1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ከልጅነት ልምሻ ነፃ መሆንና ኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 26 2012

ባሳለፍነው ሳምንት ነው አፍሪቃ ከልጅነት ልምሻ ማለትም ፖሊዮ ነፃ የመሆኗ ዜና የተበሰረው። ለዓመታት ጥረት የተደረገበት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትን ለሽባነት የሚዳርገውን ተሐዋሲ የማጥፋቱ ዜና ኮቪድ 19 ከባድ ስጋት በሆነበት በዚህ ወቅት መሰማቱ እንደ አንድ እፎይታ ተወስዷል። ፈንጣጣ ታሪክ እንደሆነ ሁሉ ፖሊዮም ፈለጉን መከተሉ ይሆን?

https://p.dw.com/p/3hsQC
Nigeria Polio Virus Impfung
ምስል picture-alliance/dpa/M. Wolfe

«የአፍሪቃ ከልጅነት ልምሻ ነፃ መሆንና ኢትዮጵያ»

በጎርጎሪዮሳዊው 1996 ዓ,ም ነበር የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች 32ኛ ጉባኤያቸውን ያውንዴ ካሜሮን ላይ ሲያካሂዱ ልጆችን በለጋ ዕድሜያቸው ለአካል ጉዳት የሚዳርገውን የልጅነት ልምሻ ልክ ፈንጣጣ እንደጠፋው ለማጥፋት ቃል የተገባቡት። በዚያን ወቅት በየዓመቱ በዚህ በሽታ ምክንያት 75 ሺህ የሚሆኑ ልጆች ለሽባነት ይዳረጉ እንደነበር የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም ክትባቱ በዘመቻ መልክ መሰጠቱን ቀጠለ። ጥረቱም 1,8 ሚሊየን የሚሆኑ ሕጻናትን ከዕድሜ ልክ ሽባነት ሲከላከል፤ 180 ሺህ ሕይወት ማትረፉ ይነገራል። የዓለም የጤና ድርጅት አፍሪቃ ከዚህ ተሐዋሲ ነፃ የመሆኗ ዜና በተነገረበት ዕለት 90 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ከዚህ አደገኛ ተሐዋሲ ነፃ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። አሁን የዚህ የጤና ችግር ስጋት ያለው በግጭት ጦርነት በሚታመሱት ፓኪስታንና አፍጋኒስታን ውስጥ መሆኑንም ገልጿል።

የልጅነት ልምሻ ማለትም ፖሊዮን የማጥፋቱ የተጠናከረ ዘመቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲደረግም ኢትዮጵያን ጨምሮ የመደበኛ ክትባት አገልግሎት፣ ይህንንም በዘመቻ መልክ ማጠናከርና ማዳረስ፣ እንዲሁም የበሽታ ቅኝት ማካሄድ ዋነኛ ሥራዎች ነበሩ። በዚህ መሠረትም በተለይ ኢትዮጵያ ከዛሬ አራት ዓመት ጀምሮ ከዚህ ተሐዋሲ ነፃ ሆና መሰንበቷን በጤና ሚኒስቴር የብሔራዊ ጤና የክትባት መርሃግብር አስተባባሪ አቶ ሙላት ንጉሥ ገልፀውልናል።

Symbolbild | Masern Impfung
ምስል imago/blickwinkel

በጎርጎሪዮሳዊው 2009 ዓ,ም  ኬንያ ከዚህ በሽታ ነጻ መሆኗ ይፋ ሲደረግ ነበር አብሮ ኢትዮጵያም ከአንድ ዓመት በፊት ከበሽታው መላቀቅ መቻሏ የተነገረው። ከኢትዮጵያ ቀደም ብላ ከበሽታው ነፃ መሆኗ በተነገረላት ጎረቤት ሶማሊያ ውስጥ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ዳግም 70 ልጆች ላይ ተሐዋሲው ተገኘ። ተዛማቹ በሽታ በዚያ ብቻም አላበቃም ኬንያ እና ኢትዮጵያ ውስጥም እንደገና ታየና የማጣራት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ከሰባት ዓመት በፊት በዚህ መሰናዶ ባለሙያ በማነጋገር ማቅረባችን ይታወስ ይሆናል። በድረ ገጻችንም መረጃው ይገኛል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው አፍሪቃ ውስጥ የመጨረሻው ታማሚ ናይጀሪያ ውስጥ የተገኘው በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ነበር። ከዚያ ወዲህ በተደረገው ክትትል መሠረትም እስካለፈው ሳምንት ማክሰኞ ድረስ የታየ ነገር ባለመኖሩ አፍሪቃ ከበተፈጥሮ ከሚመጣው የፖሊዮ ተሐዋሲ ነፃ ሆነች የሚለው መልካም ዜና ዓለምን አዳረሰ።

አሁን በአፍ የሚሰጠው የዚህ በሽታ ክትባት የዛሬ 65 ዓመት ገደማ መገኘቱም ለዚህ ስኬት ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉ ይነገርለታል። በርካታ ተቋማትም ክትባቱ እንዲዳረስ የየበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል አሁንም እያደረጉ ነው። ካለፈው ተሞክሮና ከበሽታው ባሕሪ በመነሳት ይህ የጤና ችግር እንደገና እንዳይመጣ መደረግ በሀገርም ሆነ በአህጉር ደረጃ ሊደረግ የሚገባውን አቶ ሙላት ይናገራሉ። ፖሊዮ ይገኝባቸዋል ተብለው የሚጠቀሱት የፀጥታ ችግር ያለባቸው አፍጋኒስታንና ፓኪስታን መሆናቸውን የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል። አንዳንድ ቦታዎች በተለይ በሽታው ይስፋፋባቸዋል ተብለው እንደሚገመቱና የዘመቻው ትኩረት እንደሚሆኑም ይነገራል። ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያሉ አካባቢዎች የትኞቹ ይሆኑ?

Nigeria Polio Virus
ምስል Getty Images/AFP/P. Utomi Ekpei

አሁን ዓለም ከአፍሪቃ በተፈጥሮ የሚመጣውና በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚዛመተው የልጅነት ልምሻ ተሐዋሲ በመጥፋቱ ቢደሰትም ከክትባቱ ጋር በተገናኘ ይከሰታል የሚባለው የፖሊዮ አይነት በ16 ሃገራት ውስጥ እየታየ መሆኑን፤ ይህ ደግሞ በቂ ክትባት ካለማግኘት ጋር እንደሚገናኝ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ከእነዚህ ሃገራት አንዷ ሱዳን ናት። ከበሽታው ተላላፊነት አኳያ ስጋቱ እንዴት ይታያል? አፍሪቃ እንዲህ ካለው ተዛማች በሽታ ነጻ የመሆኗ ዜና ሲነገር ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በጎርጎሪሳዊው 1979 ኅዳር ወር ማለቂያ ላይ ነበር አፍሪቃ ከሰው ወደሰው ተላላፊ ከነበረው ፈንጣጣ በሽታ ነጻ የመሆኗ ብስራት የተሰማው። ያኔም በሽታው ስለመጥፋቱ ከመነገሩ ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ ታማሚዎች የተገኙት በጎረቤት ሶማሊያ እንደነበር የዓለም የጤና ድርጅት መዝግቦታል። ስለበሽታው ታሪክ ሲወሳ ብዙ ሺህ ዓመታት ወደኋላ ያስቆጥር ለነበረው የጤና ችግር ክትባት መገኘቱ ለህክምናው ዘርፍ ታላቅ ስኬት ነበር። የልጅነት ልምሻ ክትባትም አሁን ለዚህ በቅቷል። ተሐዋሲውን ለመከላከል የሚያስችለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠሉም የተገኘውን ውጤት ያሰነብተዋል ተብሎ ይታሰባል።

ሸዋዬ ለገሠ