የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ውይይት በአውሮጳ
ሰኞ፣ ሐምሌ 8 2011ኢትዮጵያ ያልተቋረጠ የቀደመ የሀገረ መንግስት ታሪክ ያላት ብትሆንም እስካሁን ግን ፍጹም ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ መሆን አልቻለችም። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ጥንታዊ የስነ ጽሁፍ እና የስነ ጥበብ ባለቤት፣ የነጻነት ተምሳሌት በመሆን በሌላ በኩል ደግሞ ድህነት የሰፈነባት፣ ግጭት እና ጦርነት የሚካሄድባት እና አምባገነናዊ አስተዳደር የሰፈነባት ሀገር በመሆን ታውቃ ቆይታለች።
የሀገረ ግንባታ ፕሮጀክት አጀማመርም ከዚህ መሰረታዊ አስተሳሰብ በመነሳት ኢትዮጵያውያን ያለፉትን ጥሩ እና ጥሩ ያልሆኑ ታሪኮቻቸውን ተቀብለው የአሁኗን እና የወደፊቷን ኢትዮጵያ በእኩልነት እና በመከባበር ላይ እንዲመሰርቱ ለማገዝ እንደሆነ ተገልጿል። በደህናጉ ስብሰባ ላይ የስዊዲን፣ የኔዘርላንድስ እና የቤልጂየም የሀገር ግንባታ ታሪኮች እና ልምዶችም ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከጀርመን፣ ቤልጄየም እና ከስካንዲኒቪያ ሀገራት የመጡ የልዩ ልዩ ስብስቦች ተወካዮች እና አባላት ስብሰባውን ተሳትፈዋል።
የፕሮጀክቱን ዓላማ ለማሳካት በኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉባቸው ሲምፖዚየሞች እና ስብሰባዎች መካሄዳቸውን የፕሮጀክቱ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ ገልጸዋል። በአውሮፓ እና በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ለመሳተፍም ጥረት መደረጉን እና ውጤቶችም መገኘታቸውን ለዶይቼ ቬለ አብራርተዋል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።
ገበያው ንጉሴ
ተስፋለም ወልደየስ
አዜብ ታደሰ