1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሕአዴግ እና አጋር ፓርቲዎች ውህደት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 16 2012

የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ) ከብልጽግና ፓርቲ ጋር እንደሚዋሐድ አስታወቀ። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አባል የሆነው አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ፓርቲዉ የብልጽግና ፓርቲን ለመዋሐድ በሚያስችለዉ ሐሳብ ዛሬ ሲነጋገር ዉሏል።

https://p.dw.com/p/3TmBr
Karte Sodo Ethiopia ENG

በፓርቲው ፕሮግራም ላይ ተወያይቶ ውህደቱን ተቀብሎአል

 

የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ) ከብልጽግና ፓርቲ ጋር እንደሚዋሐድ አስታወቀ። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አባል የሆነው አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ፓርቲዉ የብልጽግና ፓርቲን ለመዋሐድ በሚያስችለዉ ሐሳብ ዛሬ ሲነጋገር ዉሏል።የብልፅግና ፓርቲን እስካሁን ያልተቀየጠዉ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በበኩሉ ሥለ ዉሕደቱ ለመወሰን የድርጅቱን ጠቅላላ የጉባኤ እንደሚጠራ አስታውቋል ።  
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አባል ከሆኑት አራት ድርጅቶች ውስጥ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ድርጅታዊ ጉባኤውን ዛሬ መጥራቱን አስታውቋል። ኢሕአዴግ ተዋህዶ የሚመሰረተውን አዲሱን የብልጽግና ፓርቲ በድርጅታዊ ጉባኤ ለማስወሰን ይህ የመጨረሻ ምዕራፍ ነው ተብሎለታል። ሌላኛው የኢህአዴግ አባል ድርጅት ህወሃት ትላንት በሰጠው መግለጫ በብልጽግና ፓርቲ ላይ ውሳኔ ለማሰለፍ ድርጅታዊ ጉባኤ እንደሚጠራ ገልጿል። 
አዴፓ በፌስ ቡክ ገጹ ዛሬ እንዳስታወቀው ዛሬ ከሰዓት በሚጀመረው ድርጅታዊ ጉባኤው በኢህአዴግ ምክር ቤት የተቀመጠውን የውሳኔ አቅጣጫ መሰረት በማድረግ በአዲሱ የብልጽግና ፓርቲ ህገ-ደንብ፣ ፕሮግራም፣ አሰራር እና አደረጃጀት ላይ ውሳኔ ያሳልፋል። በዚህ ጉባዔው ውህደቱ ሊጸድቅ እንደሚችልም አዴፓ አመልክቷል።
በአንጻሩ በግንባሩ ውስጥ ለ27 ዓመታት ገደማ የመሪነት ሚና ነበረው የሚባልለት ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በስራ አስፈጻሚው እና በማዕከላዊ ኮሚቴው ውህደቱን ከተቃወመ በኋላ የድርጅቱን የጉባኤ አባላት ለመጨረሻ ውሳኔ ለስብሰባ እንደሚጠራ የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ትላንት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
“ የውሳኔውን ኺደት ጀምረነዋል እንጂ አላለቀም። ለኢሕአዴግም እናሳውቃችኋለን ብለናቸዋል። የመጨረሻው ውሳኔ በጉባዔ ይደረሳል። ሕዝብም እንጨምራለን። ስለዚህ በእኛ በኩል ቶሎ ጉባዔ ለመጥራት ወስነናል።”
ኢህአዴግን በማዋሃድ ስም እየተሰራ ያለው ስራ እንደተባለው ኢህአዴግን ለማዋሃድ ሳይሆን አዲስ ፓርቲ የመመስረት ስራ እየተሰራ መሆኑን እንደሚያምኑም ዶ/ር ደብረጽዮን ገልጸዋል። ነገር ግን ሕወሓት ጠቅላላ ጉባኤውን መቼ እንደሚጠራ የተገለጸ ነገር የለም። የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች የሆኑት ኦዲፒ እና ደኢህዴን የግንባሩን ውህደት ቀደም ሲል በስራ አስፈጻሚ እና በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ቢያጸድቁም ለየጉባኤዎቻቸው መቼ እንደሚያቀርቡ እስካሁን በግልጽ አላሳወቁም።
በሌላ በኩል የኢህአዴግ አጋር ይባሉ የነበሩ ፓርቲዎች ወደ ውህደቱ መቀላቀላቸውን እያስታወቁ ነው። የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ)፣ የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕአዴን)፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉሕዴፓ) ሰሞኑን ባካሄዷቸው አስቸኳይ ጉባኤዎቻቸው የኢሕአዴግ እና አጋር ፓርቲዎችን ውህደት መቀበላቸውን አስታውቀዋል። የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ) በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደረጃ ዛሬ ተመሳሳይ ውሳኔ አሳልፏል። 
የሶዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ ባካሄደው ስብሰባው በውህድ ፓርቲው ህገ- ደንብ እና በፓርቲው የፖለቲካ ፕሮግራም ላይ ተወያይቶ ውህደቱን መቀበሉን አስታውቋል። ፓርቲው ቀደም ሲል በማዕከላዊ ኮሚቴው ውህደቱን በተመለከተ በመርህ ደረጃ ከተቀበለ በኋላ በሁለት ጉዳዮች ላይ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ መልስ ሲጠብቅ እንደነበር የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽቤት ሃላፊ አቶ መሐመድ ሻሌ ለዶይቸ ቬለ«DW»ተናግረዋል።
“ከዚህ በፊት በመርህ ደረጃ ውህደቱን እንደሚቀበል እና አንዳንድ መስፈርቶችን ማሟላት አለበት ብሎ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያስቀመጣቸው ነገሮች ነበሩ። እነዚያም አንደኛ አሁን ያለው የፌዴራል ስረዓት እና ፌዴራሊዚሙ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፤ ሁለተኛ የሶማሊኛ ቋንቋ በሀገራዊ የፓርቲው ቋንቋዎች ውስጥ መኖር አለበት የሚሉትን ያገናዘበ ነው ወይ የሚል ነበር ። የተቀመጡ ቅድመ ኹኔታዎችን ያሟላ እና የፖለቲካ ፕሮግራም እና በህገ ደንቡ በግልጽ እንደተቀመጡ በሰፊው ከተወያየን በኋላ በሙሉ ድምጽ ውህደቱን አጽድቋል። ”
ሶዴፓ በነገው ዕለት ውሳኔውን ለማዕከላዊ ኮሚቴ በማቅረብ እንዲጸድቅ ካደረገ በኋላ ለጠቅላላ ጉባኤ እንደሚያቀርብ አቶ መሐመድ ገልጸዋል። በአሶሳ ከተማ ትላንት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ውህድ ፓርቲውን መቀላቀሉን ይፋ ያደረገው የቤጉሕዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አሻድሊ ሀሰን በሀገሪቱ ውስጥ በሚከናወኑ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በባለቤትነት ለመሳተፍ ፓርቲያቸው ብልጽግና ፓርቲን መቀላቀሉን አስታውቀዋል።
“ይኽ ውህደት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት በሚደረገው ሀገራዊ የጋራ ጥረት ውስጥ በባለቤትነት መንፈስ የመሳተፍ ዕድል የሚያሰፋ ከመሆኑ ያለፈ ራስን በራስ የማስተዳደር እና የመምራት ሕገ መንግስታዊ መብታችንን ይበልጥ በማጠናከር እና ከሌሎች የሀገራችን ሕዝቦች ጋር ያለንን አንድነት እና ሕብረት በማጥበቅ በኺደት አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የበኩላችንን ሚና እንድንወጣ የሚያደርግ ነው።” በተመሳሳይ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ) መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ በሐረር ከተማ ማካሄድ መጀመሩን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 
ታምራት ዲንሳ


ተስፋለም ወልደየስ