የኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡር
ከጎርጎረሳዊ 2018 ዓመት ጀምሮ የቻይናዉ ባቡር ከወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ የቀይ ባህር ወደብ መንገደኞችንና ቁሳቁስን ጭኖ ማመላለስ ጀምሮአል። የ«DW» ተወካይ ጀምስ ጄፍሪ በዚሁ ባቡር ከመዲና አዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ጅቡቲ በመጓዝ ተከታዮን የፎቶ ዘገባ አጠናቅሮአል።
የቻይናዉ ባቡር
አዲስ አበባ ከተማ አጠገብ የሚገኘዉ የባቡር ጣብያ የተመለከተ «ኦሪንታል» ማለትም የድሮ የምሥራቅ ቤተ-መንግሥት ቢመስለዉ አይፈረድበትም። ካለፈዉ ዓመት ጥር ወር ወዲህ ሥራን የጀመረዉ ይህ የባቡር ጣብያ ከአዲስ የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር ማመላሸሻ አገልግሎት መስመር የሚጀምርበት ሥፍራ ነዉ። የባቡር ማመላለሻ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ጅቡቲ ምድር ባቡር ኩባንያ «EDR» እና ከቻይና በተገኘ በ 4 ቢሊዮን ዶላር ወጭ የተገነባ ነዉ።
ጥብቅ አሠራር
ኢትዮጵያዉያኑ የመንገደኞች ባቡር ማመላለሻዉ አስተናጋጆች አጠር ያለ ቀይ ቀሚሳቸዉንና ቆብን አድርገዉ ከጠዋቱ 2 ሠዓት ወደ ጅቡቲ የሚጓዘዉን መንገደኞች እንኳን ደህና መጣችሁ እያሉ ወደ ባቡሩ ያስገባሉ። የባቡሩን ሥራ የኢትዮ- ጅቡቲ ምድር ባቡር ኩባንያ ከመረከቡ በፊት ባቡሩን የሚሾፍሩትም ሆኑ እንቅስቃሴዉን የሚቆጣጠሩት ቻይናዉያኑ ባለሞያዎች ይሆናሉ። የባቡሩን የኤሌክትሮኒክስ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩትም ሆኑ በብልሽት ጊዜ ባቡሩን የሚጠግኑት ቻይናዉያኑ ብቻ ናቸዉ።
ከከተማዉ በስተጀርባ
ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣ ሲባል ትናንሽ የገጠር ከሞች አነስ አነስ ያሉ የገጠር መኖርያ ቤቶች ይገኛሉ። አካባቢዉ ላይ ከብቶች በባቡሩ ሃዲድ አካባቢ በሚገኘዉ አረንጓዴ በለበሰዉ ሚዳ ላይ ሳር ሲግጡና ሲንቀሳቀሱ ይታያል። የባቡር መስመሩ ዋና ተቆጣጣሪ ቻይናዊዉ ቫንግ ሁግዌ እንደገለፁት «ባቡር በሚያልፍበት ሃዲድ መስመር አካባቢ በርካታ የጋማ ከብቶች በመኖራቸዉ ምክንያት ነዉ፤ የባቡሩን ፍጥነት የምንቀንሰዉ» ብለዋል። «የባቡር መስመር ሥራዉን እንደጀመረ አካባቢዉ ካሉ ገበሪዎች ጋር ጥቂት ችግር አጋጥሞን ነበር። አሁን ግን ገበሪዎቹ በባቡር ለተገጩባቸዉ ከብቶቻቸዉ ካሳን አግኝተዋል» ሲሉ ቻይናዊዉ ቫንግ ሁግዌ ተናግረዋል።
የምቾት ጉዞ
12 ሰዓታትን የሚፈጀዉ አዲስ-ጅቡቲ የባቡር ጉዞ፤ ባቡሩ መንገደኞችን አሳፍሮ ወደ ምስራቅ ያስገመግማል። በባቡሩ ዉስጥ ሁለቱ ወጣት ፍቅረኛሞች ተዝናንተዉ በመጓዝ ላይ ናቸዉ። በባቡሩ ላይ የተሳፈረች በአንዲት አዲስ አበባ ቆይታ አድርጋ ወደ ጅቡቲ በመጓዝ ላይ ያለች ወጣት «ቀደም ሲል ከአዲስ ጅቡቲ የምንጓዘዉ በአዉቶቡስ ነበር፤ እጅግ አሰልቺና ከባድ ጉዞ ነበር። ጅቡቲ ለመድረስ በትንሹ አንድ ቀን ተኩል ይወስድብን ነበር፤ በዝያ ላይ ከአንድ አዉቶቡስ ወደሌላ አዉቶቡስ ቀይረን አድረን ነበር የምንደርሰዉ» ስትል ተናግራለች። ወጣትዋ በጅቡቲ በሚገኝ አንድ ት/ቤት የእንጊሊዘኛ ቋንቋ መምህር ናት።
ጊዜን ለመጠቀም
በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ የሚጓዘዉ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ባቡሩ የተለያዩ ፉርጎዎች በተሳፋሪ ባልተያዙ ቦታዎች ላይ አንዳንድ ተሰፋሪዎች በሂና እጅን ማስጌጥን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰሩ ይታያል። እንድያም ሆኖ የባቡር አገልግሎቱ ለተሳፋሪዎች ምቾት ቅድምያን ይሰጣል። ከአዲስ ጅቡቲ- ከጅቡቲ አዲስ በየቀኑ በሚጓዘዉ፤ በሁለቱም የባቡር መስመር አገልግሎት ላይ ሁለት የእቃ መጫኛ ፉርጎዎች ይገኛሉ። በእያንዳንዱ ፉርጎ ኢትዮጵያዉያን የሚፈልግዋቸዉን ቁሳቁሶች የያዙ 106 የጅምላ የእቃ ማሸግያዎች በእቃ መጫኛ ፉሮጉዎች ዉስጥ ይገኛሉ።
ያለፈዉን ማመስገን
አዲስ የተዘረጋዉ የአዲስ ጅቡቲ የባቡር መስመር በቀድሞዉ ንጉስ ዘመን በ 20ኛዉ ምዕተ ዓመት ከተገነባዉ የባቡር መስመር ጋር ተመሳይነት አለዉ። አክስቱን ለመጠየቅ ወደ ጅቡቲ የተጓዘዉ ዩልዩስ «ምርጫ ቢኖረኝ፤ በቀድሞዉ ባቡር እጓዝ እመርጥ ነበር» ሲል ይናገራል። ዩልዮስ ለዚህ ምክንያቱ « ምክንያቱም የቀድሞዉ ባቡር መስመር የተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞችን እያቆራረጠ ነበር ጅቡቲ የሚደርሰዉ። በጉዞ ወቅት ባቡሩ የተለያዩት ከተሞችን እያቆራረጠ ሲቆም በግዛቱ ዉስጥ የሚነገሩትን የተለያዩ ቋንቋዎች ባህሎች መስማት ማየት ይቻል ነበር። ይህ የአሁኑ ባቡር ግን ሁሉን ነገር አልፎ ነዉ ጅቡቲ የሚደርሰዉ።» ባይ ነዉ።
ሕይወት የዘራዉ ባቡር
ሁለት ሦስተኛዉ የመንገደኞች ማመላለሻ ፉርጎ ተሳፋሪ አልባ የነበረዉ ባቡር ከአዲስ አበባ 728 ኪሎ ሜትር ተጎዞ ድሪደዋ ከተማ ሲደርስ በርካታ ተጓዦችን ማሳፈር ቀጠለ። አብዛኞቹ ተሳፋሪዎቹ በአማርኛ በሶማሊ ሌሎች ደግሞ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ያወራሉ። ተሳፋሪዎቹ የተለያዩ የሚበሉ ነገሮችን ከሚያዞሩ ሱቅ በደረቴዎች ይገዛሉ፤ ይወያያሉ፤ ሙዚቃም ከሩቅ ይሰማል። የባቡሩ ዉስጥ ያለዉ ካፊቴሪያ ወይም ቡና ቤት እስካሁን ሥራዉን አልጀመረም። ጅቡቲ በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ሥር በመቆየትዋ አብዛኛዉ የጅቡቲ ተወላጅ የፈረንሳይኛ ቋንቋን ይናገራል።
የተጓዥ ፍጎትን እናከብራለን
«ማስተካከያ ማድረግ አለብን» አሉ የባቡር መስመሩ ዋና ተቆጣጣሪ ቻይናዊዉ ቫንግ ሁግዌ። ቫንግ ሃገራቸዉ ቻይና እፅ ብላ ወደ ሃገርዋ እንዳይገባ ያገደችዉን ጫት የያዘ ሰዉ እሳቸዉ በሚቆጣጠሩት ባቡር ዉስጥ በመግባቱ አይተዉ ነዉ። ቫንግ በመቀጠል «ቀደም ሲል ባቡር ዉስጥ ጫት እንዲገባ ከልክለን ነበር። ግን ቆየት ብሎ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ኩባንያ ጫት የባህላችን አንዱ ክፍል ነዉ ብሎ በማለቱ ጫትን ይዞ ባቡሩ ላይ መሳፈር ተፈቅዶአል። ባህልን እናደንቃለን እንጂ አናጠፋም፤ መከባበር ያስፈልጋል።» ሲሉም አክለዋል።
በትክክለኛ መንገድ
ባቡሩ ረጭ ብሎ በረሃዉን እያቆራረጠ ጅቡቲ ሊደርስ ወደ 200 ኪሎ ሜትር ገደማ ቀርቶታል። ከባቡሩ ሞተር የሚወጣዉ ድምፅም ቀነስ ያለ ይመስላል። በባቡር መስመሩ እና በባቡር ጉዞ ምክንያት በሁለቱ ሃገራት መካከል የተነቃቃዉ የኤኮኖሚ የንግድ እንቅስቃሴ፤ በአፍሪቃ ቀንድ ሠላምና ትብብርን እያተጠናከረ መምጣቱን ያመለክታል። ይህን እንቅስቃሴ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች «ሁከትና ብጥብጥ በማያጣዉ ቀጠና አዲስ የተስፋ ጎህ የመቀደዱ ምልክት ነዉ» ይሉታል።