1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢህአዴግ ውህደት፥ በፖለቲካ አመራሮችና በፖለቲካ ምሁራን እይታ!

እሑድ፣ ኅዳር 7 2012

በአማራ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሀም አለኸኝ እንደገለፁት ውህደቱ ለኢህአዴግ እህት ድርጅቶችና ለአጋር የፖለቲካ አደረጃጀቶች በአገራቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ እኩል የተሳታፊነት ድርሻ ይሰጣቸዋል።

https://p.dw.com/p/3TC2Z
Äthiopien l Leiter der politischen Strukturabteilung der ADP - Abrahan Alehegn
ምስል DW/A. Mekonnen

የኢህአዴግ ውህደት

የጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ የኢህአዴግ ውህደት ዕውን እንደሚሆን በተለያዩ ጊዜዎች ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ በኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ድጋፍና ተቃውሞ ሳይለየው ዛሬ የደረሰው የአህአዴግ ውህደት ሌሎች ቀሪ ሂደቶች ቢኖሩትም በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል፡፡
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር አቶ ቻላቸው ታረቀኝ የኢህአዴግና የአጋር ድርጅቶች ውህደት ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን አመልክተው፣ አሁን እየታየ ያለውን የብሔር አክራሪነት ስሜት ያለዝበዋል ብለዋል፡፡ ለሌሎች ተፎካካሪ ብሔር ተኮር ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም አረአያ እንደሚሆን አቶ ቻላቸው ተናግረዋል፡፡
የውህደቱን ጠቃሚነትና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው በአማራ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሀም አለኸኝ እንደገለፁት የውህደት ጥያቄ ዛሬ እንዳልተጀመረ አስታውሰው፣ ውህደቱ ለኢህአዴግ እህት ድርጅቶችና ለአጋር የፖለቲካ አደረጃጀቶች በአገራቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ እኩል የተሳታፊነት ድርሻ ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡
አቶ አብርሀም አያይዘውም ከዚህ በፊት በነበረው ሂደት አጋር ፓርቲዎች የነበራቸው ፖለቲካዊ ተሳትፎ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የተለየ ሚና እንዳልነበራቸውም አመልክተዋል፡፡ ውህደቱ አህዳዊ ሥርዓተ መንግስት ለማምጣት የታቀደ ሂደት ነው የሚለውን ስሞታ በተመለከተ አቶ አብርሀም በሰጡት ምላሽ፣ ውህደቱ ተንገራግጮ አንዲቆም የሚሰራ የፖለቲካ ሴራ መሆኑንና፣ ይልቁንም ውህደቱ የፌደራሉን ስርዓተ መንግስት ያጠናክረዋል ብለዋል አቶ አብርሀም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ፍልስፍና በሚተችበት ወቅትና አገሪቱ አሁን ባለችበት ደረጃ የውህደቱ ተግባራዊነት ፈተና አይገጥመውም ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ አብርሀም፣ከለውጥ ኃሎች አንጻር ከፍተኛ አንደሆነ፣ የጨቋኝና ተጨቋን ትርክት የሚቀብር ፍልስፍና እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም የሚሰሙ ትችቶችን መቀበልና ሃሳቡን መርምሮ የሚታረመውን በማረም ውህደቱን በማፋጠን ወደፊት መጓዝ እንጂ ወደ ኋላ መመለስ ተገቢ አይደለም ሲሉ መልሰዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን
ልደት አበበ