1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሕዴግ የ«ውኅደት» ሒደትና ኦዲፒ

ዓርብ፣ ኅዳር 5 2012

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሊወሀድ ነው መባሉን ተከትሎ ከግንባሩ አባል ድርጅቶች አንዱ በሆነው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ውስጥ ክፍፍል መፈጠሩ ተሰምቷል። ምንም እንኳን ፓርቲው ያን ቢያስተባብልም። የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እና አንድ የፖለቲካ ተንታኝን ዶይቸ ቬለ(DW) አነጋግሯል።

https://p.dw.com/p/3T7Ux
Taye Dendea
ምስል Geberu Godane

ውህደቱ እና ኦዲፒ

በኢትዮጵያ ላለፉት 28 ዓመታት መንበረ-ሥልጣኑን ተቆጣጥሮ የቆየው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የግንባርነት ጉዞውን ጨርሶ የፖለቲካ ርዕዮቱንም ቀይሮ አንድ ወጥ አገራዊ ፓርቲ ለመሆን የውኅደት ጉዞ መጀመሩን የግንባሩ ጽሕፈት ቤት ዛሬ ዐስታውቋል።

የግንባሩ ውህደት በመጪው የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ አዲስ ነገር ይዞ እንደሚመጣ፤ ተስፋ እና ስጋቶችም ስለመኖራቸው ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተነገረ ነው። ኢህአዴግ ወደ ውህደቱ የመጨረሻ መድረክ ከመድረሱ በፊት በኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ውስጥ በአመራሩ መካከል የሃሳብ ልዩነት መንጸባረቁ ተገልጧል። ያን ተከትሎም በግንባሩ የውህደት ሂደት ላይ አሉታዊ አስተዋጽዖ ሊኖረው ይችላል የሚሉ ግምቶች ሲሰነዘሩ ተስተውሏል።

የኦዲፒ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ ግን ለዚህ ሃሳብ መልስ ሲሰጡ በኦዲፒ ውስጥ የግንባሩን መዋሀድ በተመለከተ በሥራ አስፈጻሚውም ሆነ በማዕከላዊ ኮሚቴው ሙሉ ድጋፍ የተቸረው ነው በማለት ከውጭ የሚወራው ውሸት ነው ሲሉ አጣጥለዋል። «በዚህ ጉዳይ ላይ የተፈጠረ ልዩነት የለም ። በውጭ የሚነዙ አሉባልታዎች በኦዲፒ ክፍፍል አለ፤ እገሌ እንደዚህ ብሏል የሚባለው ነገር ውሸት ነው። ፓርቲው በመዋቅሩ መሠረት ተወያይቶበት ሥራ አስፈጻሚው እና የማዕከላዊ ኮሚቴው በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።»

የኦሮሞ ህዝብን መሠረት ያደረገውን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት እና በመተንተንም ጭምር የሚታወቁት ዶ/ር ፍርዲሳ ጀቤሳ በአቶ ታዬ ሃሳብ አይስማሙም። እርሳቸው የ«ኦሮሙማ» ወይም ኦሮሞነት አስተሳሰብ ያላቸው የድርጅቱ አመራሮች የውህደት እንቅስቃሴውን እንደተቃወሙት አስረግጠው ይናገራሉ። «ከበላይ ኾኖ ዳቦ ሊጨምርልህ የሚችል ሰው ማነው? ስለዚህ እሱን አትቋቋምም እንጂ በአስተሳሰባቸው ላይ በተለይ ደግሞ ኦሮሙማ ያለባቸው ሰዎች ይህን አልተቀበሉትም።»

የኢህአዴግ ውህደት በክልሎች ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መሠረትን በተመለከተ፤ በተለይም የውህደቱ አካል ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት እና ቀደም ሲል አጋር የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸው የነበሩ ፓርቲዎች በውህደቱ የሚሳተፉበት ሂደትም ጥያቄን አስነስቷል። አቶ ታዬ ደንደአ ለዚህ ሲመልሱ፦ ሂደቱ የክልል መንግሥታትን አቅም በማሳደግ የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንጂ በስጋት መታየት የለበትም ብለዋል።
«በሕገ መንግሥቱ መሰረት ለክልሎች የተሰጠ መብት እና ስልጣን አለ። እነዚያ ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲተገበሩ እናደርጋለን።» የፖለቲካ ተንታኙ ዶ/ር ፍርዲሳ ጀቤሳ ግን ከዚህ የተሻለ አማራጭ ነበር ይላሉ ። ግንባሩን አፍርሶ ከማዋሀድ እዚያው ባለበት የማጠናከር ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባ ነበርም ባይ ናቸው።

«አሁን መደረግ የነበረበት ኢህአዴግን አዋህዶ ቁመናቸውን ሳይቀይሩ በሕዝብነታቸው ሳይዋሀዱ ማድረግ ይቻል ነበር።» ኢህአዴግ  ግንባር ኾኖ ይቆይ የሚለውን የተቃውሞ  ሐሳብ እንደ

ዶ/ር ፍርዲሳ ሁሉ የኢህአዴግ መስራች እና አባል ድርጅት የሆነው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)ም በተደጋጋሚ ሲያሰማ ነበር። ውኅደቱን በተመለከተ ሕወሓት የያዘው አቋም ትክክለኛ ውሳኔ ነው ሲሉ ዶ/ር ፍርዲሳ  አሞግሰውታል። ቀደም ሲል እንጠላቸው የነበሩትን የቀድሞውን ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን የምናመሰግንበት ጊዜ ላይ ደርሰናልም ብለዋል። በተያያዘ የህወሓት ከግንባሩን ውህደት ራሱን ለማግለል ያየያዘውን አቋም በተመለከተ ፓርቲያቸው ቀለል አድርጎ የማይመለከተው መሆኑን አቶ ታዬ  ደንደአ ለዶቸ ቨሌ ተናግረዋል።

«ይኸ ምንም ችግር አይፈጥርም አይባልም። የሚፈጠሩ ጥቃቅን ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ከዚህ በፊት በነበረው መዋቅር የተጠቀመ የነበረያለ አግባብ ሌላውን የበታች እሱ ጌታ ሆኖ የነበረ ድርጅት ይኽንን እስኪቀበል ከጠበቅን ያው ዘመናት ሊያልፍ ስለሚችሉ ያንን መጠበቅ አንችልም ማለት ነው።» የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነገ ቅዳሜ ኅዳር 6 2012 ቀን ስብሰባውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ