1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ አውሮጳ ሕብረት ጉድኝት

ቅዳሜ፣ የካቲት 5 2014

ትኩረት በአፍሪቃ የአፍሪቃ ሕብረት እና የአውሮጳ ሕብረት ጉድኝትን እንዲሁም ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የሚንቀሳቀሱባት ሊቢያን ወቅታዊ ፖለቲካ ይቃኛል።

https://p.dw.com/p/46u4a
Deutschland | G20 | Compact with Africa meeting in Berlin
ምስል Michele Tantussi/REUTERS

ትኩረት በአፍሪቃ

በመጪው ሳምንት የአውሮጳ ሕብረት እና የአፍሪቃ ሕብረት ስድስተኛው የትብብር ጉባኤ ብራስልስ ላይ እንደሚካሄድ ይጠበቃል። አውሮጳም ቁልፍ አጋር ላለችው አህጉር መሠረተ ልማት ማስፋፊያ  በሚል በርከት ያለ ገንዘብ መመደቧን ይፋ አድርጋለች። የአውሮጳ ትኩረት ወደ አፍሪቃ መሳብ የጀመረው አሁን አይደለም። አስቀድሞ በንግዱ ቀጣና እና መስመር በመካከለኛው ምሥራቅ ከአረብ ብሎም በደቡብ ምዕራብ እስያ ከኦቶማን ሥርወ መንግሥታት የሚጣልባቸውን ቀረጥ ለመሸሽ ሲያማትሩ በደቡባዊ እና ምሥራቃዊ አፍሪቃ ወደቦች ላይ ዓይናቸውን ጥለው አካባቢው ላይ የበላይነታቸውን አስጠብቀው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። አውሮጳ 54 ሃገራትን ካካተተችው በመልክአ ምድር በቅርብ ከምትጎራበተኝ አፍሪቃ ጋር በጉድኝት ለመሥራት ስነሳ ,አህጉሪቱ ጋር በምጋራው የዳበረ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የጋራ እሴት እና ፍላጎት ስላለኝ ነው ትላለች። በአፍሪቃ - የአውሮጳ ሕብረት ጉድኝት አማካኝነትም በፖለቲካ እና በፖሊሲ ውይይቶች አብሮ በመሥራት ከአፍሪቃ ጋር ያለውን የትብብር ግንኙነት መግለጽ እንደሚፈለግም አመላክታለች። የአፍሪቃ እና የአውሮጳ ሕብረት ጉድኝት የተሰኘው መርሃግብር የተመሠረተው በጎርጎሪዮሳዊው 2000 ዓ,ም ካይሮ ላይ በተካሄደው የመጀመሪያ የሁለቱ አህጉራት ሕብረቶች ጉባኤ አማካኝነት ነው። ጉድኝቱ ከምሥረታው ጉባኤ ሰባት ዓመታት በኋላ ሊዛቦን ላይ በተካሄደው ሁለተኛው የአውሮጳ ሕብረት እና የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ ላይ በጸደቀው የሁለቱ አህጉራት ሕብረት ስልት በምህጻሩ JAES ደንቦች እንደሚመራ የአውሮጳ ኮሚሽን መረጃዎች ያሳያሉ። የአፍሪቃ እና የአውሮጳ ተጓዳኞች ይፋዊ በሆኑ በመሪዎች፣ እንዲሁም በሚኒስትሮች እና በየሕብረቱ ኮሚሽኖች ደረጃ በሚካሂድ ውይይቶች ትብብሮቻቸውን የማጠናከር ሥራዎችን ያከናውናሉ።  

Ministerkonferenz EU und Afrikanische Union zur Migrationspolitik
ምስል picture-alliance/ dpa

 የዛሬ አምስት ዓመት የተካሄደው አምስተኛው የአፍሪቃ ሕብረት እና የአውሮጳ ሕብረት ጉባኤ «ሁሉን አቀፍ እድገት እና ዘላቂ ልማትን ለማፋጠን ወጣቶች ላይ አስፈላጊውን አቅም ማዋል» የሚል የጋራ መግለጫ አውጥቷል። የአውሮጳ እና የአፍሪቃን ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ትስስርን በማሰብም በተለይ ወጣቶች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ አራት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የማገባ የተባሉት ዘርፎች ተለይተዋል።

በትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኒዎሎጂ እና በክህሎት እድገት አማካኝነት የሰዎችን አቅም ማሳደግ፤ ሰላም፣ደህንነት እና አስተዳደርን ማጠናከር፤ ለአፍሪቃ መዋቅር እና ዘላቂ ለውጥ መዋዕለ ንዋይን ማሰባሰብ፤ እንዲሁም በስደት እና እንቅስቃሴ ላይ ያተኮሩ ፖሊሲዎች ቀዳሚዎቹ ተደርገዋል።

ከፊታችን ባለው ሳምንት በአውሮጳ ሕብረት መቀመጫ ብራስልስ ቤልጂየም እንደሚካሄድ ከሚጠበቀው የአፍሪቃ አውሮጳ ሕብረት ጉባኤ አስቀድሞ የአውሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ለአፍሪቃ ከ151 ቢሊየን በላይ ዩሮ መመደቡን ይፋ አድርጓል። የኮሚሽኑ ፕሬዝደንት ዑርዙላ ፎን ደር ላይን ለቀናት ጉብኝት ባደረጉባት የወቅቱ የአፍሪቃ ሕብረት ሊቀመንበርነት በያዘችው ሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ላይ ሐሙስ ዕለት ይኽንኑ ገልጸዋል።

Senegal Ursula von der Leyen und Präsident Macky Sall
ምስል Christophe Licoppe/EU-Kommission/picture alliance

«በዛሬው ዕለት ከ150 ቢሊየን  በላይ ዮሮ በአፍሪቃ አውሮጳ መርሃግብር አማካኝነት መመደቡን ይፋ ሳደርግ ኩራት ይሰማኛል። ይኽ በዓለም አቀፍ ደረጃ መሠረተ ልማት ላይ ያተኮረ የመጀመሪያው አህጉራዊ ዕቅድ ነው። በአውሮጳዊ ቡድን የሚመራ ሲሆን ተግባራዊነቱ በእናንተ ተጓዳኝነት ይከናወናል።»

የአውሮጳ ሕብረት በመላው ዓለም እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2027 ዓ,ም ባሉት ዓመታት በመንግሥት እና በግሉ መሠረተ ልማት ዘርፍ የ300 ቢሊየን ዮሮ መዋዕለ ነዋይ ፍሰት ሥራ ላይ ለማዋል አቅዷል። ገንዘቡም የአውሮጳ ሕብረትን የተለያዩ የገንዘብ ድጋፎች፣ የአባል ሃገራት የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት እንዲሁም በአውሮጳ የመዋዕለ ነዋይ ባንኮች የተሰባሰበ ካፒታሉን እንደሚያካትት ተገልጿል። በበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት በመሠረተ ልማት እና መንገዶች ግንባታ በሰፊው እየተንቀሳቀሰች የምትገኘው የቻይና ይዞታ የገፋው ሳይሆን እንዳልቀረ የሚነገርለት የአውሮጳ ሕብረት ተነሳሽነት በቀጣይ ሳምንት ብራስልስ ላይ ከአፍሪቃ ሕብረት ጋር በሚካሄደው ስድስተኛ ጉባኤ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳው ገንዘብን ሥራ ላይ ማዋል እንደሚሆን ፎን ደር ላይን አጽንኦት ሰጥተዋል።

«መዋዕለ ንዋይ ፍሰቶች የጉባኤው ማዕከላዊ መነጋገሪያ ጉዳይ ይሆናሉ፤ ምክንያቱም የምንጋራቸው ፍላጎቶቻችን ማሳኪያ መንገዶች ናቸውና።  አውሮጳ ይኽን በተመለከተ ለአፍሪቃ እጅግ አስተማማኝ ከመሆኗም ሌላ በጣም አስፈላጊ ተጓዳኝ ናት።»

ረቡዕ ዕለት ዳካር የገቡት የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዑርዙላ ፎን ደር ላይን የአውሮጳ ሕብረት እና ሴኔጋል ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው በመጠቆም ጉብኝታቸው የሁለቱን ወገኖች ጉድኝት ጠቀሜታ አጽንኦት እንደሚሰጥላቸውም ተናግረዋል። ሴኔጋል በዲጂታል እና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለማደግ የምታደርገውን ጥረትም አድንቀዋል። ሁለቱ አህጎሮች የጋራ ፍላጎት እንዳላቸው ያመለከቱት፤ የአውሮጳ ሕብረት ኮሚሽንን በዋና ከተማቸው ተቀብለው ያስተናገዱት የወቅቱ የአፍሪቃ ሕብረት ሊቀመንበር እና የሴኔጋል ፕሬዝደንት ማኪ ሳል በበኩላቸው አፍሪቃ ከአውሮጳ ሕብረት አዲስ፣ ዘመናዊ እና ንግድ ላይ ያተኮረ ተጓዳኝነትን እንደምትጠብቅ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

Äthiopien Afrikanische Union Addis Ababa
የሴኔጋል ፕሬዝደንት ማኪ ሳልምስል Tony Karumba/Getty Images/AFP

«አውሮጳ እና አፍሪቃ በጋራ መሥራት ይኖርባቸዋል፤ በመጀመሪያ በመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ተቀራራቢ በመሆናቸው፤ የሁለቱ አህጎራት ሰላም እና መረጋጋት በቅርብ የተያያዘ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በሰብአዊ እና ተፈጥሯዊ ሃብቶች እንዲሁም የልማት ፍላጎቶች የጋራ ዕድገት እና ብልጽግና አፍሪቃ ለአውሮጳ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ዕድሎች እና የተጓዳኝነት ዕድሎችን ታቀርባለች።»

Afrika-China-Beziehungen | Xi Jinping
ምስል Huang Jingwen/Xinhua/picture alliance

የአፍሪቃ ጥሬ ሃብት ትኩረቷን እንደሳበው የሚታመነው ቻይና ገንዘቧን ሥራ ላይ ባዋለችባቸው ሃገራት የሰብዓዊ መብቶች ይዞታውም ሆነ የአካባቢ ተፈጥሮ ላይ የሚደርሰው ጉዳት አያሳስባትም በሚል ትወቀሳለች። በዚህ ረገድ በሩሲያም ላይ የሚቀርበው ትችት ተመሳሳይ ነው። ከዚህም ሌላ ቻይና ከፍተኛ ብድርስ እየሰጠች የአፍሪቃ ሃገራትን ሊከፍሉት በማይችሉት የዕዳ ወጥመድ ውስጥ ጥላቸዋለች በሚል በጽኑ ትችት ይቀርብባታል። ወቀሳውን የምታጣጥለው ቤጂንግ በበኩሏ የምትሰጠው ብድር ድህነትን ለመቀነስ ይረዳል በሚል ትሞግታለች። በአውሮጳ በኩል የሕብረቱ የወቅቱን ሊቀመንበርነት የተረከበችው ፈረንሳይ ናት። ፕሬዝደንቷ ኢማኑዌል ማክሮ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሃገሮችን በማስተባበር ነጻ የንግድ ትብብር ለማመቻቸት ትሠራለች ብሎ ቢገመትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ፈረንሳይ አፍሪቃ ውስጥ በገጠማት ተቃውሞ ምክንያት ውጤታማ የመሆኑ ጉዳይ አነጋጋሪ ነው።

                                             ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትር ያደናገራት ሊቢያ

Libyen | Checkpoint von Soldaten in Tripolis
ምስል Mahmud Turkia/AFP/Getty Images

ከ40 ዓመታት በላይ ሊቢያን የገዙት መሐመድ ጋዳፊ በአብዛኛው የአረብ ሃገራት ውስጥ የተቀሰቀሰውን አብዮት ተከትሎ በጎርጎሪዮሳዊው 2011 ዓ,ም ጥቅምት ወር ከተገደሉ ወዲህ ሀገሪቱ ከትርምስ አልወጣችም። ጋዳፊን ገድለው ዋና ከተማዋን የተቆጣጠሩት አማጽያን ከበርካታ ወራት በኋላ ለብሔራዊ አጠቃላይ ምክር ቤት የሽግግር ሥልጣኑን ቢያስረክቡም ሊቢያ ውስጥ እየከፋ የሄደው የደህንነት ስጋት በወቅቱ ቤንጋዚ የነበሩት ሦስት የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን ሕይወት እስከመቅጠፍ ደረሰ። በመቀጠልም አብዛኞቹ የውጪ ሃገራት ዲፕሎማቶች ሊቢያን ለቅቀው ወጡ።  ጀሃዲስቶች ተጠያቂ የሆኑባቸው በርካታ ጥቃቶችም በየቦታው ይደርሱ ጀመር። በጎርጎሪዮሳዊው 2014 ሰኔ ወር ምርጫ ተካሂዶ ጸረ አክራሪ ሙስሊሞች የበረከቱበት ምክር ቤት ተቋቋመ። ሆኖም ከፍተኛ ተቃውሞ ከዚያኛው ወገን ገጠመው። ዓለም አቀፍ ዕውቅናውን የያዘው ብሔራዊ አጠቃላይ ምክር ቤት ወደ ምሥራቃዊቱ ከተማ ቶቡርክ መቀመጫውን አዛወረ። በመሃሉም ተቃዋሚው ወገን ምዕራብ ትሪፖሊ ላይ የራሱን ከፍተኛ ምክር ቤት አቋቋመ። በዚህ ጊዜም ሊቢያ ሁለት አስተዳደር እና ሁለት ሥራ አስፈጻሚ አካላት ያላት ሀገር ሆነች። ከብዙ ጥረቶች በኋላ በቀጣዩ ዓመት ተቀናቃኞቹ ምክር ቤቶች ሞሮኮ ላይ ብሔራዊ መንግሥት ለመመሥረት ስምምነት ደርሰው ተፈራረሙ። የቶቦርኩን ምክር ቤት ይመሩ የነበሩት ፋይዝ አል ሲራጅ ወደ ትሪፖሊ ሄደው አዲስ አስተዳደር ለመመሥረት ሲንቀሳቀሱ የምሥራቁ የጦር መሪ ካሊፋ ሀፍታር እና ከቶቦርክ ጠቅላላ ጉባኤ ዕውቅና ነፈጋቸው። አንዳቸው ሌላቸውን ለማስወገድም ውጊያ ከፈቱ። በሊቢያው የእርስ በርስ ጦርነት ሩሲያ፣ ግብጽ እንዲሁም አረብ ኤሜሬትስ በአንድ በኩል ቱርክ እና ተባባሪዎቿ በሌላ ወገን ሆነው ተፋልመዋል። የቱርክ ድጋፍ ያለው የትሪፖሊው አስተዳደር የሀፍታርን ኃይል ይዞታ ገፍቶ ካዳከመ በኋላ ተቀናቃኝ ወገኖች የዛሬ ሁለት ዓመት ጄኔቫ ላይ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደረሱ። ባለፈው ዓመትም ታኅሣስ ወር ላይ የምክር ቤትም ሆነ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለማካሄድ ተስማሙ።

Libyen | Polizeikräfte
ምስል Mahmud Turkia/AFP/Getty Images

ባለፈው ዓመት መጋቢት ወርም በጊዜያዊነት የሊቢያ ልዑካን ሀገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲያስተዳድሩ አብዱልሀሚድ ድባቢህ በተመድ አማካኝነት በተደረገው ሂደት ተቀበሉ። የቶብሩክ ምክር ቤት የምርጫ ሕጎችን አዘጋጀ። የጋዳፊ ልጅ ሳይፍ አል ኢስላም፤ ዲባቢህ እና ሀፍታርም ለእጩነት ራሳቸውን አዘጋጁ። ማንኛውም ይወዳደሩ በሚለው ውዝግብ ተጀመረ። የምርጫው ወቅት ሲቃረብ የሀፍታር ደጋፊዎች ከአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች ጋር ይታኮሱ ጀመር። ውጥረቱ በመባባሱም ምርጫውን የማካሄድ ሥልጣን የተሰጠው ኮሚቴ ታኅሣስ 15 ቀን 2014 ዓ,ም ለሊቢያ የመጀመሪያ የሆነውን ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል ይፋ አደረገ። ጥር ወር ላይ ወትሮም ውጥረት በነበረት በምሥራቁ ምክር ቤት እና በምዕራብ ትሪፖሊ በኩል በሚገኘው በአብዱልሀሚድ ድባቢህ አስተዳደር መካከል ችግሩ ተባባሰ። ሐሙስ ዕለት የምሥራቁ ምክር ቤት የቀድሞ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር እና የተዋጊ ጀት አብራሪ የነበሩትን ፋትህ ባሻጋን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰየመ። ይኽም ያለችበት ውጥንቅጥ ሳያንሳት ሊቢያን ብቸኛዋ ባለሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሀገር አደረጋት። አዲስ የተሰየሙት ፋትህ ባሻጋም ወደ ትርፖሊ በመሄድ ሁሉንም ያካተተ መንግሥት ለመሆን እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

Libyen | Fathi Bashagha kandidiert als Präsident
አዲስ የተሰየሙት ሁለተኛው የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትርምስል Hazem Turkia/AA/picture alliance

«መጪው መንግሥት ለሁሉም የሚሆን እና ሁሉንም የሚያካትት ይሆናል። ማንንም ሳናስቀር ሁሉንም እንደርሳለን። ከፓርላማው እና ከሀገሪቱ ምክር ቤት ጋር ሁልጊዜም እንተባበራለን። ምክንያቱም መንግሥት ከሥራ አስፈጻሚ አካላት ጋር ካልተባበረ እና ካልሠራ ስኬታማ ሊሆን አይችልም።»

ከዚህ ሌላ «ለጥላቻ፣ ለብቀላ ወይም ሚዛናዊ ላለመሆን ቦታ የለም ያሉት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሁንም እያንዳንዱን የሊቢያ ዜጋ ለመድረስ እንጥራለን ሲሉ ቃል ሰጥተዋል።

«በአስቸጋሪ ወቅት ኃላፊነት የወሰደውን በአብዱልሃሚድ ደባቢህ የሚመራውን የአንድነት መንግሥት ማመስገን እፈልጋለሁ። ይኽ ዴሞክራሲ በሰላማዊ መንገድ ሥልጣንን ማስተላለፍን ያረጋግጣል።»

በተመድ የሚደገፈው የሊቢያ የአንድነት መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ደቢባህ እና አዲስ የተሰየሙት ባሻጋ ጠንካራ ከሚባለው የምዕራብ ሊቢያ ግዛት ሚስራታ የተገኙ በመሆናቸው ሁለቱም ደጋፊዎች እንዳሏቸው ታዛቢዎች ይናገራሉ። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሰየማቸው ከሰዓታት ብፊት ከተደረገባቸው የመግደል ሙከራ የተረፉት ደቢባህ ሥልጣኑን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አይመስሉም። ይኽም ሊቢያን ዳግም ወዴት ያመራት ይኾን የሚል ስጋትን አስከትሏል። የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ሁለቱም ወገኖች ሊቢያን እንደተረጋጋች ማስቀጠሉን ቅድሚያ ሊሰጡት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሸዋዬ ለገሠ