የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ያጸደቀው የግንባሩ ውህደት 180 አባላት ላሉት ምክር ቤትይቀርባል
ቅዳሜ፣ ኅዳር 6 2012የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውህደቱን ያጸደቀው ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ማካሄድ የጀመረውን ስብሰባ የአንደኛ ቀን ውሎ ሲያጠናቅቅ ነው። በዛሬው ስብሰባ ላይ የኢህአዴግ ውህደትን የተመለከተ ጥናት ቀርቦ ግልጽ ውይይት መደረጉን የጠቆሙት አቶ ፍቃዱ በስተመጨረሻ ከውሳኔ ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው “በአጠቃላይ ብስለት፣ መደማመጥ እና ግልጽነት ያለበት ውይይት ካካሄደ በኋላ ማምሻው ላይ በስድስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ከስምምነት ላይ ደርሷል” ብለዋል። አቶ ፍቃዱ የኢህአዴግን ውህደት የተቃወሙ አባላትን ግን በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ከሰላሳ ስድስቱ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መካከል ዘጠኙ የግንባሩን መዋሃድ በግልጽ ሲቃወም የቆየው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አባላት ናቸው። በዛሬው የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እና ምክትላቸው ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚብሔርን ጨምሮ ሌሎችም የድርጅቱ የስራ አስፈጻሚ አባላት ተገኝተዋል። የህወሓት ስራ አስፈጻሚ አባል እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በስብሰባው መክፈቻ ላይ አለመገኘታቸውን ስብሰባውን ከሚያሳዩ ምስሎች ለመመልከት ተችሏል። የኢህአዴግ አምስት አጋር ፓርቲዎች ሊቀመንበር እና ምክትሎቻቸው የዛሬውን ስብሰባ ድምጽ ሳይሰጡ ተከታትለውታል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የድርጅቱን ውህደት አስመልክቶ በቀረበው ጥናት ላይ ከስምምነት ላይ ቢደርስም ቀሪ ሂደቶች መኖራቸውን አቶ ፍቃዱ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል። “ስራ አስፈጻሚው ቢያጸድቀውም ነገር ግን ወደ ምክር ቤት ነው የሚወስደው” ብለዋል። የኢህአዴግ ምክር ቤት ከአራቱ የግንባሩ መስራች ድርጅቶች የተውጣጡ 180 አባላት ያሉት ነው። ነገ በሚቀጥለው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ለውይይት ይቀርባል የተባለው የውህድ ፓርቲው የፕሮግራም ረቂቅ ለኢሕአዴግ ምክር ቤት እንደሚመራም ጠቁመዋል። በነገው ስብሰባ ሌሎች አምስት ጉዳዮችም ውይይት እንደሚደረግባቸው አቶ ፍቃዱ ጠቅሰዋል።
የቋንቋ ጉዳይ፣ ህብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ስርዓትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዲሁም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እና የማስተዳደር ጉዳዮች ለውይይት ከሚቀርቡት ጉዳዮች መካከል እንደሆኑ ጠቁመዋል። ሁሉንም ብሔር ብሄረሰቦች የማካተት እና ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖራቸው ማድረግ እንደዚሁም የብሔርና ሀገራዊ ማንነትን አስታርቆ የመሄድ ጉዳይም በነገው ውይይት እንደሚነሱም አመልክተዋል። እነዚህ አምስት ጉዳዮች ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ በሚዋሃደው ፓርቲ ፕሮግራም እና ህገ ደንብ እንደሚካተቱም አብራርተዋል።
ተስፋለም ወልደየስ
እሸቴ በቀለ