1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃና የቱርክ አጋርነት

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 9 2014

የቱርክና የአፍሪቃን የየሁለትዮሽ ንግድ በጎርጎሮሳዊው 2021 የመጀመሪያዎቹ 5 ወራት ወደ 21 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ነበር።የንግድ ግንኙነቱ በየዓመቱ ከ27 በመቶ በላይ እያደገ ነው የሄደው። ቱርክ የንግድ ልውውጡን ወደ 50 በመቶ ከፍ የማድረግ እቅድ አላት።

https://p.dw.com/p/44V4k
Türkei-Afrika Gipfel in Istanbul
ምስል Murat Kula/AA/picture alliance

የአፍሪቃና የቱርክ አጋርነት

በአፍሪቃ ቁልፍ በሆኑ መሠረተ ልማቶችና በጤናው ዘርፍ የምትወርተው ቱርክ በተፈጥሮ ሀብት ከበለጸጉት ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር ግንኙነትዋን ይበልጥ ለማጠናከር እየጣረች ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሰብዓዊ እርዳታ በኃይል ዘርፍም በንቃት እየተሳተፈች ነው። ወታደራዊ ውሎችንም ስትፈራረም ቆይታለች። ከመካከላቸው ባለፈው ጥቅምት የቱርክ ፕሬዝዳንት ተይፕ ሬሴፕ ኤርዶሀን በአንጎላ ቶጎና ናይጀሪያ ጉብኝታቸው የተፈራረሟቸው ወታደራዊና ከኃይል ዘርፍ ጋር የተያያዙ ውሎች ተጠቃሽ ናቸው። ቱርክ በአፍሪቃ በሰብዓዊና በማኅበራዊ እርዳታዎች ፕሮጀክቶች ላይ ብዙ ወርታለች።ከማሊ እስከ ሶማሊያ ትምህርት ቤቶችን ሆቴሎችን መስጊዶችን ሰርታለች የውኃ አቅርቦትና  የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ዘርግታለች። ከ54ቱ የአፍሪቃ ሀገራት በ43ቱ ኤምባሲዎች አሏት።
 ለሁለት ቀናት ተካሂዶ ዛሬ የተጠናቀቀው የቱርክና የአፍሪቃ ሶስተኛ ጉባኤ ለሁለቱ ወገኖች « ስልታዊና ዘላቂ ግንኙነቶች » መሠረት የሚጥል ተብሏል። በጉባኤ ላይ 16 ርዕሳነ ብሔራትና መራኅያነ መንግስት ተገኝተዋል። 102 ሚኒስትሮችም የጉባኤው ተካፋይ ነበሩ።  የቱርክና የአፍሪቃን የየሁለትዮሽ ንግድ ስንመለከት በጎርጎሮሳዊው 2021 የመጀመሪያዎቹ 5 ወራት የሁለቱ ወገኖች የንግድ ልውውጥ ወደ 21 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ነበር።የንግድ ግንኙነቱ በየዓመቱ ከ27 በመቶ በላይ እያደገ ነው የሄደው። ቱርክ የንግድ ልውውጡን ወደ 50 በመቶ ከፍ የማድረግ እቅድ አላት። አፍሪቃውያን ባለሀብቶች ከቱርክ ጋር በሚካሄድ ንግድ ደስተኛ ይመስላሉ።ዶቼቬለ ከጠየቃቸው ባለሀብቶች ሁለቱ የቱርክ ምርቶችን ጥራት ያደንቃሉ።የዋጋቸው ተመጣጣኝነትም ያረካቸዋል። 
ሊሊ ፍሪማን ትሬ አይቮሪኮስታዊው ነጋዴ ናቸው። አይቮሪ ኮስት የሚገኝ «ቤት ሰርቶ የሚሸጥ» ሲጅ ግሩፕ የተባለ ኩባንያ ዋና ሃላፊ ናቸው።ከቱርክ ጋር ረዥም ጊዜ የዘለቀ የንግድ ግንኙነት ያላቸው ባለሀብቱ በቱርክ የንግድ አጋርነት ይተማመናሉ። ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳሉት ቱርክን ምርጫቸው ያደረጉበት ምክንያት አላቸው።  
« ቱርክ ምርጫዬ የሆነችው በምርቶችዋ ጥራት ነው። ከሌሎች ሀገራት በተለየ ለገበያ ከሚያቀርቧቸው ምርቶች 80 በመቶው ከቱርክ ናቸው።»
ባለሀብቱ ትሪ ከእስያ ሀገራት ጋር እያነጻጸሩ ከቱርክ ብዙ መማር ይቻላልም ይላሉ።
«ከቱርክ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ብዙ ትምሕርት መውሰድ ይቻላል።ቱርኮች ጠለቅ ያለ ልዩ እውቀት አላቸው።በአሰራር ጥራት በውስጥ ዲዛይን በትክክለኛ የቀለም ምርጫ ጥሩ ናቸው።ከእስያዎች ጋር ሲነጻጸር ጥሩ የግንባታ እቃዎችም አሏቸው።»ሲሉ ቱርኮችን ያወድሳሉ።ይህ ብቻ አይደለም እንደ ትሬ ዋጋቸውም ውድ አይደለም 
«ምርቶቹ ጠንካራ ናቸው።የምርቶቻቸው የጥራት ደረጃ ከአውሮጳ ምርቶች ጋር የሚስተካከል ሆኖ ዋጋቸው ወደ እስያዎቹ ምርቶች ዋጋ ያጋድላል።በማንኛውም ሁኔታ ከአውሮጳ ምርቶች ዋጋ በጣም ይቀንሳል» 
ትሬ እንዲህ ከሚያወድሷት ከቱርክ ጋር በሚካሄድ የንግድ ልውውጥ ችግር መኖሩ አልቀረም ። ችግሩም እርሳቸው እንደሚሉት ቋንቋ ነው። ከቱርኮች ጋር በቋንቋ ምክንያት በቀላሉ መግባባት ይከብዳል ።የትሬ ቅሬታ የቱርክ ባለሀብቶች እንግሊዘኛ ብዙም አለመቻላቸው፣ ፈረንሳይኛ ደግሞ ጭራሽ አለመሞከራቸው ነው። በዚህ የተነሳ መግባባት የሚቻለው በአስተርጓሚ መሆኑ አዳጋች ነው በትሬ አስተያየት።ያም ሆኖ ከቱርክ ጋር የሚካሄደው ንግድ አብቧል። ቱርክ በፈንታዋ ከአይቮሪኮስት ካካዋ ፣የሺአ ቅቤ፣ ኦቾሎኒና አልፎ አልፎ እንጨትም ትገዛለች። ሌላዋ የቱርክ የንግድ ሸሪክ ሴኔጋል ናት ።በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ሴኔጋል የሚገኙት ሙሳ ምያቤ «ላ ቱርክዋዝ»የተባለ የቱርክ ኩባንያ ውስጥ የቱርክና የሴኔጋል ንግድ አስተባባሪ ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት የሴኔጋልና የቱርክ የንግድ ግንኙነት ከቀድሞው በእጅጉ አድጓል።
«ከሴኔጋልና ቱርክ የንግድ ልውውጥ 90 በመቶውን የማስተባብረው እኔ ነኝ።ዓለም አቀፉን ንግድ እያስፋፋን ነው።የቤት እቃዎች፣ብረት እና የመኪና መለዋወጫዎች እንሸጣለን፤ እስካሁን በወር ከሶስት እስከ አራት ኮንቴይነሮች እዚህ ይመጡ ነበር።አሁን ግን በእጥፍ አድጓል።ጨምሯል» 
ሲሉ ምባዬ ከዳካር ሴኔጋል ለዶቼቬለ ተናግረዋል።እርሳቸው እንደሚሉት ሁሉንም እቃዎች ከቱርክ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ይቻላል። የአይቮሪኮስቱ ባለሀብት ትሬና የሴኔጋሉ ምባዬ ከቱርክ ጋር የሚያካሂዱት ንግድ ፣አፍሪቃ የወደፊቷ የቱርክ ገበያ መሆኗ ማሳያ ናቸው።ቱርክ ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር የምታካሂደውን ንግድና የተለያዩ ትብብሮች ለማጠናከር መሰረት የምትጥልበትን ጉባኤ ከአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ጋር ማካሄድ ከጀመረች 13 ዓመታት ተቆጥረዋል። የመጀመሪያው የቱርክ አፍሪቃ ጉባኤ  በጎርጎሮሳዊው 2008 ነበር የተካሄደው። ሁለተኛው ደግሞ የዛሬ 7 ዓመት በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓመ ተ ምህረት ነበር። ሦስተኛው ጉባኤ ደግሞ ትንናትናና ዛሬ ኢስታንቡል ውስጥ ተካሂዷል።በዚሁ ጉባኤ ላይ በዙር የሚደርሰው የወቅቱ የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበር የኮንጎው ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቺሴኬዴና የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሙሳ ፋኪ መሐሜት ንግግር አድርገዋል። የአፍሪቃ ነጻ የንግድ ቀጣና ዋና ጸሀፊም በጉባኤው ላይ ተካፍለዋል። የቱርክ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ተቋም ባልደረባ የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ጉቬን ሳክ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት እስካሁን ቱርክ ከአፍሪቃ ጋር ያካሄደችው ንግድ መጠን 70 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል። የ2020 ዓመተ ምኅረቱን ብቻ ለይተን ስናይ ደግሞ 15 ቢሊዮን ዶላር ነው። ከዓለማችን አህጉራት የወጣቱ ቁጥር የሚያመዝንባት አፍሪቃ የህዝብዋም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው። የተባበሩት መንግሥትት ድርጅት እንደሚለው በጎርጎሮሳዊው 2100 የአፍሪቃ ህዝብ ቁጥር ከአሁኑ ቢያንስ በሦስት እጥፍ አድጎ 4 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።  
እንደ ሳክ የአፍሪቃ ና የቱርክ የንግድ ግንኙነት መገለጫ፣ በከተሞች የሚካሄደው መሠረተ ልማት እንዲሁም በኃይልና በግንባታ ዘርፍ ያሉት የኢንቬስትመንት እድሎች ነው። አፍሪቃ በባህላዊና ታዳሽ የኃይል ምንጮች የበለጸገች መሆኗ በጣም እያደገ በመሄድ ላይ ያለውን የሁለቱን ወገኖች የገበያ እድል ያስፋል እንደ ባለሞያው ።አንካራ ጎርጎሮሳዊውን 2005 ዓም የአፍሪቃ ዓመት ካለች በኋላ የሁለቱ ወገኖች ግንኙነት በእጅጉ ተሽሽሏል። የቱርክ መንግሥት በአፍሪቃ በኢንዱስትሪና በግንባታ ዘርፎች አትራፊ የንግድ እድሎች አግኝቷል። የቱርክ ኩባንያዎች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በክፍለ ዓለሙ በተለይም በትምሕርቱ ዘርፍ ተሰማርተዋል።ከተሻሻለው የምጣኔ ሀብት ግንኙነት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱም አብሮ አድጓል። ቱርክ ከጎርጎሮሳዊው 2008 ዓም አንስቶ የአፍሪቃ ኅብረት ስልታዊ አጋር ነች ። ፕሬዝዳንትዋም ከአፍሪቃ መራኂያነ መንግስታት ጋር በየጊዜው ይገናኛሉ።በቅርቡ እንኳን በጥቅምት አንጎላን ናይጀሪያንና ቶጎን ጎብኝተዋል። ከዚህ ሌላ ቱርክ በክፍለ ዓለሙ በሰብዓዊ እርዳታው መስክም ለጋስ መሆንዋን አስመስክራለች። በእርስ በርስ ጦርነትና በድርቅ በተጎዳችው በሶማሊያ መንገድ ትምሕርት ቤትና ሆስፒታሎች የሚሰሩ ባለሞያዎቿን ልካለች። ለዚህ ውለታዋ ደግሞ የኅይል ጥሟን ለማርካት ስልታዊውን የአደን ባህረ ሰላጤ አካባቢ መተላለፊያ መጠቀም ችላለች በወታደራዊው ትብብር ዘርፍም ኤርዶጋን በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓም የፕሬዝዳንትነቱን ስልጣን ከያዙ በኋላ በአፍሪቃ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ቱርክ ከፍተኛ ተጽእኖ የምታሳድር ሀገር ሆናለች። ቱርክሶም የተባለው በ2017 ሶማሊያ የተቋቋመው ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም  ለቱርክ ከሰሀራ በረሀ በታች ወደሚገኙ ሀገራት መተላለፊ በር ሆናታል። በዚያ ብዙ ቁጥር ያለው የቱርክ ጦር ይገኛል። ቱርክ ከተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት ጋር ወታደራዊ ውሎችም አሏት። ለብዙዎቹም የጦር መሳሪያ አቅራቢ ሀገር ናት። የዶቼቬለዋ ማርቲና ሽቪኮቭስኪ የቱርክ የውጭ ነጋዴዎች ምክር ቤትን ጠቅሳ እንደዘገበችው  ቱርክ ለኢትዮጵያ የምታቀርበው የጦርና የበረራ መሳሪዎች ሽያጭ ካለፈው ዓመት ጥር አንስቶ እስከ ህዳር ድረስ ባለው ጊዜ ከ235 ሺህ ዶላር ወደ 94.6 ሚሊዮን ዶላር አሻቅቧል።ከአንጎላ ቻድና ሞሮኮ ጋር የሚካሄደው ተመሳሳይ ንግድም እድገት አስመዝግቧል። ቱርክ በሰው አልባ አውሮፕላኖች በድሮን ሽያጭም ትታወቃለች። ድሮኗቿ በገበያ ላይ ተፈላጊ ናቸው። በተለያዩ ግጭቶች ጥቅም ላይ ያዋሉት የቱርክ ድሮኖች ውጤታማነታቸውን ያስመሰከሩ ናቸው ተብሏል። በሮይተርስ የዜና አገልግሎት ዘገባ መሰረት በዚህ ዓመት በመስከረም ወር ሞሮኮና ቱኒዝያ ከቱርክ ድሮን ወስደዋል። ሌሎች በርካታ የአፍሪቃ ሀገራትም የቱርክ ድሮኖችን የመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል።

Angola | Recep Tayyip Erdogan trifft Joao Manuel Goncalves Lourenco
ምስል Mustafa Oztartan/Turkish Presidency/handout/AA/picture alliance
Türkei | Besuch Präsident Taschad Mahamat Idriss Déby Itno bei Präsident Erdogan
ምስል Präsidentschaft des Tschad
Türkei Recep Tayyip Erdogan in Eskisehir
ምስል Murat Cetinmuhurdar/Turkish Presidency/AA/picture alliance

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ