1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ-ቴሌኮም ድርሻ ሲሸጥ ምን ይለወጥ ይሆን?

ረቡዕ፣ ሐምሌ 25 2010

ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ገበያ ለመሳተፍ እየተዘጋጁ ነው። በኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ መሠረት የውጭ ኩባንያዎች የኢትዮ-ቴሌኮምን የተወሰኑ ድርሻዎች ሲገዙ ምን ይለወጣል? 

https://p.dw.com/p/32TJe
Äthiopien Addis Abeba Universität Kommunikation Internetsperre
ምስል DW/J. Jeffrey

የኢትዮጵያ ውሳኔ የቴሌኮም ኩባንያዎችን ትኩረት ስቧል

የደቡብ አፍሪቃው ኤም.ቲ.ኤን.፤ የኬንያው ሳፋሪኮም የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እግር አብዝተዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኃላፊ አቶ በላቸው መኩሪያ ለሬውተርስ እንደተናገሩት የአሜሪካን ኩባንያዎች ሳይቀሩ የጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ መንግሥት ውሳኔ ቀልባቸውን ገዝቷል። ውድድር በሌለበት ገበያ በብቸኝነት ወቀሳ የበዛበት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የኢትዮ-ቴሌኮም ድርሻ የሚሸጠው በዋናነት አገሪቱ በገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ነው። የድርሻ ሽያጩ ለኢትዮ-ቴሌኮም እና ደንበኞቹ ምን ይፈይዳል? ዶክተር አብዱልቃድር ሙደሲር የገመድ አልባ የስልክ ቴክኖሎጂ ባለሙያ ናቸው። በግዙፉ ዶች ቴሌኮም የሚቀጥለው ትውልድ ቴክኖሎጂ (Next Generation Technology) ኃላፊ ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ። 

ለሁለት አመታት በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮምዩንኬሽን ኮርፖሬሽን አስተዳደር ውስጥ በሙያቸው ያገለገሉ አንድ ከፍተኛ አማካሪ ግን የተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ድርሻ በመሸጥ የሚፈታ እንዳልሆነ ያምናሉ። ማንነታቸው እንዳይገለፅ የፈለጉት ከፍተኛ ባለሙያ የኩባንያውን የአገልግሎት ጥራት ማሳደግ እና የአስተዳደር ሥራውን ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር ማጣጣም ፈተና እንደነበር በኢ-ሜይል ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። የተቋሙን ድርሻ መሸጥም ቢሆን ለአስተዳደር ሥራው እንደየአስፈላጊነቱ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ቁመና ከመፍጠር የተሻገረ እንደማይሆን ባለሙያው ዕምነታቸውን ገልጸዋል። ባለሙያው የኢትዮጵያ ገበያ አስተዳደራዊ ብቃት፣ እውቀት እና ቴክኖሎጂ ያላቸው ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ውድድር እንደሚያሻው ገልጸዋል። 
ለበርካታ አመታት ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ገበያው ከኢትዮ-ቴሌኮም ኩባንያውም ከእጁ እንዲወጣ ሳይፈልግ ቆይቷል። ዶክተር ቴዎድሮስ ወርቅነሕ እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ሶስት መከራከሪያዎች ነበሩት። ዶክተር ቴዎድሮስ በአሜሪካው ኬንት ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። 

የመንግሥት አቋም ተቀይሮ በጥቂቱም ቢሆን የኢትዮጵያ ገበያ ገርበብ ብሎ ሲከፈት የቴክኖሎጂ እና የቴሌኮም ኩባንያዎች በተቻለ ፍጥነት ወደ ገበያው ለመግባት ተቻኩለዋል። በአፍሪቃ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ገበያዎች የተሰማራው ኤምቲኤን ባለፈው ወር የኢትዮጵያ ገበያ ተስማሚው እንደሆነ ገልጾ ነበር። የፈረንሳዩ ኦሬንጅ ኩባንያም በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ለመሰማራት ፍላጎቱ አለው። በሞዛምቢክ፣ ቡሩንዲ፣ ካሜሩን እና ታንዛኒያ ገበያዎች የሚሰራው የቪየትናም ኩባንያ ቪቴል ጭምር ወደ ኢትዮጵያ ማማተር መጀመሩን ሬውተርስ ዘግቧል።
እነዚህ ኩባንያዎች ያሰቡት ተሳክቶ ከኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ ቢገዙ ምን ይዘው ይመጣሉ? ዶክተር አብዱልቃድር ሙደሲር ኩባንያዎቹ ካላቸው ዓለም አቀፍ ልምድ ኢትዮጵያ ልትጠቀም እንደምትችል ዕምነት አላቸው። 

ከ60 ሚሊዮን በላይ የሞባይል ስልክ ደንበኞች አሉኝ የሚለው ኢትዮ-ቴሌኮም በምን አይነት አደረጃጀት ድርሻዎች እንደሚሸጥ የታወቀ ነገር የለም። ቢኤምአይ የተባለው የጥናት ተቋም የቴሌኮምዩንኬሽን ጥናት ኃላፊው አንድሪው ኪትሰን "ኩባንያው ምን ያክል ትልቅ እንደሆነ ምን ያክል እዳ እንዳለበት፤ ድክመቶቹ ምን እንደሆኑ የምናውቀው ነገር የለም። የምናውቀው ምን ያክል ደንበኞች ብቻ እንዳሉት ነው" ሲሉ ተጨማሪ መረጃ እንደሚያስፈልግ ለሬውተርስ ተናግረዋል። 

ዶክተር ቴዎድሮስ ግን ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ የቴሌኮም ገበያን ለውድድር ለመክፈት ዝግጁ አይደለችም የሚል አቋም አላቸው። የተቋሙን አሰራሮች የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚከተላቸው ፖሊሲዎች ጋር እያነፃጸሩ የሚያስተነትኑ ጥናታዊ ፅሁፎች ያዘጋጁት ባለሙያው ከትርፍ ባሻገር የሕዝብን ጥቅም ማስጠበቅ ይገባል ሲሉ ይናገራሉ። 

የቀድሞ ሠራተኞች፣ ቀረብ ብለው ያጠኑት ባለሙያዎች ጭምር የኢትዮ-ቴሌኮም «የፖለቲካ መሳሪያ» ተብሎ የሚታማ ተቋም እንደሆነ ይናገራሉ። በተቋሙ «ሠራተኞች ያለ ዕቅድ ይቀጠራሉ፤ ያለ ዕቅድ ይባረራሉ» እየተባለም ይተቻል። ከ60 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ይዞ በጎረቤት አገራት በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ያነሰ ገቢ በሚያስገባው ኩባንያ ላይ ተግባራዊ የሚሆነው ውሳኔ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ይነካል። እንደ ዶክተር ቴዎድሮስ ያሉ ባለሙያዎች ውሳኔው ለሌላ የኢ-ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል መነሻ እንዳይሆን ሥጋት አላቸው። 
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ