1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ወጣቶች በአሕጉሪቱ ስለሚታዩ ግጭቶች ምን አስተያየት አላቸዉ?  

ዓርብ፣ ጥቅምት 30 2011

የአፍሪቃ ወጣቶች በአህጉሪቱ በሚገኙ የተለያዩ ሃገራት የሚታዩት የእርስ በርስ ግጭትና ስደት ምን ያህል አሳሳቢነቱን ይረዳሉ ይላል የእለቱ 77 % በተሰኘዉ የ « DW » ያዘጋጀዉ ርዕስ። በኢትዮጵያ ስላለዉ ሁኔታ ከአምስት ዓመት በላይ በእስር ላይ የነበረና በጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ሥልጣን ዘመን ከእስር ነፃ የሆነን ወጣት አነጋግረናል።

https://p.dw.com/p/37yZp
Kamerun Bamenda Schüler entführt
ምስል Reuters/B. Eyong

የአፍሪቃ ወጣቶች በአህጉሪቱ በሚገኙ የተለያዩ ሃገራት የሚታዩት የእርስ በርስ ግጭትና ስደት ምን ያህል አሳሳቢነቱን ይረዳሉ ይላል የእለቱ 77 % በተሰኘዉ የ « DW » የአፍሪቃ እንጊሊዘኛ ስርጭት ክፍል ያዘጋጀዉ ርዕስ። በካሜሩን በደቡብ ሱዳን፤ እንዲሁም በዴሞክራቲክ ኮንጎ የእርስ በርስ ጦርነቶች ዓመታትን አስቆጥረዋል፤ በሌሎች የአህጉሪቱ ክፍሎች እዚህም እዝያም የሚታዩት ግጭቶች ግጭቶች በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን በሃገር ዉስጥ እና ከሃገር ዉጭ አፈናቅሎአል? የዛሬዉ ዝግጅታችን በካሜሩን ያለዉን ሁኔታ በአጭሩ ዳሰን ወጣት በባህርዳር ነዋሪ የሆነዉን ወጣት ደህናሁን ቤዛን ጋብዘናል መልካም ቆይታ።  
በ 1990 ዎቹ በተለይ በአዉሮጳ ምርጥ የሙዚቃ መዘርዝር ለሳምንታቶች የመጀመርያዉን ቦታ ይዞ የቆየዉ የታዋቂዉ ካሜሩናዊ አሌን ቬዝ ሙዚቃ ነበር።  24 ሚሊዮን ነዋሪዎች የሚገኙባት ማዕከላዊ አፍሪቃዊትዋ አፍሪቃ ሃገር ካሜሩን ፤ በ 1884 ዓመት ግድም በጀርመን ቅኝ ግዛት የነበረችና ከአንደኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲህ ደግሞ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆኑት የካሜሩን ግዛቶች በፈረንሳይ ስር ፤ እንጊሊዘኛ ተናጋሪ የሆኑት ደግሞ በብሪታንያ ቅኝ ግዛት ሥር ወድቀዉ ቆይተዋል። በፈረንሳይ ቅን ግዛት ሥር የነበረዉ የካሜሩን ግዛት በ 1960 ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ተላቅዋል፤ በብሪታንያ ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩት የካሜሩን ግዛቶጭ በ 1961 ዓም ከብሪታንያ እጅ ሥር መዉጣታቸዉ የታሪክ ማኅደራት ያሳያሉ።  በካሜሩን 80 % ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሲሆን 20% ዉ ደግሞ ኢንጊሊዘኛ ተናጋሪ ነዉ። የብሪታንያ ቅኝ ግዛት የነበሩ ሁለት የካሜሩን ግዛቶችን ከያዉንዴ ማዕከላዊ አስተዳደር ነፃ ለመዉጣት የሚፈልጉ ኃይላት ከጎርጎረሳዉያኑ 2016 ጀምሮ በተደጋጋሚ አመፅ አድማ እያደረጉ ነዉ። እነዚሁ ነፃነትን የሚፈልጉ ኃይላት በጎርጎረሳዉያኑ 2017 መጨረሻ  የ«አምባዞኒያ አስተዳደር» የተባለ መንግሥት እንደሚመሰርቱ በአደባባይ ሰልፍ ካስታወቁ በኋላ ነበር የአምባዞኒያ ሪፐብሊክ የተባለች አገር መመሥረታቸው ያወጁት ።  
በዚህ ሳምንት ማክሰኞ  ሰባተኛ ዓመት የሥልጣን ዘመናቸዉን የጀመሩት የካሜሩን ፕሬዝደንት ፖል ቢያ፤ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሕዝብ በብዛት የሚኖርባቸዉን ግዛቶችን ከያዉንዴ ማዕከላዊ መንግስት አገዛዝ ለመገንጠል የሚዋጉ ኃይላትን እንደሚያጠፉ ዝተዋል። ከነፃነት በፊት የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች ይገዙት በነበረዉ አካባቢ የሚኖረዉ ሕዝብ፤ በፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች ይገዛ ከነበረዉ አካባቢ በተሰየመዉ መንገሥት እየተደበለ ነዉ የሚሉ ወገኞች ካለፈዉ ዓመት ጀምሮ የፕሬዝደንት ቢያን መንግሥት እየተቃወሙ ነዉ። ተቃዉሞዉ  ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት እየተቀየረ፤ በሃገሪቱ ሕጻናት መታገት መለቃቃቸዉ ሁሉ እየተሰማ ነዉ። እንዲህ አይነቱ ሁኔታ በካሜሩን ብቻ ሳይሆን በደቡብ ሱዳን በካሜሩን ጎረቤት ሃገር በዴሞክራቲክ ኮንጎም አልፎ አልፎ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ይታያሉ። በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል። አፍሪቃዉያን ወጣቶች  እንዲህ አይነቶቹ ግጭቶች በሃገር በማኅበረሰብ ምን ያህል አስከፊ ነገርን ይዘዉ ሊመጡ እንደሚችሉ ምን ያህል ይረዱታል ስል በባህርዳር ነዋሪ የሆነዉን የ 28 ዓመት ወጣቱን ደህናሁን ቤዛ ን ጠይቄዉ ነበር።
ደህናሁን ቤዛ ለአምስት ዓመት በእስር ላይ በነበረበት ወቅት በርካታ እንግልትና መከራ እንደደረሰበት አሁንም በደረሰበት ድብደባ ጤንነቱን እንዳጣ ተናግሮአል። ደህናሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ መሐመድ ወደ ሥልጣን እንደመጡ የአምስት ዓመት እስሩን ጨርሶ በቀጣይ ታስሮ ከነበረበት መለቀቁን ተናግሮአል። እንደ ወጣት ደህናሁን ኢትዮጵያዉያን ወጣቶች ሃገራቸዉን ከግጭት ከጥፋት መጠበቅ እንዳለባቸዉ እንዲህ ይናገራል። ከወጣት ደህና ሁን ቤዛ ጋር የተደረገዉን ሙሉ ቃለ ምልልስ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመቻን ይከታተሉ ።

አዜብ ታደሰ

ተስፋለም ወልደየስ