1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ባንድን ታሪክ ዘጋቢ ፊልም እየሰራ የሚገኘው ድርብድል አሰፋ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 13 2014

የፊልም ባለሙያው ድርብ ድል አሰፋ በአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ የመጀመሪያ ባንድ በሚባለው የአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ባንድ ላይ ያተኮረ የ90 ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም በመስራት ላይ ይገኛል። ድርብድል ከአንድ ዓመት በፊት በዶይቼ ቬለ አካዳሚ የወጣውን ውድድር በማሸነፍ በኢትዮጵያ እስከ 10 ሺህ ዩሮ የገንዘብ እና ሌሎች ድጋፎች እያገኙ ካሉ ባለሙያዎች አንዱ ነው።

https://p.dw.com/p/4ABPU
Äthiopien, Addis Abeba | Dirbdil Assefa, Äthipischer Filmemacher
ምስል Seyoum Getu/DW

የባህል መድረክ፦ የአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ባንድን ታሪክ ዘጋቢ ፊልም እየሰራ የሚገኘው ድርብድል አሰፋ

ውልደትና እድገቱ አዲስ አበባ ነው፡፡ የህይወት አቅጣጫውም ወደ አካደሚኩ ያመራ የሚመስል የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ነበር። በጎርጎሳውያኑ 2003 እና 2006 በፓለቲካል ሳይንስ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪውን ተከታትሎ ባጠናቀቀበት አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለስድስት ዓመታት ያህል በመምህርነትም አገልግሏል። በዚሁ በጎርጎሳውያን የዘመን ቀመር 2009 እና 2011 ከቶም ቪዲዮግራፊ እና ብሉናይል ፊልም እና ቴሌቪዥን አካዳሚ የተከታተላቸው የፊልም ስራ ሙያንም ጨብጧል።

ቀደም ሲል ከአካዳሚክ ህይወቱ ጎን ለጎን ያስኬድ የነበረው ሙያ ሙሉ ጊዜውን ጠቅልሎ ሊወስድ በቃ፡፡ የ42 ዓመቱ የፊልም ስራ ዳይሬክተር እና ጸሐፊ ድርብድል አሰፋ አቂርሶ፡፡ ድርብድል ባለፉት 10 ዓመታት ከ8 ያላነሱ አጫጭር እና ዶክመንተሪ ፊልሞችንም በሙያው አበርክቶ ለምልከታ አብቅቷል። ከአንድ ዓመት በፊት የጀርመኑ ዶይቼ ቬለ አካዳሚ በኢትዮጵያ የፊልም እድገትን ለመደገፍ የሚረዳውን የስልጠና እና ገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ተወዳድረው ካሸነፉ አምስት ፊልም ሰሪዎችም አንዱ ነበር፡፡

የፊልም ባለሙያው ድርብድል አሰፋ አቢይ ትኩረቱን በፊልም ዳይሬክተርነት እና ጸሐፊነት ላይ አድርጎ ይስራ እንጂ በፕሮዲውሰርነት ወይም ፊልሞችን ካስት በማድረግም ተሳትፎ አለው፡፡ እኔና ቤቴ፣ ግሽበት፣ ማካፈል፣ “WHICH DIRECTION TO GO? Becaus I Dear, the Broken Chain, Smokes Of Endurance, HORIZON BEAUTIFUL” በዳይሬክተርነት እና ካስቲንግ የተሳተፈባቸው ስራዎቹ ናቸው፡፡

Äthiopien, Addis Abeba | Dirbdil Assefa, Äthipischer Filmemacher
ድርብድል ሙሉ በሙሉ ፊቱን ወደ ፊልም ሙያ ከማዞሩ በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ነበር። ምስል Seyoum Getu/DW

በጀርመን የኢኮኖሚክ ትብብር እና ልማት ሚኒስቴር የሚደገፈው የዶይቼ ቬለ አካዳሚ የአንድ ዓመት በጀት፣ ስልጠና እና ክትትል ድጋፍ ለማግኘት ከአንድ አመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ በርካታ የፊልም ሰሪ ባለሙያዎች ጋር ተወዳደሮ ካሸነፉት 5 ባለሙያዎች አንዱ የሆነው ድርብድል፤ ለሱ ይሄ መልካም አጋጣሚ እንደነበር ይገልጻል፡፡

ድርብድል በዚህ ዶይቼ ቬለ ባመቻቸው የገንዘብና ስልጠና ድጋፍ ላይ በኦሮምኛ ቋንቋ በአንጋፋነቱ ብቻ ሳይሆን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተመሰረተው የድሬዳዋው የአፍራን-ቃሎ የሙዚቃ ባንድ ላይ ዘለግ ያለ የ90 ደቂቃዎች ዘጋቢ ፊልም እየሰራ ነው፡፡ በርግጥ የፊልም ባለሙያው ድርብድል ይህን ፕሮጀክት ዶይቼ ቬለ አካዳሚ ለ5 የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች የሚያደርገውን ድጋፍ ይፋ ከማድረጉና ከማወዳደሩም ከአንድ ዓመት በፊት የያዘው ነበር፡፡ “Children of Afran Qalloo Wake up” ለፊልሙ የተሰጠ ርዕስ ነው፡፡

Bildkombo Filmemacher DW
ከግራ፦ ፍሬሕይወት አድማሱ፣ ድርብድል አሰፋ፣ ቤዛ ኃይሉ፣ አብርሐም ገዛኸኝ እና ሔኖክ መብራቱ ለአንድ አመት የሚዘልቅ የገንዘብ እና የስልጠና ድጋፍ ከዶይቼ ቬለ አካዳሚ ያገኙ ኢትዮጵያውያን የፊልም ባለሙያዎች ናቸው።

ድርብድል አሰፋ ይህ በአፍረን-ቃሎ የሙዚቃ ባንድ ላይ እያሰናዳ የሚገኘው ታሪካዊ ዘጋቢ ፊልም የሚዘጋጀውም በአፋን ኦሮሞ መሆኑን ተናግሯል። የባንዱ መስራች አንጋፋ ሰዎችን ለማግኘት በቅርብ ጊዜ እንኳ ወደ አውሮፓ ጀርመን በማቅናት ካገኛቸው አንዱ ኢስማኤል ሙመድ ናቸው፡፡

ከዚህም ሌላ በአውሮፓው ጉዞ በተመቻቸው መድረክ በርካታ ልምድ ያላቸው የአገራት ፊልም ሰሪዎች በተሰባሰቡበት የፊልሙን ኢንደስትሪ ደረጃ ከመረዳት ጀምሮ ከፍ ያለ ልምድ የቀሰመበት እንደሆነም ያስረዳል፡፡

ዛሬ ላይ ቆሞ ነገውን ከፍ ለማድረግ ሚያልመው፤ በኢትዮጵያ የፊልም ኢንደስትሪ የራሱን ጉልህ አሻራ ስለማኖር የሚያቅደው ድርብድል አሰፋ ፊልም ለመሆን የሚጠባበቁ ጽሁፎች፤ ከመጽሐፍ ወደ ስክሪፕትነት የተለወጡ ስራዎችም በእጁ ላይ እንደሚገኙ አጋርቶናል፡፡ ፊልም ሆኖ ለመውጣት ቀን የሚጠባበቀው የአሲምባ ፍቅር መጽሃፍ እና በቅርቡ ለተመልካቾች አይን እንደሚደርስ የሚጠበቀው የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ታሪክ በሚል ወደ አማርኛ ተተርጉሞ የተሰናዳው መጽሃፍ በቴሌቪዥን ለመቅረብ ከጫፍ ደርሷልም ብሏል፡፡ አበበ ባልቻ፣ ሚካኤል ታምሬ እና ግሩም ዘነበ ደግሞ ይተውኑበታል፡፡

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

ስዩም ጌቱ