1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብልፅግና ፓርቲ እና ሕወሓት

ሰኞ፣ ኅዳር 8 2012

አንዳዶች እንደሚሉት ሕወሓት አብዛኞቹን የኢሕአዴግ አባልና አጋር ፓርቲዎችን በመፈንስም፣በአካልም፣ በስምም፣ በምግባርም ባምሳያዉ የፈጠረ ፓርቲ ነዉ።እራሱ የፈጠረ፣ ያደራጀና የመራቸዉ የፖለቲካ ማሕበራት አንድ እንሁን ሲሉ አንድነቱን የተፃረረበት  ምክንያት ያጠያይቃል።

https://p.dw.com/p/3TFqJ
Äthiopien |  Abstimmung EPRDF
ምስል EPRDF

የብልፅግና ፓርቲ ምስረታ፣ የሕወሓት ተቃዉሞ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)ን የመሠረቱት የፖለቲካ ማሕበራት እንደ አማፂ ቡድናትም ሆነ እንደ ገዢ ፓርቲ፣ በተናጥልም ሆነ እንደ ግንባር የቀየሱትን ዓላማ መርሕ ከግብ ማድረስ-አለማድረሳቸዉ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መጠቅም-አለመጥቀማቸዉ እንደ ዛሬ እስከዛሬዉ ሁሉ ወደፊትም ማነጋገሩ አይቀርም።ኢትዮጵያን ለ29ኝ ዓመታት የገዛዉ ግንባር ግን ሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴዉ እንደወሰነዉ የ31 ዓመታት የአብዮታዊ ዴሞክራሲዊ ግንባርነት ጉዞዉ አክትሟል።ግንባሩን የመሠረተዉ፤ የተቀሩትን የግባሩን አባላትና አጋር ፓርቲዎች በባሕሪ-አካል አምሳያዉ «ፈጥሯል» የሚባለዉ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)ዉሕደቱን መቃወሙ ብዙዎችን አንድም ሴራ፣ ሁለትም እንቆቅልሽ ሶስትም ጉድ፣ አጃኢብ እያሰኘ ነዉ።ዉሐደቱ መነሻ፣ የ31 ዓመቱ ጉዞ ማጣቀሻ፣ የአዲሱ ፓርቲ ዓላማና የሕወሓት ተቃዉሞ መድረሻችን ነዉ። ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

መጀመሪያ፣ ከአንድ የምክር ቤት እንደራሴ ሌላ የትግራይ ተማሪዎች ነበሩ።ተማሪዎቹም አሉ «ማሕበር ገስገስቲ ብሔር ትግራይ «Association of Progressives of the Tigray Nation» መሠረትን።ብዙም አልቆዩ ለትግራይ ግስጋሴ፣ ዕድገት እንበለዉ ብልፅግና ያለመዉ ማሕበር ለትግራይ ነፃነት በነፍጥ ወደሚፋለም፣ ኮሚንዝምን ወደሚያቀነቅን የፖለቲካ ፓርቲነት ለወጡት።ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)ን መሠረቱ።ደደቢት።የካቲት 1967።

ኢትዮጵያ በአብዮት ፀረ-አብዮት ቀዉስ በምትናጥበት በዚያ ዘመን ለትግራይን ነፃነት ለመዋጋት ደደቢት-የሸመቀዉ ሕወሓት ከሱ በፊት እዚያዉ ትግራይ የሸመቁና ትግራይ ዉስጥ የሚዋጉ አፍቃሬ ትግራይና አፍቃሬ ኢትዮጵያ ፓርቲዎችን በፖለቲካ ሴራ፣ ሻጥርም በጦር ኃይልም ተራ በተራ እየመታ ከትግራይ ጠራርጎ ለማስወጣት ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም።

EPRDF Logo

በሕወሓት ዱላ ከተፈረካከሱት ሸማቂዎች መሐል ከኢሕአፓ የወጣዉ የኢትጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) በ1975 ግድም ዋግሕምራ-ወሎ ላይ ሲመሰረት እስከዚያ ጊዜ ድረስ የሰባት ዓመት የጦር ልምድ፤ የብሔረተኝነት ፖለቲካ፣ ሴራ ሽጥሩንም ያዳበሩት የሕወሓት መሪዎች ወደፊት ለሚያማትሩት ከፍ ያለ ዓላማና ሥልጣን ጠቃሚ ነዉ በሚል በቅርብ ሳይከታተሉት አልቀረም። ኢሕድን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከንቅናቄዉ መሪዎች ገሚሱን በመርዳት፣በማባበል፣ በማማለልም አግባብተዉ ከስድት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን ለ29 ዓመታት የገዛዉን ግንባር መሠረቱ።ስሙንም፣ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አስቀድመዉ በዓላማ-መርሐቸዉ ሰየሙት።የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ብለዉ።1981።

ኢሕአዴግ ደርግን ካስወገደ ከ1983 ጀምሮ እስከ 2010 ድረስ ሕወሓት ኢትዮጵያን በቀጥታም በተዘዋዋሪም ገዝቷል።ትግራይን ደግሞ አሁንም እየገዛ ነዉ።ኢሕአዴግ የግንባሩ ሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈዉ ቅዳሜ በመወሰነዉ መሠረት የግንባርነት ጉዞዉን ለማጠናቀቅ እነሆ ከመጨረሻዉ መጀመሪያ ላይ ደርሷል።

ዶክተር አረጋዊ በርሔ እንደ እስከ ቅርብ ጊዜዉ ስደተኛ፤ እንዳሁኑ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዶክተርም ሳይሆኑ የማሕበር ገስግስቲ ብሔረ ትግራይም፤ የሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይም መሥራች ናቸዉ።የመሰረቱት ማሕበር እንደ አማፂ ቡድንም እንደ ገዢ ፓርቲም 45 ዓመታት ገቢር ያደረገዉ ዓላማ መርሑ ከግብ ደርሶለት ይሆን?አቶ ያሬድ ጥበቡ የኢሕአፓ ታጋይ፣ የኢሕዴን መሥራችም ነበሩ።የመሰረቱት ፓርቲ ሁለቴ ስሙን ለዉጧል።ከኢትዮጵያዊነት ወይም ከሕብረ-ብሔር ፓርቲነት ወደ አማራ ፓርቲነት ዝቅ ብሏል።የኢሕአዴግ የ31 ዓመት ጉዞ-ከፍፃሜዉ ሲደርስ ዛሬ ኢሕዴን በተናጥል ወይም እንደ ኢሕዴግ አባል  ዓላማዉን ከግብ አድርሶት ይሆን? አቶ ያሬድ «አይ-አዎ» ይላሉ።

Äthiopien |  Abstimmung EPRDF
ምስል EPRDF

ቅዳሜ አዲስ አበባ የተሰየመዉ የኢሕአዴግ ሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ በአብላጫ ድምፅ ያሳለፈዉ ዉሳኔ በግንባሩ ማዕከላዊ ኮሚቴና ጠቅላላ ጉባኤ ከፀደቀ ኢሕአዴግን የሚተካዉ ዉሑድ ፓርቲ «የብልግና ፓርቲ» ነዉ-የሚባለዉ።እነ አረጋዊ በርሔ የመሯቸዉ የያኔ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የመሰረቱት ማሕበር ግስግስቲ ነበር ስም-ዓላማዉ።እርግጥ ነዉ የጥንቱ «የብሔረ ትግራይ«፣ ያሁኑ «የኢትዮጵያ» የማለታቸዉ ልዩነት ግልፅ ነዉ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃዋሚ ይባሉ ገዢ፣ አማፂ ይሁኑ ሰላማዊ፣ ብዙ ጊዜ የሚይዟቸዉ ስም ዓላማዎች ድሮም፣ በመሐሉም፣ ዛሬም ግስጋሴ፣ እርምጃ፣ እድገት፣ብልፅግና፤ ነፃነት፣ ዴሞክራሲ፣ አንድነት ወዘተ በሚሉ ቃላት ማሸብረቃቸዉ፣ እስከ ዛሬ የተደረጉ ትግሎች፣የተከፈሉ መስዋዕትነቶች፣ የጠፋዉም ጊዜ ኢትዮጵያዊዉ ለዘመናት የሚመኘዉን አለማስገኘታቸዉን ባያረጋገጡ ጠቋሚዎች ናቸዉ።

አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘዉ አምደ መረብ የለጠፈዉ የብልፅግና ፓርቲ ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ እንደሚመለዉ የፓርቲዉ መርሕ ኢሕአዴግ እስካሁን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ያልመለሳቸዉን፣የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ፣የአንድነት ጥያቄዊችን አካትቷል።

የፓርቲዉ መርሕ ከወረቅት ማለፍ-አለማለፉ በርግጥ ወደፊት የሚታይ ነዉ።ወረቀት ላይ ግን ሕዝባዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነት፣ የሕግ የበላይነት ፤ ተግባራዊ እዉነታ፣ ሐገራዊ አንድነትና ሕብረ-ብሔራዊነት ተብሎ ተዘርዝሯል።ኢሕአዴግን የሚተካዉ ፓርቲ ዓላማ መርሁን ገቢር አደረገም አላደረገ፣ አቶ ያሬድ እንደሚሉት፣ ግንባሩ እንዲዋሐድ እራሳቸዉን ጨምሮ ከዉጪም ከዉስጥም የተለያዩ የፖለቲካ ኃይላት ግፊት ሲያደርጉ ነበር።«ግን አሁን አልነበረም።» ይላሉ።

የብልፅግና ፓርቲ ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 8 ቁጥር 1 ላይ ባንድ አረፍተ-ነገር እንደጠቀለለዉ የፓርቲዉ ዓላማ፣-«ጠንካራ ዴሞክራሲዊና ቅቡልነት ያለዉ ዘላቂ ሐገረ-መንግስት እና ልማትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አካታች የኤኮኖሚ ስርዓት መገንባት እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልፅግናን የሚያሰፍን ማሕበራዊ ልማት ማረጋገጥ እና ሐገራዊ ክብርን ማዕከል ያደረገ የዉጪ ግንኙነት ማካሔድ ነዉ።»

Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

ይሕን ዓላማ ያነገበ ዉሕድ ፓርቲ መመስረቱን ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ መቃወሙ በርግጥ ለብዙዎች ግራ ነዉ።አንዳዶች እንደሚሉት ሕወሓት አብዛኞቹን የኢሕአዴግ አባልና አጋር ፓርቲዎችን በመፈንስም፣በአካልም፣ በስምም፣ በምግባርም ባምሳያዉ የፈጠረ ፓርቲ ነዉ።እራሱ የፈጠረ፣ ያደራጀና የመራቸዉ የፖለቲካ ማሕበራት አንድ እንሁን ሲሉ አንድነቱን የተፃረረበት  ምክንያት ያጠያይቃል። የሕወሐት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የትግራይ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ እንደሚሉት ግን ሕወሓት ዉሕደቱን የተቃወመዉ በተዋሐጅ ፓርቲዎች መካከል የዓላማ አንድነት ስለሌለ ነዉ።

ሕወሓት፣ ግንባሩ እንዲወሐድ ከብዙዎቹ ድርጅቶች ቀድሞ የጣረ መሆኑን የሚያዉቁ ደግሞ የትግራዩ ገዢ ፓርቲ ዉሐደቱን እንቢኝ ያለዉ ከሥልጣን ስለተገፋ ነዉ ይላሉ።ወይም ሴራና ሻጥር።ዶክተር አረጋዊ በርሔ አንዱ ናቸዉ።

የሕወሓት እና የዉሕዱ ወይም የብልፅግና ፓርቲ ግንኙነት ምናልባት የተቃዋሚና የገዢ፣ ምናልባት እስከሚቀጥለዉ ምርጫ ድረስ ድጋፍ የማሰባሰብ ተሻሚዎች ሽኩቻ፤ ምናልባት የጠላትነት ሊሆን፣ ላይሆንም ይችላል።አቶ አማኑኤል ግን ሕወሓት ኢሕአዴግ ላይ የቆመ ድርጅት አይደለም ይላሉ።

የብልፅግና ፓርቲስ? የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ይቆም ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ