የሚሉትን ሰው ሊጠቁሙን ይችላሉ።"

ኮሚቴዎቹ በመጪዎቹ ወራት፣በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማኀበረሰብ አባላት፣ ሐሳቦችንና አስተያየቶችን ይሰበስባል፤ውይይቶችንም እያቀናጀ ይመራል ብለዋል ሊቀመንበሩ።
በተጨማሪም የተለያዩ ምርምሮችንና ጥናቶችን በማሳተምና በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በማውጣት፣ለኤፓክ አባላትና በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን ያሰራጫል።

እንደ አቶ መስፍን ገለጻ፣በመጨረሻም የእነዚህን ሐሳቦችና ጥናቶች ዋና ዋና ነጥቦች እየጨመቀ አጠናቅሮ በአስተያየት መልክ ለብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ያቀርባል።

ኤፓክ፣መድረኩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ፣ዋናው እና በአንደኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚገባዉ የኢትዮጵያ ችግር፣አሁን በሀገሪቱ ያለው ህገ መንግስት ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።

 ይህ ህገ መንግስት ለችግሮች መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ችግር ፈጣሪ፣ ከህዝብ አንድነት ይልቅ ከፋፋይ፣ ከሰላም ይልቅ እርስ በርስ መጋጨትን የሚያበረታታና ፍፁም ኋላቀር ነው ብሎታል መግለጫቸው።

በተቃራኒው ደግሞ፣ይህ ህገ መንግስት የህልውናችን መሠረት የሆነ የቃል ኪዳን ስነዳችን ነው የሚሉ ወገኖች አሉና፣የእነሱን አመለካከት እንዴት ለማስታረቅ አስባችኃል የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የኤፓክ ሊቀመንበር የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።

"ይጠቅመናል የሚሉ ሰዎች የሚሻሻለው ህገ መንግሥት፣ይሄ የሚጠቅማቸው ከሆነ የሚሻሻለው የእውነት የሚጠቅማቸው ነው የሚሆነው እንጂ የሚጎዳቸው አይደለም። የግለሰብ መብት የሚጠበቅባት ኢትዮጵያ የእያንዳንዳቸው አናሳም ሆነ ብሔረሰቦች በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ተዘዋውረው ሥራ ፈጥረው ልጆቻቸውን አሳድገው ንብረት ፈጥረው የሚሩባት ኢትዮጵያ ነው የሚሻላቸው እንጂ እንደዚህ አርቴፊሻል በሆነ ክልል ተካልሎ የሚኖርባት ኢትዮጵያ አይደለችም የሚል እምነት አለን።"ብለዋል። 
ታሪኩ ኃይሉ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር