1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢህአዴግ ውህደት በፖለቲካ ሰዎች ዕይታ

ሰኞ፣ ኅዳር 8 2012

ኢህአዴግ ግንባርነቱ ቀርቶ አንድ ወጥ አገራዊ ፓርቲ ለመሆን የውህደት ሂደቱን ከጫፍ እየደረሰ መሆኑን ተከትሎ የተለያዩ ሃሳቦች እየተንጸባረቁ ነው። ዶይቸ ቬለ ህወሓት ውህደቱን ተቃውሞ ስለመውጣቱ፤ በግንባሩ ውስጥ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሆኑ ግለሰቦችን ምልከታ እንዲሁም የኢዜማን አስተያየት አሰባስቧል።

https://p.dw.com/p/3TFwZ
Äthiopien Anhänger der Partei EPRDF
ምስል Imago/Xinhua Afrika

የኢህአዴግ ውህደት በፖለቲካ ሰዎች ዕይታ

የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ «ለቅሶው ከዕቅድ በታች ነው እና በድጋሚ ይለቀስ» ሲሉ የኢህአዴግን ውህደት ተቃውመዋል ያሏቸውን ምሁራን የተቹበትን ሃሳብ እንደሚከተለው አስፍረዋል። «የአንዳንድ "ምሁራን" ሁኔታም ገራሚ ነዉ። በ2009 ዓ.ም. የአፋን ኦሮሞን የፊደል ቅደም ተከተል ለማዛባት በተሞክረ ጊዜ በጉዳዩ ላይ አስተያዬት ለመስጠት ሲፈራ የነበረ እና በወቅቱ "OPDO" መባል ያሳፈረዉ የፓርቲዉ አባል የነበረ "ምሁር" ዛሬ በኢህአዴግ ፍቅር ወድቆ " ከታላቁ አፄ መለስ ባልተናነሰበት ሁኔታ EPP ከመጣ እሞታለሁ" ሲል ትሰማና ፈገግ ትላለህ። በደርግ ጊዜም በአንድ ቀን ስብሰባ ከሌኒን በላይ ሌኒኒዝምን የሰበከ ቄስ በኢትዮጵያ እንደነበር ስታውቅ ደግሞ ነገሩ የተለመደ መሆኑን ትረዳለህ። አድርባይነት በዚህ ፍጥነት ማንነትን ይለውጣል» ብለዋል በፌስቡክ ጽሑፋቸው። 

Taye Dendea
ምስል Geberu Godane

የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አሰማኸኝ አስረስ በበኩላቸው ሰዎች በብሄር ማንነታቸው የሚመዘኑበት ጊዜ አልፎ በብቃታቸው ብቻ ኃላፊነት የሚረከቡበት ጊዜ ስለመድረሱ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። «በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ፍትሐዊነት፣ እኩልነት፣ ዴሞክራሲያዊነት እና ሕብረ-ብሔራዊነት የሚመሠረተው ሰዎች የሚመዘኑት በብሔር ማንነታቸው ሳይሆን በአጠቃላይ ብቃትና ሀሳባቸው ሆኖ እንዲህ አይነቱን ስርዓት መዘርጋት የሚችል የፖለቲካ ምኅዋር ሲኖር ብቻ ነው። ያ ማለት ብሔሮችና ብሔረሰቦች ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እኩልነትን እና ፍትሃዊነትን በእናት አገራቸው ውስጥ ይጎናጸፋሉ። ያ ማለት አንዳንድ ብሔር ብሔረሰቦች ሁልጊዜ ታሪክ እየተመዘዘ marginalize አይደረጉም። “አናሳ” እየተባሉ ከአገራቸው ዋና ዋና ጉዳዮች አይገለሉም። ይህ ሁሉ የሚሆነው በውህድ ፓርቲው ውስጥ ነው» ሲሉ ጽፈዋል ።

Asemahegn Aseres
ምስል DW/A. Mekonnen

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ወደ ውህደት የሚያደርገውን ጉዞ ተቃውሞ የወጣው ህወሓት ቀደም ሲል ለዓመታት ይህንኑ የውህደት ጉዞ ሲደግፍ ቆይቶ በመጨረሻ ተቃውሞ መውጣቱ ለምን ሲሉ አንዳንዶች ይጠይቃሉ። የህወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አማኑኤል አሰፋ እንዳሉት ህወሓት ከፓርቲም ሆነ መንግሥታዊ ሕግጋት ባፈነገጠ ሂደት ውስጥ መግባት አይፈልግም። «የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች በአዋጅ መልክ ውህደትን በውጭ አገርም በሀገር ውስጥም በተለያዩ ሚዲያዎች ፣ በተለያዩ ስብሰባዎች እነርሱ ናቸው ውህደት እንደሚፈጸም እየነገሩን ያሉት ። እንደዚያ አይነት በኢትዮጵያ ህግም ሆነ በፓርቲው በኢህአዴግም ሆነ ብሄራዊ ፓርቲ የሚመሩባቸው ህጎች እንደዚያ አይልም» ብለዋል።

 ከግንባሩ መሥራች ድርጅቶች አንዱ የሆነው ህወሓት ከኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ በኋላ ጉዳዩን ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ ወስጄ እመክርበታለሁ መባሉን ተከትሎ የአቋም ለውጥ ይኖር እንደሁ የተጠየቁት አቶ አማኑኤል፤ «ህወሓት ግልጽ ነው። አሁን እኔ ስላልተሳተፍኩኝ ፣ የስራ አስፈጻሚ አባል ስላልሆንኩኝ ምን እንደነበር ግልጽ የሆነ ዝርዝር ነገሮችን አላገኘሁም ። እኔ በመርህ ደረጃ የህወሓት እና የትግራይ ህዝብ አቋም ግን አውቀዋለሁ። ህወሓት በዚህ በሚካሄደው መንገድ ገብቶ መንቦጫረቅ እንደማይፈልግ ቀድሞ ግልጽ አቋም አውጥቷል» ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

Äthiopien | EZEMA - Diskussion mit Jugendlichen
ምስል DW/Y.G/egziabher

የሀገሪቱ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ መዋሃዱ በበጎ ጎኑ እንደሚመለከት የገለጸው ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ኢዜማ ነው። የፓርቲው ድርጅት ጉዳይ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እንዳሉት ውህደቱ አገሪቱ ከዘውግ አስተሳሰብ የፖለቲካ ምሕዳር መውጣት ስለመፈለጓ አመላካች ነው። «የፖለቲካ ድርጅቶች በዚህ አይነት መልኩ መቆም አለባቸው። መወዳደር ያለባቸው በዘር በሀይማኖት ወይም በአካባቢ ሳይሆን በሚያመነጩት ሀሳብ ነው ባይ ነኝ። እያንዳንዱን ዜጋም በሰውነት፣ በኢትዮጵያዊነት ማየት አለባቸው የሚል ነው ያለኝ። አጠቃላይ ሃሳቡ ከእኛ ሃሳብ ጋር የሚጣጣም አልነበረም ከዚህ ቀደም። ስለዚህ ወደዚህ መቀየሩ እንደተባለው በፖለቲካ ሜዳው ላይ የሚፈጥረው ልዩነት ይኖራል» ሲሉ አቶ የሺዋስ ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምሕዳር ውስጥ ኢዜማን ጨምሮ የርዕዮት ወይም የጎራ መደበላለቅን ይፈጥር እንደሁ አቶ የሺዋስ ሲመልሱ የኢህአዴግ መዋሃድ ተጨማሪ የፖለቲካ ምርጫን ይዞ ቢመጣ እንጂ የእርሳቸው ፓርቲ ከሚያራምደው የፖለቲካ አስተሳሰብ ጋር አይጋጭም ይላሉ። «የእነርሱ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲ ወይም የብልጽግና ብቻ ምንም ይሁን ቢሉ ከእኛ ጋር ግልጽ የሆነ ልዩነት ያለው በመሆኑ አጠቃላይ በአይዲዮሎጂ ወይም በፖለቲካ መቃኘትን ከመደገፍ ውጪ ይኽ ሃሳብ የሚጠቅም ነው ብለን አናስብም። ስለዚህ የራሳችንን አማራጭ ይዘን እንቀርባለን» ብለዋል። 

ኢህአዴግ ወደ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብልጽግና ፓርቲ የውህደቱ የመጨረሻ ምዕራፍ የሚያደርሰውን የፓርቲውን ንድፈ ሃሳብ በማጽደቅ ወደ ግንባሩ ጉባኤ ማምራቱን አስታውቋል።

ታምራት ዲንሳ

ማንተጋፍቶት ስለሺ