1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ቀንድና የቻይና ግንኙነት

ሐሙስ፣ ሰኔ 16 2014

ቻይና እና የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በሰላም ፣ በመልካም አስተዳደር እና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኞ እና ትናንት በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉባኤ ለቀጣናው ተስፋን የሚያጭር መሆኑ ተነገረ። በመጀመሪያው የቻይና - አፍሪካ ቀንድ የሰላም ፣ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጉባኤ ላይ ከኤርትራ በስተቀር ተሳትፈዋል።

https://p.dw.com/p/4D8xG
China Flagge vor Vollmond
ምስል AP

የቻይና - አፍሪካ ቀንድ ጉባኤ ከኤርትራ አልተካፈለችም

 

ቻይና እና የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በሰላም ፣ በመልካም አስተዳደር እና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኞ እና ትናንት በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉባኤ ለቀጣናው ተስፋን የሚያጭር መሆኑ ተነገረ።
በእርስ በርስ ጦርነት እና ግጭት፣ በጠንካራ መንግሥት እጦት፣ በሽብር ጥቃቶች ፣ በድንበርና የጎሳ ውዝግብ የሚታበጡት የምስራቅ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ አገራት በጉባኤው ማብቂያ ችግሮቻቸውን በውይይትና በመግባባት ለመፍታት ተስማምተው ተለያይተዋል። 
ቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት እንዲሆን ፣ ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማድረግ ፣ አገራቱ ሉዓላዊነትን እና የግዛት አንድነትን በማክበር አንዱ አገር በሌላው ላይ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖረው ፣ ሽብርተኝነትን፣ ሕገ ወጥ የሰዎች እና የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከልም በውይይታቸው መስማማታቸውን ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። 
ቻይና ይህንን የሰላም ፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ገባኤ ማድረጓ መልካም እድል ነው ያሉት ቻይና በአፍሪካ ያላትን ተሳትፎ በቅርበት የሚከታተሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ቀጣናው በውስብስብ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ በአካባቢው ከፍተኛ ፍላጎት ያለው የምእራቡ ዓለም ይህንን የቻይናን በአፍሪካ ቀንድ የግንኙነት አድማሷን የማስፋት እርምጃ በበጎ ይመለከቱታል የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል። 
ቻይና በምስራቅም ይሁን በመላው አፍሪካ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ከማድረግ ባሻገር ለአገሮች ከፍተኛ ብድር የሰጠች መሆኑ ከበጎ ሊታይላት የሚገባ መሆኑንም ገልፀዋል።
የቻይና መንግሥት ከእነዚህ አገራ ጋር በልማት ፣ በሰላምና በአካባቢ መረጋጋት የመሥራት ፍላጎት ያሳየበት ጉባኤ መሆኑን የጠቀሱት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አገሪቱ ከበለፀጉት እና ግንባር ቀደም ኢኮኖሚ ካላቸው አገሮች አንዷ በመሆኗ መሰል ጉባኤ ማድረጓ አዲስ ነገር አለመሆኑን ተናግረዋል።
በመጀመሪያው የቻይና - አፍሪካ ቀንድ የሰላም ፣ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጉባኤ ላይ ከኤርትራ በስተቀር ሁሉም የምስራቅ አፍሪካ አገራት ማለትም ኢትዮጵያ ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳ ተሳትፈዋል።


ሰለለሞን ሙጬ 
አዜብ ታደሰ 
ነጋሽ መሐመድ