1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሕአዴግ ሥንብት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 27 2012

ኢሕአዴግ ከ30 ገደማ የሥልጣን አመታት በኋላ ፈረሰ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ከኢሰፖ ቀጥሎ የመንግሥት ሥልጣን በመያዝ ኢሕአዴግ ሁለተኛው ነበር። ለመሆኑ በ2007 ምርጫ የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶችን የጠቀለለ ኢሕአዴግ በምርጫ ሳይሸነፍ፣ ፖሊሲ ሳይለውጥ እንዴት ለዚህ በቃ?

https://p.dw.com/p/3Vlnc
EPRDF Logo

የኢሕአዴግ ሥንብት

ህወሓት በ45 አመታት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የጠራው አስቸኳይ የጠቅላላ ጉባኤ መቐለ በሚገኘው ሐውልቲ አዳራሽ ሲካሔድ መሰብሰቢያው በቀይ ቀለም ደምቆ ነበር። የአዳራሹ ወንበሮች ቀይ ናቸው። የጉባኤው ተሳታፊዎች ከአንገታቸው ጣል ያደረጓቸው ስካርፎች ቀይ ናቸው። "ውግንናችን ለህዝባችን እና መስመራችን" እንዲሁም "ሁሉ ተግባራችን ለህዝባችን ደህንነት እና ህልውና" የሚሉትን ጨምሮ በርከት ያሉ መፈክሮች በአዳራሹ ግድግዳዎች ይታያሉ። ከመድረኩ ጀርባ ህወሓት ደርግን ለመጣል ለአስራ ሰባት አመታት ባደረገው ትግል ሕይወታቸውን የገበሩ ታጋዮች ፎቶ ግራፎች ይታያሉ።

አንድ ሺሕ ስልሳ ስድስት ድምፅ የመስጠት መብት ያላቸው የህወሓት አባላት የተሳተፉበት ጠቅላላ ጉባኤ ሲጠናቀቅ ያወጣው መግለጫ ግንባሩ ኢሕአዴግ ፈርሶ ከተቋቋመው ብልፅግና ፓርቲ እንደማይቀላቀል አስታውቋል። ያለ ምንም ተቃውሞ እና ያለ አንዳች ድምጸ-ተዓቅቦ በጉባኤው የጸደቀው የውሳኔ ሐሳብ ኢሕአዴግን አፍርሶ አዲስ ፓርቲ መመሥረት "ታሪክ የማይረሳው ስህተት" ነው ብሏል። ውሳኔው ከዚህ ቀደም በህወሓት ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ከተላለፈው የተስማማ ነው። 

በጉባኤው ጅማሮ ንግግር ያደረጉት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ደብረጺዮን ገብረ-ሚካኤል ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ጋር በመሆን ኢሕአዴግን የመሠረተው የቀድሞው ብአዴን ወይም የኋላው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በማፍረሱ ሒደትም እጁን ማስገባቱን ጠቅሰው ወቅሰዋል። 

Meles Zenawi Ministerpräsident Äthiopien
ምስል AP

ኢሕአዴግ የተመሠረተው በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና በቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) ጥምረት በግንቦት ወር 1981 ዓ.ም.  ነበር። መጋቢት 17 ቀን 1982 ዓ.ም. የተመሠረተው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና በመስከረም 1985 ዓ.ም. የ«አስራ ስድስት የብሔረሰብ የፖለቲካ ድርጅቶች» ጥምረት የሆነው ደኢሕዴን ግንባሩን የተቀላቀሉት ዘግይተው ነው። በግንቦት 1983 ዓ.ም. በተካሔደ ጉባኤ 86 አባላት ያሉት እና በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ያሳተፈ የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ሲመሰረት ቁልፍ ሥልጣኖች በኢሕአዴግ እጅ ነበሩ። 

ከሶስት አመታት በኋላ በግንቦት 1987 ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫ ተካሄዶ ፤የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲመሰረት ኢሕአዴግ አሸናፊ ሆነ ። ምክር ቤቱ በነሐሴ ወር አጋማሽ ባደረገው ስብሰባ የሽግግር መንግስቱ ፕሬዝዳንት የነበሩትን አቶ መለስ ዜናዊን ጠቅላይ ምኒስትር አድርጎ ሾመ። ከዚያ በኋላ በተካሔዱ ምርጫዎች ፈፅሞ ከሥልጣኑ የሚነቀንቀው አልተገኘም።በ2002 ዓ.ም. በተካሔደው ምርጫ 98 በመቶ እንዲሁም በ2007 ዓ.ም. በተካሔደው ምርጫ መቶ በመቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን አሸንፎ ተወዳዳሪ አልባ ሆነ። 

Hailemariam Desalegn, ehemaliger äthiopischer Ministerpräsident
ምስል DW

ከአምስት አመታት በፊት በተካሔደ ምርጫ ያለ አንዳች ተቃዋሚ የሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶችን የጠቀለለ ኢሕአዴግ ምርጫ ሳይሸነፍ፣ ፖሊሲ ሳይለውጥ እንዴት ለዚህ በቃ? የእነ በረከት ስምዖን፣ አባዱላ ገመዳ፣ አባይ ጸሀዬ እና ሽፈራው ሽጉጤ ኢሕአዴግ ከቶ እንዴት መጨረሻው መዘላለፍ እና መወነጃጀል ሆነ? አንደኛው ጉዳይ የግንባሩ ውህደት ነገር ነው። ኢሕአዴግ የፈረሰበትን ሒደት ህወሓት ኢ-ዴሞክራሲያዊ የሆነ እና ከመተዳደሪያ ደንቡ ውጪ የተፈጸመ ነው ሲል ይወቅሳል። ኢሕአዴግ በሥልጣን በቆየባቸው አመታት አጋሮቹን ገሸሽ አድርጓል ሲል የሚተቸው የእነ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወገን በበኩሉ ውህደቱ ቀድሞም ከሥምምነት የተደረሰበት ነበር የሚል ሙግት ያቀርባል። 
በዓለም አቀፉ የቀውስ ጥናት ማዕከል የኢትዮጵያ ጉዳዮች ተመራማሪው ዊሊያም ዳቪድሰን «ገዢው ኢሕአዴግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፅንሰ-ሐሳብን ጥሎ በመደመር እሳቤ ወደ ሚመራ አንድ ፓርቲ ለማዋኃድ ሁኔታዎቹ አጋጣሚዎቹም ትክክል ናቸው የሚል ዕምነት ሕወሓቶች የላቸውም። ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ምኒስትሩ ያቀረቡትን የፖለቲካ ፕሮግራም እና ርዕዮተ- ዓለም አላመኑበትም፣ አይቀበሉትም። ይልቁን ይህ የኅብረ-ብሔራዊው ወይም የብሔር ፌድራሊዝሙ የመጨረሻ መጀመሪያ እንደሆነ ህወሓት ያምናል» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ነው። በሐንጋሪ ብሔራዊ የፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ አስተዳደር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እያጠኑ የሚገኙት እና የኢሕአዴግን ፖለቲካ ቀረብ ብለው ያጠኑት አቶ ታከለ በቀለ ግን ከውህደቱ ባሻገር በግንባሩ አባላት መካከል ያለው የርስ በርስ ግንኙነት ፈተና ሆኖ እንደቆየበት ያስረዳሉ።

Äthiopien |  Abstimmung EPRDF
ምስል EPRDF

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ ፦ 


እሸቴ በቀለ