1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሕአዴግ ውሕደት የመጨረሻ ምዕራፍ 

ሐሙስ፣ ኅዳር 18 2012

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) እና እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ብልጽግና የተባለውን የአዲሱን ዉሕድ ፓርቲን መመስረት ከማፅደቃቸዉ በፊት ከውህደት በኋላ ሊገጥሟቸው በሚችሉ ተግዳሮቶች ላይ ከአባላቶቻቸው ጋር መምከራቸውን በየፊናቸዉ አስታወቁ።

https://p.dw.com/p/3TuJ5
EPRDF Logo

«ግንባሩ አሁን ወደ አንድ ፓርቲ መለወጡ ቢዘገይ እንጂ አልፈጠነም»

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) እና እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ብልጽግና የተባለውን የአዲሱን ዉሕድ ፓርቲን መመስረት ከማፅደቃቸዉ በፊት ከውህደት በኋላ ሊገጥሟቸው በሚችሉ ተግዳሮቶች ላይ ከአባላቶቻቸው ጋር መምከራቸውን በየፊናቸዉ አስታወቁ። እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያን የሚገዛዉ የአራት ፓርቲዎች ሕብረት (ኢህአዴግ) ፤ ግንባር ሆኖ ለበርካታ አመታት መቆየቱ ተገቢ እንዳልነበር አንድ የህግ ምሁር ተናግረዋል። የሕግ ምሁሩ እንዳሉት ግንባሩ አሁን ወደ አንድ ፓርቲ መለወጡ ቢዘገይ እንጂ አልፈጠነም።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) እና እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ጠቅላላ ጉባኤዎች ፓርቲዎቻቸውን አክስመው አዲሱን የብልጽግና ፓርቲ መዋሃዳቸውን አስታውቀዋል።
ፓርቲዎቹ ባላፈዉ ማክሰኞ እና ረቡዕ፣ አዳማ እና ባህርዳር ባካሄዷቸው ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔዎች ቀደም ሲል ብልጽግና ፓርቲን ለመዋሃድ የየፓርቲዎቹ ማዕከላዊ ኮሚቴ የወሰነዉን አፅድቀዋል።

ሌላዉ የኢህአዴግ አባል ድርጅት ደኢህዴን ብልጽግና ፓርቲን ለመዋሃድ የሚያስችለውን ዉሳኔ ለማፅደቅ ጠቅላላ ጉባዔው ዛሬ ሐዋሳ እየተወያየ ነዉ። በስራ አስፈጻሚ እና በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ውህደቱን ተቃውሞ የነበረው ሕወሓት ለመጨረሻ ውሳኔ ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚጠራ በሊቀመንበሩ በኩል አስታውቆ የነበረ ቢሆንም እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ቀደም ሲል የኢህአዴግ አጋር በመባል ይታወቁ የነበሩት ሶዴፓ ፣ አብዴፓ ፣ ቤጉአዴፓ፣ ጋሕአዴን እና ሐብሊ የብልጽግና ፓርቲን መቀላቀላቸውን ሰሞኑን አስታውቀዋል።
በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ኦዲፒ እና አዴፓ ወደ ውህደት ለመምጣት በየደረጃው ሲደረጉ በነበሩ ውይይቶች በአመራሩ እና በጉባዔ አባላት መካከል ልዩነት እና መከፋፈል መፈጠሩ ሲነገር ነበር ።

ኦዲፒ ለሁለት ቀናት ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔው በውህደቱ ውስጥ ሊያጋጥሙ ይችላሉ የተባሉ ስጋቶች ተነቅሰው በውይይት ስምምነት ላይ ከመደረሱ ያለፈ መከፋፈል አለመኖሩን የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት እና አስተያየት ጉዳይ ሃላፊው አቶ ታዬ ደንደኣ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

“አንዳንድ ብዥታዎች ነበሩ ፤ አንደና ከፌዴራል አወቃቀሩ ጋር እንዴት ይታያል የሚል ጥያቄ ያነሱ ጓዶች ነበሩ። በዚያ ላይ ግልጽ የሆነ መልስ ተሰጥቷል። የፓርቲ መዋቅር እና የፌዴራል መዋቅሩ ፈጽሞ ሊገናኙ እንደማይችል እስካሁን የመጣንበት የፌዴራል ስርዓቱ ከዚህ በፊት የነበሩ ጉድለቶችን በሟሟላት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በግልጽ ተቀምጧል።

Äthiopien vor der Wahl EPRDF Anhänger in Addis Abeba
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

“አዴፓም በተመሳሳይ አዲሱን ብልጽግና የተባለውን ፓርቲ ከመዋሃዱ በፊት በሂደት ሊያጋጥሙ ይችላሉ በተባሉ ስጋቶች ላይ በመምከር ውህደቱን ማጽደቁን የፓርቲው የአደረጃጀት ሃላፊ አቶ አብረሃም አለኸኝ ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። አቶ አብረሃም በድርጅታዊ ጉባዔው በትኩረት የ,ተመከረባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ከማንሳት ግን ተቆጥበዋል።

“የአብዛኞቹ ሃሳብ ከትክክለኛ የህገ መንግስት ስርዓት ፣ከትክክለና የፌዴራሊዝም ስርዓት ለሀገር እና ለሕዝብ ከሚመጥን የፖለቲካ አስተሳሰብ እንደዚሁም ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ የተረዳ በተለይም ደግሞ እንደ ሀገር የደረሰውን ስብራት ሊጠግን የሚችል የፖለቲካ ፕሮግራም ነድፈን ወደ ስራ መግባት አለብን የሚለው ሀሳብ ብዙ ጉዳዮችን መዘን እንድንወያይ የሚያደርግ እና የሚያስገድድ ነው። “  

ኦዲፒ እና አዴፓ ቀደም ሲል በየክልሎቻቸው ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት ከስምምነት የተደረሱ ጉዳዮችን በተመለከተ ውህደቱ ምንም ተጽዕኖ እንደማይኖረው አቶ ታዬ ደንደአ እና አቶ አብረሃም አለኸኝ ገልጸዋል።

በኢህአዴግ ድርጅቶች እና በአጋር ፓርቲዎች ወደ ብልጽግና ፓሪቲ የሚደረገው የውህደት ሂደት በፍጥነት መከናወኑ ለምንድነው ሲሉ የተለያዩ ሃሳቦች በብዙሃን መገናኛም ሆነ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲ,መላለስ ይታያል ፤ ይሰማል። ይህንኑ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር እና የወቅቱን የፖለቲካ ሂደት የሚከታተሉት አቶ ስሜነህ ኪሮስ እንዳሉት ኢህአዴግ ግንባር ሆኖ ያለፉትን ሶስት አስርት አመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሀገሪቱን መምራቱ ተገቢነት አልነበረውም። 

“ኢሕአዴግ ከስሙም እንደምንረዳው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ነው የሚለው። 29 ዓመት ያህል አስተዳድሯል። ግንባር ሆኖ ይህን ያህል ዘመን ማስተዳደሩ በእውነት አስደናቂ ነው። እንግዲህ ለምርጫም ሲወዳደር የቆየው ኢሕአዴግ ሆኖ ነው። ግንባር ሆኖ ነው እንጂ ፓርቲ ሆኖ አልነበረም። ስለዚህ ከሽግግር ጊዜ በኋላ ግንባር መቀጠል አልነበረበትም። ውህደቱ ቢዘገይ እንጂ ፈጥኗል ሊባል አይችልም።“

እንደተባለው ኢህአዴግ ከስሞ ብልጽግና የተባለው አዲሱ ፓርቲ መመስረቱ እውን ከሆነ መንግስታዊ ስልጣን ይዞ የመቀጠል ህጋዊ መሰረት ባይኖረውም የሁኔታዎች አስገዳጅነት ምርጫ እስኪከናወን መንግስት ሆኖ መቀጠል እንደሚችል አቶ ስሜነህ አስረድተዋል። “አዲስ ነው ከተባለ ፣ በፊት ተመርጦ የነበረው ኢህአዴግ ነው ከተባለ ይኸኛው ምን ይሁን የሚለውን ጥያቄ ከህግ አንጻር ሳይሆን እንዲህ ተጨባጭ ችግር ሲገጥም መፍትሔ በሚሰጥበት አይነት ነው የምናየው“ 

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ዛሬ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክታቸው የብልጽግና ፓርቲ እንዲመሰረት የቄሮ እና ፋኖ እና ዘርማ ለበረከቱት አስተዋጽዖ መታሰቢያ እንደሚያቆሙላቸው ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠቅላላ ጉባዔውን በማድረግ ላይ የሚገኘው ደኢህዴን የብልጽግና ፓርቲን እንደሚዋሃድ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ