1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ የእግር ኳስ አባትና የሞሮኮ የኳስ ጥበብ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 6 2015

ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የአፍሪቃ አገራት ያደረጉትን የማጣሪያ ውድድር አሸንፋ በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ1970 ዓ.ም በሜክሲኮ የዓለም ዋንጫ አፍሪቃን ወክላ የተካፈለች የመጀመሪያዋ አገር ሞሮኮ ነበረች። ሞሮኮ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ፖርቱጋልን ገጥማ አንድ ለዜሮ አሸንፋ ወደ ግማሽ ፍፃሜ በማለፍም የመጀመሪያዋ አፍሪቃ አገር ሆናለች፡፡

https://p.dw.com/p/4Kxah
Artist Tessema Asrate supporting Morocco National team with his Art
ምስል Tessema Asrate

የአፍሪቃ የኳስ አባት ክቡር ይድነቃቸዉ ተሰማን ሞሮኮ አክብራቸዋለች

« ሞሮኮ ከክሮኤሽያ አቻ ሲወጣ፣ ቤልጅየምን፣ስፔይንንና ፖርቹጋልን ሲያሸንፍ በተደጋጋሚ ታሪክ ሰርቷል። በተለይ ፖርቹጋልን ሲያሸንፍ ቢያንስ አራተኛ ደረጃ ማግኘቱን አረጋግጧል። ለፍጻሜ ጨዋታዉን የሚያበቃዉን ግጥምያ ከፈረንሳይ ጋር ሲካሂድም የሚደነቅ ጥረት አድርጓል። ይሁንና በፈረንሳይ ሁለት ለዜሮ በሆኔ ዉጤት ተሸንፏል። ይሁንና የሞሮኮ የእግርኳስ ቡድን እዚህ ደረጃ ድረስ የመጣዉ በአጋጣሚ አይደለም። ሞሮኮዎች በአገራቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች በብዛት አዘጋጅተዋል። ሕፃናትን  ታዳጊዎችንና ወጣቶችን በተለያየ የስፖርት እንቅስቃሴዎች በብዛት ያሰለጥናሉ። በሁሉም የዕድሜ ክልል ካለማቋረጥ ውድድሮች ያዘጋጁላቸዋል። ለአውሮጳ ቅርብ ስለሆኑም ወደ አዉሮጳ እየመጡ በየጊዜው የወዳጅነት ጨዋታዎች በማድረግ ልምድ ይቀስማሉ። ሞሮኮዎች በአውሮጳ የተወለዱና ከልጅነት ጀምሮ እዚያው አዉሮጳ ዉስጥ የሰለጠኑ እንዲሁም ከአገራቸው ተመልምለው በአውሮጳ ታላላቅ ክለቦች የሚጫወቱ ዜጎች አሏቸው። ሞሮኮዎች በኳታር በሚካሄደዉ የዓለም ዋንጫ ያገኙት አስደናቂ ውጤት የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው። ሊደነቁ ይገባል።»

Artist Tessema Asrate supporting Morocco National team with his Art
ሠዓሊ ተሰማ አስራት፤ የሞሮኮ ብሔራዊ ለግማሽ ፍፃሜ ባለፈ እለት፤ ክቡር ይድነቃቸዉ ተሰማን ምስል ይዞ ከሞሮኮ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ጋር ዶሃ ዉስጥ መታየቱ ብዙዎችን አስደምሟል። ምስል Tessema Asrate

ኢትዮጵያዉ ስፖርተኛ የእግር ኳስ አፍቃሪ የክቡር ይድነቃቸዉ ተሰማ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸዉ ከዶቼ ቬሌ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የተናገሩት ነዉ። ሰሞኑን የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን በኳታሩ የዓለም እግርኳስ ግጥምያ ላይ ባሳየዉ ከፍተኛ ብቃት ኢትዮጵያዊዉ ስፖርተኛ የእግርኳስ አፍቃሪ ክቡር ይድነቃቸዉ ተሰማ በከፍተኛ ደረጃ ተወስተዋል።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ፖርቱጋልን አሸንፋ ወደ ግማሽ ፍጻሜ በማለፍ የመጀመሪያዋ አፍሪቃዊት ሀገር ሆና ታሪክ የሰራችዉ ሞሮኮ፤ ለፈረንሳይ መንገዱን ክፍት አድርጋለች። ሞሮኮ በፈረንሳይ ሁለት ለዜሮ ትሸነፍ እንጂ ቡድኑ ጠንካራ ጨዋታን ማሳየቱን የኳስ አፍቃሪዎች ይመሰክራሉ።  

Artist Tessema Asrate supporting Morocco National team with his Art
የሠዓሊ ተሰማ አስራት ጥበብ፤ የአፍሪቃ የእግር ኳስ አባት ክቡር ይድነቃቸዉ ተሰማ በኳታሩ የዓለም ኳስ ግጥምያ ታዉሰዋል ምስል Tessema Asrate

በሀገር አቀፍ፣ በአኅጉራዊ፣ እና በዓለም አቀፍ የስፖርት አመራር ከፍተኛ አስተዋጽኦን ያበረከቱት ታላቁ ኢትዮጵያዊ ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ሰሞኑን ከሞሮኮ የኳስ ጨዋታ ብቃት ጎን ለጎን ስማቸዉ ከፍ ብሎ ሰንብቷል። መኖርያዉን በኳታር ያደረገዉ እና በዶሃ ሲኖር ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ የሆነዉ፤በኳታር አየር መንገድ በፔንቲንግ ዲፓርትመንት ወይም በቀለም ቅብ ክፍል ዉስጥ በማገልገል ላይ የሚገኘዉ ሠዓሊ ተሰማ አስራት፤ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ የተባለዉን ፖርቱጋልን አንድ ለዜሮ ረቶ ለግማሽ ፍፃሜ ባለፈ እለት፤ የአፍሪቃ አህጉር ካርታን በትልቁ ስሎ የኢትዮጵያዊዉን የክቡር ይድነቃቸዉ ተሰማን ምስል እና የሞሮኮን ብሔራዊ ቡድን ኮከብ ተጫዋች ምስል አፍሪቃ አህጉር ካርታ ዉስጥ በስዕል መልክ አስገብቶ ከሞሮኮ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ጋር ዶሃ ዉስጥ ስዕሉን ይዞ ሲጨፍር መታየቱ ብዙዎችን አስደምሟል። ሰዓሊ ተሰማ አስራት የሞሮኮዎች ለክቡር እንዳልካቸዉ ተሰማ እዉቅና ሰጥተዉ በስማቸዉ ካዛብላንካ ዉስጥ ስቴድዮምን መሰየማቸዉን በመስማቴ ተገርሜያለሁ። በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያዊዉ  የእግርኳስ አባት ክቡር ይድነቃቸዉ ተሰማ መታወሳቸዉ ደስ ብሎኛል። በሌላ በኩል አንድ አፍሪቃዊ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለሩብ ፍጻሜ በማለፉም አስደስቶኛል። ከሞሮኮ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ጋር ሆኜ ደስታዬን ገልቻለሁ። አገሪንም አስተዋዉቄያለሁ ብሏል።   

ክቡር እንዳልካቸዉ ተሰማ በእግር ኳስ ማኅበራት (ፊፋን ጨምሮ) በነበራቸው የአመራር ተሳትፎ እና ብቃት ከብሔራዊ ደረጃ አንስቶ በአህጉር አቀፍ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ይታወሳሉ።

Artist Tessema Asrate supporting Morocco National team with his Art
የሠዓሊ ተሰማ አስራት ጥበብ፤ በኳታሩ የዓለም ኳስ ግጥምያ ምስል Tessema Asrate

የክቡር ይድነቃቸዉ ተሰማ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸዉ ተሰማ የሞሮኮ የእግርኳስ ጥበብ ከቀድሞ ጊዜ ጀምሮ እንደነበር ይናገራሉ።

«የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የአፍሪቃን በዓለም ዋንጫ የመካፈል መብት ለማስከብር ከፊፋ ጋር ለብዙ ዓመታት ታግሏል፡፡ ትግሉ ተሳክቶ በጊዜው የፊፋ ፕሬዚዳንት የነበሩት እንግሊዛዊው ሰር ስታንሌ ራውስ በዚያን ጊዜ በ16 አገራት መካከል ይካሄድ በነበረው የዓለም ዋንጫ አፍሪቃ አንድ ተወካይ እንዲኖራት ፊፋ መወሰኑን ያሳወቁት በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ1968 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጉባኤ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የአፍሪቃ አገራት ለዚህ አንድ ቦታ ያደረጉትን የማጣሪያ ውድድር አሸንፋ እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ1970 ዓ.ም በሜክሲኮ በተደረገው የዓለም ዋንጫ አፍሪቃን ወክላ የተካፈለች የመጀመሪያዋ አገር ሞሮኮ ነበረች። ሞሮኮ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ፖርቱጋልን ገጥማ አንድ ለዜሮ አሸንፋ ወደ ግማሽ ፍፃሜ በማለፍም የመጀመሪያዋ አፍሪቃ አገር ሆናለች፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደዉ 10ኛው  የአፍሪቃ ዋንጫ ሞሮኮ ስታሸንፍ በአፍሪቃ እጅግ ዝነኛ የነበረዉ እና የዓመቱ ብርጥ ተጫዋች ተብሎ የተጠራዉ የሞሮኮ ተጨዋች አህመድ ፋራስ ለአፍሪቃ የመጀመሪያ በነበረው በሜክሲኮ የዓለም ዋንጫም ተጫውቶ ነበር፡፡  ሞሮኮ ኢትዮጵያ የተዘጋጀዉን 10ኛዉን የአፍሪቃ ዋንጫ ስታሸንፍ አህመድ ፋራስ ዋንጫዉን የተቀበለዉ ከደርግ ሊቀ መንበር ከነበሩት ከብርጋዲየር ጄኔራል ተፈሪ በንቲ እና ከክቡር ይድነቃቸዉ ተሰማ ነበር።»

Soccer championship Africa (CAF) in 1976
ኢትዮጵያ በተካሄደዉ 10ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ሞሮኮ አሸንፍ የሞሮኮ ኮከብ ተጫዋች አህመድ ፋራስ ዋንጫዉን ሲረከብምስል Tadele Yedenekachew Tesema

የስፖርተኛዉ ልጅ አቶ ታደለ ይድነቃቸዉ የዓለምን የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ። የእግር ኳስ አፍቃሪም ናቸዉ። የዘንድሮዉ የኳታሩ የዓለም እግርኳስ ግጥምያ ለዋንጫ ይጠበቁ የነበሩ ቡድኖች ቀድመዉ የመዉጣታቸዉ ዜና ፈገግ አሰኝቷቸዋል። ይሁንና ጀርመንን ጨምሮ አብዛኞቹ ቡድኖቹ በወጣት ተጫዋቾች አለመታካታቸዉ፤ ለዚህ ዉጤት እንዳበቃቸዉ ተናግረዋል።

የእግርኳስ የዓለምን ህዝብ የሚያቀራርብ ሰላማዊ ግጥምያ በመሆኑለብዙ ሃገራት ባህላዊ የሆነ የመጣ የስፖርት አይነት መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። የኳታሩን ዋንጫ ማን ከፍ ያደርግ ይሆን ፈረንሳይ ወይስ አርጀንቲና። በሳምንቱ መጨረሻ ብዙዎች ግጥምያዉን እና አሸናፊዉን በጉጉት እየተጠባበቁ  ነዉ። ቃለ ምልልስ የሰጡንን በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ