1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሕልዉና

ሰኞ፣ ሐምሌ 8 2011

የሚጠበቅ አይደለም ግን ፓርቲዎቹ የሚጠበቁትን አልሆኑም።የሚጠበቁትን አለመሆናቸዉ ለየፓርቲዎቹ ብቻ ሳይሆን በጋራ ለመሰረቱት፣ ለገዢ ፓርቲነት ላበቁትም ኢሕአዴግ አንድነት በዉጤም በሽግግር ላይ ለምትገኘዉ ኢትዮጵያ አስጊ፣ አደገኛም ነዉ።

https://p.dw.com/p/3M7BZ
Äthiopien vor der Wahl EPRDF Anhänger in Addis Abeba
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

ኢሕአዴግ መስራቾች መወነጃጀልና የግንባሩ አንድነት

አምና መጋቢት አዲስ አበባ ላይ የተደረገዉ የመሪዎች ለዉጥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የዘመናት ትግሉ ዉጤት፣ የሰላም፣ የፍትሕ፣ የነፃነት የልማት ዕድገቱም ተስፋ ነበር።የቦምብ ሽብር፣የጎሳ ግጭት፣ ግድያ፣የሚሊዮኖች መፈናቀል ቅራ ቀኝ ሲያዳፈዉ ዓመት የዘለቀዉ ተስፋ፣ ዘንድሮ ሰኔ አጋማሽ የተፈፀመዉ የባለስልጣናት ግድያ ጨርሶ እንዳይድጠዉ ብዙዎችን አስግቷል።የሕዝብን ተስፋ ሲሆን የማዳን፣ ይሕ ቢቀር ስጋቱን የማቃለል ኃላፊነት የተጣለባቸዉ የገዢ ፓርቲ መስራቾች ከመቀሌና ባሕርዳር የገጠሙት መወነጃጀል ታዛቢዎች እንዳሉት 27 ዓመት አፈሙዝ የጋረደዉን «ድንቁርና» ገሐድ አፍግቶታል።ደቡብ ላይ የሚሰበከበዉ የራስ አስተዳደርም ገዢዉን ግንባር የሚያፍረከርክ፣ የሚንጠራወዘዉን ተስፋ ሕልቅት የሚፈጠርቅ መስሏል። ከዚሕ በኋላስ? 


ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ይመሩት የነበረዉ መንግስት ግንቦት 2001 በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ወንጅሎ ካሰራቸዉ የጦር መኮንኖች አብዛኞቹ አማሮች ነበሩ።የኢሕአዴግን መርሕና የመሪዎቹን አሰራር እናዉቃለን የሚሉ፣ ያኔ እንደተናገሩት ብዙዎቹ የፓርቲና የመንግስት ሹማምታት እርምጃዉን የሰሙት እንደአብዛኛዉ ህዝብ ከመንግስት መገናኛ ዘዴዎች ነበር።
እርምጃዉን ዘግይተዉ መስማታቸዉ፣ ተጠርጣሪዎቹ የጦር መኮንኖች «የቀድሞ» የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ታጋዮች መሆናቸዉ ያበሳጫቸዉ የንቅናቄዉ መሪ አቶ አዲሱ ለገሰ በዚያዉ ሰሞን በተደረገ የባለስልጣናት ስብሰባ ላይ፣ «ጠቅላይ ሚንስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጧቸዉ ጠየቁ» ይላሉ-ሰምተናል ባዮች።
«የተወሰደዉ እርምጃ አስተዳደራዊ በመሆኑ----መንግሥትን እንጂ ፓርቲዎችን----ደግሞም አንዳዶቻችሁ ሰምታችኋል------» እያሉ ትልቁ አለቃ ሲያብራሩ፣ አገጫቸዉን መዳፋቸዉ ላይ ተክለዉ ሲያዳምጡ የነበሩ አንድ የብአዴን ከፍተኛ ሹም፣-
 «አዲሱ---- እንዴ----እኔናተ አይደለንም እንዴ ኢሕድንን እጁን ጠምዝዘን ለሕወሓት ያስረከብነዉ----» አሉና ጠያቂዉም፣ መላሹም፣ ሌሎቹም «ሆድ ሲያዉቅ» ዓይነት ለዓመታት የሚደባብቁትን ሐቅ ተነፈሱ።«ተፈወሱ» ብንልም ያስኬድ ይሆናል።
ትረካዉ እዉነት፣ሐሰት፣ ሐሰት ቀመስ  እዉነት ይሆን አይሆንምም ይሆናል።ሕወሓትና ኢሕዴን ከ1980 ጀምሮ ኢሕአዴግን መስርተዉ እንደ ሸማቂ ተባብረዉ የተዋጉ፣እንደ መንግስት አብረዉ የገዙ ፓርቲዎች መሆናቸዉ ግን ሐቅ ነዉ።
አዲስ ተስፋ የፈነጠቀዉ የመሪዎች ለዉጥ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ግን ግንኙነታቸዉ «ትከሻሻ የመለካካት» ዓይነት መሆኑም ግልፅ ነዉ።ስማቸዉን የሸሸግነዉ የብአዴን ሹም የሁለቱን ፓርቲዎች የበላይ-በታችነት ሐቅ «ተናዘዙ» በተባለ 10ኛ ዓመቱ-ባለፈዉ ሳምንት ደግሞ ሕዝብ ለመምራትም፣ለመለያየትም፣አብሮ ለመስራትም «አቅመ ቢስ» መሆናቸዉን ለየሕዝባቸዉ አረጋግጠዋል።
በኪል ብሪታንያ ዩኒቨርስቲ የሕግ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አወል ቃሲም አሎ የሁለቱን ፓርቲዎች መወነጃጀል «አሳፋሪ» ይሉታል።
የሚጠበቅ አይደለም ግን ፓርቲዎቹ የሚጠበቁትን አልሆኑም።የሚጠበቁትን አለመሆናቸዉ ለየፓርቲዎቹ ብቻ ሳይሆን በጋራ ለመሰረቱት፣ ለገዢ ፓርቲነት ላበቁትም ኢሕአዴግ አንድነት በዉጤም በሽግግር ላይ ለምትገኘዉ ኢትዮጵያ አስጊ፣ አደገኛም ነዉ።
የኢሕአዴግ አንድነት ለአደጋ የተጋለጠዉ በሁለቱ መስራች ፓርቲዎች መወነጃጀል ብቻ አይደለም።የግንባሩ አራተኛ አባል ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን)ም እንደ ፓርቲ መቆም አቅቶት እየተዉገረገረ ነዉ።በተለይ የሲዳማ ፖለቲከኞች እስካሁን በዞን የተዋቀረዉ አካባቢያቸዉ የክልል መስተዳድርነት ሥልጣን እንዲሰጠዉ የሚያደርጉት ጠንካራ ግፊት ደቡብ ኢትዮጵያ እስካሁን በነበረችበት እንደማትቀጥል በግልፅ እያሳየ ነዉ።ዶክተር አወል የሲዳማዎችንም ሆነ የሌሎችን የራስ አስተዳደር ጥያቄን «ሕገ መንግሥታዊ» ይሉታል።ጥያቄዉን ገቢር ማድረጉ ግን ጊዜዉን አይደለም።
                                     
እስካሁን እንደሚታወቀዉ በመጪዉ ዓመት ግንቦት ምርጫ መደረግ አለበት።ሕዝብ ግን አልተቆጠረም።በየአካባቢዉ የተቀጣጠለዉ የጎሳ ግጭትም ሙሉ በሙሉ አልበረደም።የኢሕአዴግ መስራች ፓርቲዎች በአደባባይ የሚወነጃጀሉት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የራስ አስተዳደር ወይም የክልልነት ጥያቄችን ባስቸኳይ መመለስ አለበት የሚሉት ፣ ሕዝብን ማረጋጋት፣ ሕዝብን መቁጠሩን፣ የምርጫ ዝግጅት፣ፉክክሩንም እርግፍ አድርገዉ ትተዉ ነዉ።ድንቅም አይደል።
                                    
ኢሐዲግን አንድ አድርጎ የተጀመረዉን ሽግግር ዳር ማድረስ ከየትኛዉም ፖለቲከኛ በላይ ኃላፊነቱ የግንብሩ ሊቀመንበርና የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ነዉ።የዶክተር ዐብይ አሕመድ።ባለሁለት ባርኔጣ ይሏቸዋል ዶክተር አወል።የኢሕአዴግ አንድነት፣ የሽግሩ ሒደት፣የኢትዮጵያም ሕልዉና ከስጋት ተላቅቆ ከታሰበዉ የመድረስ አለመድረሱ ተስፋን ደግሞ ዶክተር አወል ተስፋ ላላማጣት የሚደረግ ተስፋ ነዉ።አማራጭ የማጣት ተስፈኝነት።ዶክተር አወልን አመሰግናለሁ። ቸር ያሰማን

Äthiopien Ethnie der Sidama
ምስል DW/S. Wegayehu
Das Logo der ADP Amharische Demokratischen Partei
ምስል ADP
Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ